የኢትዮጵያ አየር መንገድ CNN ያሰራጨዉን ዘገባ እንዲያርም ጠየቀ

October 8, 2021
airline
airline

የኢትዮጵያ አየር መንገድ CNN ቴሌቪዥን ሰሞኑን ባሰራጨው ዘገባ፣ አየር መንገዱን የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ ጋር በማያያዝ ያቀረበውን ያልተጨበጠ ክስ አጥብቆ እንደሚቃወም ገለፀ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የጆ ባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራዩ ግጭት ጦር መሳሪያ አጓጉዟል በማለት CNN ያወጣው ዘገባ« በጣም አሳሰቢ » ማለቱን ዘግቦ ነበር። CNN ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን በረራ ሕግጋትን እንደሚጥስ እና በዓለም ላይ የመንገደኞች አውሮፕላን ደኅንነትን አደጋ ላይ እንደሚጥል አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

አየር መንገዱ፣ በCNN ዘገባ መነሻነት ትናንት ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ ከ IATA ቀደምት አባላት አንዱ እና ለአሥር ዓመታት የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ላለፉት 75 ዓመታት ለአፍሪቃ አህጉር እና ለተቀረውም ዓለም አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ፣ በርካታ ሽልማቶችን ያሸነፈና በሚሰጣቸዉ ሰብአዊ እና የንግድ ተግባራት የተመሰገነ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ መሆኑን ጠቅሷል።

አየር መንገዱ ከአቪዬሽን ጋር ተዛማጅ የሆኑ ብሔራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለምአቀፍ ደንቦችን በሙሉ በጥብቅ የሚያከብር መሆኑንም በመግለጫው አሳዉቋል።

ከዚህም በመነሳት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ CNN የቀረበውን ውንጀላ እንደሚቃወመው ጠቅሶ፣ «አየር መንገዱ በውል እንደሚያውቀው እና ሰነዶቹም እንደሚያሳዩት በየትኛዎቹም የበረራ መስመሮቹ፣ በየትኛውም አውሮፕላኖቹ አንድም የጦር መሣሪያ አላጓጓዘም» ብሏል።

CNN በዘገባው የጠቀሳቸው ደረሰኞች በግልጽ የሚያሳዩት ውንጀላ በቀረበባቸው በረራዎች የተጓጓዙት ዕቃዎች፣ በሰነዱ ላይ እንደተጠቀሰው የ IATA ደረጃን በጠበቀ መሠረት የታሸጉ «ምግብ ነክ ነገሮች» መሆናቸውን፣ ከዚያ ውጪ በዘገባው ላይ የታዩትን ምስሎች አየር መንገዱ አያውቃቸውም ብሏል።

በተጨማሪም መግለጫው፣ «በአየር መንገዳችን በብሔራቸው ምክንያት ከሥራ የታገዱም ሆነ ሥራ እንዲያቆሙ የተደረጉ ሠራተኞች እንደሌሉን ማረጋገጥ እንወዳለን፤ ይህንን ከአየር መንገዱ የሰው ሀብት አስተዳደር ማረጋገጥ ይቻላል»ም ብሎአል።

«ከአቪዬሽን ጋር ተዛማጅ የሆኑ ዓለም አቀፍ ደንቦች እና መስፈርቶችን በሙሉ የሚያከብር እና በሁሉም የሥራ ክንውኖቹ ከየትኛዎቹም የሲቪል አቪዬሽን ደንቦች የማያፈነግጥ መሆኑን፤ አየር መንገዱ፣ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ማጓጓዝ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደማያውቅ ለተሳፋሪዎቹ በሙሉ እና ለሕዝብ ማረጋገጥ እንወዳለን» ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ CNN ዘገባውን እንዲያርም በመግለጫው ጠይቋልም።

DW

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የህወሓት የጦር ጄነራሎች የኮንትሮባንድ እቃዎችን በወታደራዊ መኪኖች ጭነው ይሸጡ እንደነበር ተገለፀ

dese1
Next Story

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አቀረበ

Go toTop