ወደ መቀሌ አቅንተው የተመለሱት ልዩ መልዕክተኞችና አምባሳደሮች ለሰላም ንግግሮች ጥረት ከማድረግ ይልቅ በሌላው ወገን የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ላይ መጠመዳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ልዩ መልዕክተኞቹና አምባሳደሮቹ ጉዳዩን የያዙበትና ያዩበት ሂደት ተገቢነት እንደሌለው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ወደ መቀሌ የተጓዙት ልዩ መልዕክተኞቹና አምባሳደሮቹ ለሰላም ንግግሮች በማያሻማ መልኩ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጫና ከማድረግ ይልቅ፤ በሌላው ወገን የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ላይ መጠመዳቸውን ተናግረዋል።
ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበረበት መመለስን በተመለከተ የመንግስት ፍላጎት ግልጽ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የሰላም ንግግሮችን ለማስጀመር የሚቻልባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ልዑኩ ከሰላም ንግግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ከመቀሌ መልስ ባወጣው መግለጫ ረጅም ርቀት የተሄደበትን እና መልስ የተሰጠበትን ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ የማቅረብ ጉዳይ መልሶ ማንሳቱን አምባሳደር ሬድዋን አንስተዋል።
ወደ ክልሉ ርዳታ በስፋት እየቀረበ ስለመሆኑ የአውሮፕላን በረራም ያለምንም ገደብ ስለመፈቀዱ የነዳጅ ጉዳይም መፍትሄ የተሰጠውና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን አምባሳደሩ በመልዕክታቸውገልጸዋል።
በድጋሚ መታወቀ ያለበት የሰላም ንግግሩ የሚመራው በአፍሪካ ኅብረት ብቻ ነው ሲሉም ነው አምባሳደር ሬድዋን ያስታወቁት።
(ኢ ፕ ድ)