መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በህገ–ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 448ሺህ 550 የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ዳሽን ቢራ በመጫን መነሻውን ከአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ ያደረገው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-26981 ኢት.ተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪ አዲስ አበባ ከተማ ከደረሰ በኋላ ወደ ሀረር ከተማ በማቅናት ላይ እያለ ዛሬ ቃሊቲ ኬላ ላይ በተደረገበት ፍተሻ አሽከርካሪው በህገ–ወጥ መንገድ ሲያጓጉዘው ከነበረ አራት መቶ አርባ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ የአሜሪካ ዶላር ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።
በህገ–ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ዶላር በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ አሽከርካሪው ዶላሩን በቢራ ሳጥን ውስጥ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞክር
በኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው አሽከርካሪ ከነ ዶላሩ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተላልፎ ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑም ታውቋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ቀድሞ በዘረጋቸው ኔትዎርኮች በንግድ ተቋማት የሚሰበሰብ ዶላርን በሀገ–ወጥ መንገድ በውድ ዋጋ እየገዛ ከሀገር እንዲወጣ እና በሀገር ውስጥ የዶላር እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አንዱና ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ነው የተገለጸው።
አሸባሪው ከዚህ የሚያገኘውን ገቢ ለሽብር ተግባር መፈፀሚያ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግለው ሲሰራ መቆየቱን ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት መግለጹን አስታውሷል።
ይህንን ለመከላከል ፖሊስ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ኦፕሬሽን በጥቁር ገበያ ላይ የሚንቀሳቀሰው ህገ–ወጥ የዶላር ምንዛሪ እየቀነሰ መምጣቱን አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጣቸውንም ነው የተገለጸው።
በአሸባሪው የህወሃት ቡድን አባልነት የሚጠረጠሩ አንዳንድ ግለሰቦች አሁንም ከድርጊታቸው ያልተቆጠቡ መሆኑን በተደረገው ክትትል መረጋገጡን የገለጸው ፖሊስ፤ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳሰቅ የነበረው ዶላር በቃሊቲ ኬላ የተያዘው በህብረተሰቡ ትብብር መሆኑንም አስታውቋል።
ኮሚሽኑ መረጃውን ላደረሱ ግለሰቦች ምስጋና በማቅረብ፤ በቀጣይም ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ከህግ አስከባሪዎች ጎን በመሰለፍ፣ ጥቆማ በመስጠትና መሰል ህገ–ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት