“የሠላም አማራጩ ኢትዮጵያን የሚያድን እስከሆነ ድረስ እየጎመዘዘንም ቢሆን መቀበል አለብን” – አቶ ክርስቲያን ታደለ

May 7, 2022

ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር የሚመጣው የትኛውም የሠላም አማራጭ ኢትዮጵያን የሚያድን እስከሆነ ድረስ እየጎመዘዘንም ቢሆን መቀበል አለብን ሲሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለጹ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር የሚመጣው የሠላም መፍትሄና የሠላም አማራጭ ከግል ፍላጎትና አቋም አንጻር ላይዋጥልን፣ ሊያመንና ሊጎመዝዘን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያድን እስከሆነ ድረስ እየጎመዘዘንም ቢሆን መቀበል ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር የምናመጣው የሠላም መፍትሄና የሠላም አማራጭ ከግል ፍላጎትና አቋም አንጻር ላይዋጥልን፣ ሊያመንና ሊጎመዝዘን ይችላል ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ የሚጎመዝዝ እንኳን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚያድንና ህዝቡን ወደ ፊት የሚያሻግር እስከሆነ ድረስ እየጎመዘዘንም ቢሆን መቀበል ያለብን እውነት ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ መረዳት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል::

አቶ ክርስቲያን፤ “ኢትዮጵያውያን ሠላም እንፈልጋለን:: የሠላም እጦት መላውን ኢትዮጵያዊ አንገሽግሾታል:: በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ጽንፍ በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ የማህበረሰብ ክፍል እየተማረረ ነው:: ይህ ጉዳይ አሁን ላይ በቃ ካልተባለ መቼም ሊያበቃ አይችልም” ነው ያሉት::

ከዚህ አንጻር በየትኛውም ደረጃ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በእነርሱ እምነት ኢትዮጵያን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብለው የሚያምኑበትን የሠላም አቅድና አማራጭ ይዘው ቢቀርቡ ሊታይ የሚችልበት እድል እንዳለም ጠቁመዋል:: ሁሉም የሰላም አቅድ እንዲያመጣም ጥሪ አቅርበዋል::

በየትኛውም ሁኔታ ሠላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር ተያይዞ በገለጹት ሀሳባቸው፤ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ኢትዮጵያ እንደ አገር እዚህ እንድትደርስ ጉልህ አበርክቶ ያለው ህዝብ መሆኑን አንስተዋል::፡ ይህ ጉልህ አበርክቶአቸውን እንዲቀጥል፤ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ እና ምቹ ሁኔታዎቹ ምን መምሰል አለባቸው ? አፈጻጸማቸው እንዴት ነው? የሚሆነው የሚለው ቀጣይነት ያላቸው ንግግሮችና ምክክሮችን እንደሚፈለግ ገልጸዋል::

“የምክር ቤት አባል ስሆን የትግራይ ህዝብ ሁኔታም ይገደኛል:: የትግራይንም ህዝብ ወክዬ ነው እዚህ ያለሁት:: እዚህ ስሆን ለመላው ኢትዮጵውያን እንደራሴ ነኝ:: ትግራይም ሠላም እንድታገኝ እፈልጋለሁ:: የሽብር ቡድኑ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተጎዱ አካባቢዎች በተለይ አፋርና አማራ አካባቢዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያ ሠላም እንድታገኝ እፈልጋለሁ:: ያ ሠላም እንዴት መምጣት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ እንደ ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት መወያየትና መመካከር ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል::

የትግራይ ህዝብ ህመም የሁላችንም ህመም መሆን ካልቻለ ኢትዮጵያን እንወዳለን ማለት አንችልም ያሉት አቶ ክርስቲያን ፤ይህን ጉዳይ ሁሉም ማህበረሰብና ፖለቲከኞች ሊረዱት ይገባል ብለዋል ::

አቶ ክርስቲያን፤ እንደ ህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባልነት ሳይሆን “የግል እምነቴ ነው” ብለው ባነሱት ሀሳብ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው ብለዋል:: ኢትዮጵያን አልፈልግም የሚልን አካል ኢትዮጵያን ወደ ፊት እንዴት እናሻግራት በሚል ድርድርና ምክክር ወይም ውይይት ውስጥ ይካተት የሚል አቋም የለኝም ነው ያሉት:: ምክንያቱም ጉዳዩ የኢትዮጵያውያን ስለሆነ ነው ሲሉም የገለጹት::

በተለይም አሸባሪው ህወሓት በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ድረስ እገባለሁ የሚሉ አመራሮች ያሉበት እንደመሆኑ፤ “ መርዝ ቀማሚዎችን ባለ መድኃኒት አድርጎ መቀበል ስህተት ውስጥ እንዳይከተን ጥንቃቄ ማድረግ መቻል አለብን” ብለዋል::

ምንጭ:-ኢፕድ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ሌ/ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

Next Story

በእስር የሚንገላታው ባልደራስ የአደረጃጀት ሥራውን በአዲስ መልክ አጠናክሯል!

Go toTop