የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መንግስት የሃሳብ ነጻነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያድግ የፖለቲካ ምህዳሩን ቢያሰፋም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ፈር እየለቀቁ እንደመጡ መመልከቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም እንዳሉት፥ ተቋሙ በሁሉም ዘርፍ የሚዲያ ነጻነት እንዲረጋገጥና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ለማገዝ ኢ ፍትሀዊ ሀሳቦች ሲተላለፉ በተለያየ መንገድ ለመፍታት እየጣረ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራትም ለ49 የመገናኛ ብዙሃን ግብረ መልስ መሰጠቱን ጠቅሰው፥ ለአራት መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በስልክና በደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ብለዋል።
በሂደቱ የተወሰኑ ለውጦች ቢታዩም ከህገ መንግስቱም ሆነ ከብሮድካስት ባለስልጣን አዋጅ ተጻራሪ በሆነ መንገድ የሚጓዙ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም አንስተዋል።
አያይዘውም ባለስልጣኑ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮሩ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መገናኛ ብዙሃንን እንደማይታገስ አስረድተዋል።
ከዚህ አንጻርም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ቁርሾ የሚፈጥሩ ሃሳቦችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ በአዋጁ መሰረት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምርም ተናግረዋል።
ትናንት በኦ ኤም ኤን የህዝቦችን አንድነት የሚሸረሽርና ቁርሾን የሚፈጥር መልዕክት ሙሉ ተንቀሳቃሽ ምስል ባለስልጣኑ እንደደረሰውም ገልጸዋል።
አሁን ላይ መልዕክቱ በባለሙያዎችና አመራሮች እየተገመገመ ሲሆን፥ በአጭር ጊዜ መረጃውን በማጥራት ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም አውስተዋል።
በማጣራት ሂደት ውስጥ የሚገኙ ውጤቶች የሚያስጠይቁ ሆነው ከተገኙም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ምንጭ፡- ኤፍቢሲ