የኢሕአፓን ምሥረታ እናክብር፣ ሰማዕታትን እንዘክር – በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)

July 4, 2022

ከዴቂቅ እስከ አዋቂ፣ ካልተማረ እስከ ሊቃውንት፣ ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉም የእምነት ተከታዮች፣ ጎሣዎችና ፆታዎች እኩል ተሰልፈው ለዲሞክራሲ፣ ለህዝብ እኩልነት፤ ለመሬት ላራሹና  ለዕድገት ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት ፓርቲ ነው።

ኢሕአፓ ለሥልጣንና ለግል ጥቅም አልቆመም። የጠየቀው ጥያቄ ቀላል ነበር፣  ሁሉንም የህብረተሰቡን አካላት በሙሉ ያካተተ የጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ምስረታ ነበር። ምክንያቱም ለውጡ የመጣው በወጣቱና በህዝቡ ትግል ቢሆንም ወታደሩ በጠብ መንጃ ኃይል ድሉን ነጥቆ ብቻውን አገር የማስተዳደር ብቃት ስለሌለው: ለውጡም በአስተማማኝነት ዘላቂና ህዝባዊ ግቡን ሊያሳካ የሚችለው ተጠያቂነት ያለባቸው የህዝብ ወኪሎች ሊመሩት ቢችሉ ኖሮ ነበር። የወታደሩ ኃይል ግን ሊያዳምጥ አልፈለገም። ካድሬዎቹንና አነመኢሶን የመሳሰሉትን ተባባሪዎቹን አሰልፎ በጉልበት ሥልጣን ላይ ወጣ። ትላልቅ የሀገር መሪዎች የነበሩትን አባቶች ካለምንም ፍርድ ረሸናቸው።  በተለይ በቀይ ሽብር ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ንፁሃን ዜጎች ተጨፈጨፉ።  ከ40 የሚበልጡ ጄነራሎችን በግፍ ረሽኖ ሀገሪቷን ካለመሪ አስቀራት። በመጨረሻ ሥልጣኑን ለሻቢያና ለወያኔ አስረክቦ ፈረጠጠ፣ ለዚህ ሁሉ ጉድ አበቃን።

የኢሕአፓ ጠላቶች ደርጎችና መኢሶኖች ብቻ አልነበሩም፣ ከውስጥ ሸአቢያና ወያኔዎች ነበሩ፣ ከውጪ ደግሞ እነርሱን ተገንጣዮቹን የሚረዱና ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ጠላቶች ባንድ ላይ በመተባበር በኢሕአፓ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሰነዘሩ:: ጀግኖቻችን ብዙ የጠላት ኃይል ጥለው መስዋዕትነት ከፈሉ:: በምዕራባዊያንና በዐረብ የጡት አባቶቻቸው  አቀነባባሪነት የተከናወነው የዚህ ደባ አንዱ ዓላማም የደርግን ውድቀት ተከትሎ የተበተነው የአንድነት ወታደራዊ ኃይል መሰባሰቢያ የሚሆነው ድርጅታዊ ጥላ እንዳይኖረው ነበር::  ኢሕአፓ ግን ከጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በስተቀር የማንም ድጋፍ አልነበረውም፣ ሀገሩን አይሸጥምና።

ታሪኩ እንዲህ ሆኖ ሳለ በተለይ የእነ ወያኔ ካድሬዎች የ60ዎቹ ትውልዶች ጥፋት እያሉ አርበኛውንና ባንዳውን ባንድ ላይ ለመጨፍለቅ ሲሞክሩ ማየት እጅጉን ያማል።  በተለያዩ ሥርዓቶች ሥር ባንዳዎችና  አርበኞች ነበሩ፣  አሁንም አሉ።  ኢሕአፓ ለሀገር አንድነትና ዕድገት ታገለ እንጂ ለጎጥ ወይ ለተለየ ጎሣ ወይ ለግል ጥቅም አልቆመም። ሃቁን ነው የምነግራችሁ።  ወደፊት መራመድ የምንችለው ካለፉት መልካምና መጥፎ ተሞክሮዎች በመማር እንጂ በመጥፎ ትርክት ወይንም የማይገናኙትን አካላት ባንድ ላይ በመጨፍለቅ አይደለም።

ለውድ ሀገራቸው ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ንፁሃን ዜጎችና አርበኞችን ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል፣ ነፍሳቸውን ይማርልን፣  ውድ አገራችንን ይጥብቅልን።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ብአዴን ሆይ! ነፍስ ይማር!!

Next Story

የምሥራች! አማራም እንደጓደኞቹ ጠቅ’ሎ ሊያብድ ውስን ሰዓቶች ቀሩት!! – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

Go toTop