የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንንና ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ይግባኝ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. ተቀጥሮ ቢሆንም ውሳኔው ለአራተኛ ጊዜ ተላለፈ፡፡
በተለይ የክሱን ሂደት ከሚከታተሉት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ መካከል የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ከችሎት ውጭ ከጠዋቱ 3፡40 ሰዓት የተከሳሽ ጠበቆችን 6 ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ህንፃ ቢሮ ቁጥር 9 በመጥራት ጠበቆችን “ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ወንጀል ነፃ ናቸውና በነፃ ሊለቀቁ ይገባል የሚል ክርክር ስላነሳችሁ ውሳኔውን ለመስጠት ክሱን በደንብ እየመረመርነው ስለሆነ” በሚል ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
የመሐል ዳኛው ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ እስኪሰጡ ድረስ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ከቀጠሮው በኋላ ግን አቃቂ ቃሊቲ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም እና አቶ ምትኩ ዳምጤን የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ይዘዋቸው ቢቀርቡም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮውን ችሎት ሳይገቡ በመስማታቸው ተመልሰዋል፡፡
ይህ በእዲህ እንዳለ ቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር አልቀረቡም፡፡ ይሁን እንጂ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ባደረገችው ማጣራት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮው የተሰጠውና እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌ ያልተገኙት የቃሊቲው ወህኒ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ ሰርጀንት ዘውድነሽ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ ለመጋቢት 18 ቀን 2005ዓ.ም. እንዲቀርቡ የተሰጣቸውን ማዘዣ ወህኒ ቤቱ አስተዳደሮች ማዘዣው አልደረሰንም በሚል ክደው ተከሳሾቹ በቀጠሮዋቸው እንዲቀርቡ ባለመፍቀዳቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡