የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ጉዳት ሰሞኑን ግንባር ድረስ ተጉዘው ተመልክተው ተመልሰዋል። ከዚህ ምልከታ በኋላ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂደዋል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ “አሸባሪው ህወሓት በዓለም ላይ ካሉ አሸባሪዎች ሁሉ የተለየ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
አሸባሪው ህወሓት በዓለም ላይ ካሉ አሸባሪዎቹ ሁሉ የተለየ ነው ያሉት ዲያቆን ዳንኤል፤ ልዩ ነው ያሉባቸውን ምክንያቶችንም ዘርዝረው አብራርተዋል።
እንደ ዲያቆን ዳንኤል ማብራሪያ፤ በዓለም ላይ ያሉ አሸባሪዎች የሚረሽኑት ሰዎችን ነው። ህወሓት ግን ሶስት ህይወት ያላቸውን ነገሮች እስካሁን ረሽኗል። ሰዎችን ረሽኗል፤ እንስሳትን ረሽኗል፤ እጽዋትንም ረሽኗል። ይሄ በሌላ አገር የአሸባሪ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የህወሓት የአሸባሪነት ታሪክ ነው።
“መቄት ላይ፣ ጭና ላይ ዛፎችን ነው የረሸናቸው፤ ከብቶችን ነው የረሸናቸው፤ ዶሮዎችም አልቀሩት” ያሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ “ይሄ ኅይል ቢፈቀድለትና የኢትዮጵያ ህዝብ አቅም ቢያጣ ምስራቅ አፍሪካን ብሎም አፍሪካን ከማጥፋት የሚቆም አይደለም፤ ዓለም ያልተረዳው አንዱ ነገር እሱን ነው” ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት የሆነ አንድ የተቃዋሚ ቡድን አይደለም፤ በዓለም ላይ መልካም የተባሉ ነገሮችን በሙሉ ከማጥፋት የማይመለስ አካል ነው ሲሉም ነው አሸባሪ ቡድኑን የገለጹት።
“አሸባሪው ቡድን በበጀትና በጊዜ አንድ እንዳንሆን የሰራቸውን ሁሉ ነቅለን መጣል አለብን፤ እየተከታተልን የክፋት ሶንኮፉን መንቀል ይገባናል” ብለዋል ዲያቆን ዳንኤል።
“ኢትዮጵያዊያን፤ የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ ገንብተው፣ መልካም አስተዳደርን አስፍነው፣ ዴሞክራሲን አበልጽገው ማሳየት መቻል አለባቸው” ሲሉም ነው ዲያቆን ዳንኤል የተናገሩት።
በዚሁ መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው፤ “አሸባሪው ህወሓት እሴት ያለው የተረጋጋ ሀገር መፍጠር የሚያስችሉ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ወጣቶችን፣ ምንም የማያውቁ ህጻናትንም ጭምር መጨፍጨፉን በተግባር አይተናል” ብለዋል።
ይሄ በጣም አሳዛኝ የዘር ጭፍጨፋ ተብሎ የሚጠቀስና በጦር ወንጀልም ሊያስጠይቅ የሚችል በጣም ዘግናኝ ጭፍጨፋ ነው ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ የአሸባሪው ቡድንን አገር የማፍረስ እሳቤ በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
“አሸባሪው ህወሓት ላላፉት 27 አመታት የኢትዮጵያዊነት ስረ መሰረትን በመናድ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ነበር፤። ይሄ የጥፋት አስተዳደር ስልቱ ሲፈርስበት ተስፋ በመቁረጥና በመብረክረክ ኢትዮጵያን ወደመናድ ገብቷል። ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያዊነት ስረ መሰረት እንዲገነባ እንዲጠነክር ማድረግ አለብን” ብለዋል ዶ/ር ቢቂላ ።