ህወሀት ዘንድሮን የፍልሚያ ዘመን ሲል አውጇል – መሳይ መኮነን

October 17, 2019

እሳትና ጭድ አይዋሃድም ባለው በሰሞኑ መግለጫው ለትግራይ ህዝብ ብርቱ ትግል የሚገጥምበት ዓመት መሆኑን በመጥቀስ ወገቡን ጠበቅ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። በቁም እስር የሚገኙት የህወሀት አዛውንቶች በእስተርጅና በረሃን መናፈቅ ጀምረዋል። ውስኪ ሲጨልጥና ጮማ ሲቆርጥ የሰነበተው የህወሀት አመራር በምን ወኔና ሀሞት ከደደቢት ዳግም እንደሚገባ የሚያውቁት እነዚያ በእድሜ መግፋትና በተለያዩ በሽታዎች ሞትን በቅርበት እያሸተቱ የሚገኙት አዛውንት መሪዎቹ ብቻ ናቸው። ከ42ዓመት በፊት ወደ በረሃ የገቡበት ዓላማ እነሱን ቱጃር፡ የትግራይን ህዝብ ግን እዚያው በድህነቱ የሚማቅቅ ከማድረግ ሳያልፍ ዘንድሮም የክተት ጥሪ አዋጅ መለፈፋቸው አጥፍቶ የመጥፋት ክፉ መንፈስ እያሰቃያቸው ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው።

የሰሞኑ መግለጫ የቁም ኑዛዜ ነው። ህወሀት በህይወት እያለ ተስካሩን የበላበት መግለጫ ነው ማለትም ይቻላል። ከመቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የሚፎክረው ህወሀት የትግራይን ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር ደም ለማቃባት ቋምጧል። ውሳኔው በትግራይ ህዝብ እጅ ላይ ነው። በእርግጥም ዘንድሮ የሞት ሽረት ይሆናል። ህወሀት በለውጡ መሪዎች ያገኘውን ቶምቦላ ሳይጠቀምበት፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅር ባይነት ረግጦ ለዳግም ዕልቂት ጥሪ ባደረገበት አዋጅ የራሱን ሞቱን ጨልጦ በታሪክ ውስጥ ከጥቁርና አዳፋ ስብዕናው ጋር ፋይሉ ተዘግቶ የሚሰናበትበት ዘመን እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ህወሀትና ጽንፈኛ ብሄርተኞች ዘንድሮን መሻገራቸው አሳስቦአቸዋል። ከጫፍ የደረሰውና እውን ሊሆን አጭር ጊዜ የቀረው ውህድ ፓርቲ ገና በዋዜማው ጽንፈኞችን ጸጉር አስነጭቷል። ብሄርተኝነት ጥቃት እየተፈጸመበት ነው ከሚለው እሮሮ ጀምሮ የሰነበቱበትን የቀውስ ማቀጣጠል ተግባራትን በእጥፍ ለመጨመር እጃቸውን እያሟሟቁ ነው። አስገራሚው ነገር ህወሀት ወደ መቃብር እያዘገመም እድለኛ ነው። ቀውስ በመፍጠርም ሆነ በፕሮፖጋንዳው በኩል የሚያግዘው አላጣም። በአንድም ይሁን በሌላ ዓላማውን የሚስማሙና የሚደግፉ፡ ባይነጋገሩም ስለአንድ ግብ የሚሰሩ፡ ሃይሎች ለህወሀት ምርኩዝ ሆነውለታል። እያነከሰም ለጥቂት ጊዜያት በህይወት እንዲቆይ እየረዱት ነው። ልሶ የሚነሳውን አፈር የሚያመርቱ ጽንፈኞችና የጥላቻ ማለያ ያጠለቁ አክቲቪስትና ጋዜጠኞች በጎራ መደበባለቅ ውስጥ አንድ ላይ ተሰልፈዋል።

የሰሞኑ አጀንዳቸው ተመሳሳይ ነው። የዶ/ር አብይን የኖቤል ሽልማት ጥምብ እርኩሱን ማውጣት የህወሀትና የጽንፈኛ ብሄርተኞች/ተንታኞች አንዱ ስትራቴጂ ነው። በዚህ ውስጥ ዶ/ር አብይን ሀገር ሻጭ፡ ለስልጣኑ ሲል ኢትዮጵያን ለገበያ ያቀረበ ከሃዲ፡ የምዕራቡ ዓለም አሻንጉሊት፡ የአረቦች ተላላኪ የሚሉ መገለጫዎች የቃላት ልዩነት በሌለው መልኩ በህወሀት ሚዲያዎችና በጽንፈኞቹ/ተንታኞቹ መድረኮች ላይ በብዛት የሚደመጡ የሰሞኑ መልዕክቶች ሆነዋል። የዚህ ጥምረት የመጨረሻ ግቡ ዶ/ር አብይ ከስልጣን እንዲለቁ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እንደሆነ በተለይ በዚህ ሳምንት ውስጥ በገሃድ እየተጠየቀ ነው።

ትላንት እሳትና ጭድ የሆኑት ህወሀትና በተቃዋሚነት ተሰልፈው የነበሩ ሃይሎች እጅና ጓንት ሆነዋል። የህወሀት ሚዲያዎች፡ የጽንፈኛ ብሄርተኛና የጥላቻ ተንታኞች የሚጠቀሙባቸው መድረኮች የባህሪ መወራረስ፡ የዓላማ መመሳሰል፡ የስትራቴጂ መደበላለቅ እየተንጸባረቀባቸው ነው። የህወሀት ቴሊቪዥኖች፡ ራዲዮ ጣቢያዎች፡ የህትመት ውጤቶች፡ የኦንላይን መድረኮች ለጊዜው እፎይታን ያገኙ መስለዋል። ለህወሀት ዓላማ መሳካት ሁነኛ የሆኑ፡ እጥፍ ድርብ አድርገው ጸረ አብይ፡ ጸረ ለውጥ ስብከቶችን የሚያዥጎደጉዱ ፡ ጽንፈኛ ብሄርተኞችና በጥላቻ የተነከሩ ተንታኞች የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ስለተፈጠሩ ህወሀቶች ስራ ቀሎላቸዋል። የጊዜው መፈክራቸው ደግሞ አብይ ከስልጣን ይልቀቅ ሆኗል።

በእርግጥም ይህ ዓመት ህወህት እንዳለው የሞት ሽረት ትግል የሚታይበት ይሆናል። ኢትዮጵያ ደሟን እየጠጣ፡ አጥንቷን እየጋጠ፡ ስጋዋን እየበላ ሊጨርሳት ከጫፍ ከደረሰው የጎሳ ፖለቲካ የምትገላገልበት ዘመን እንዲሆን የሚመኙ ወገኖች መንቃትና ሚናቸውን መለየት አለባቸው። ውዥንብሩ አሁን እየጠራ ነው። ማን ከማን ጋር እንደተሰለፈ ፍንትው ብሎ የሚታይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ዶ/ር ምህረት ደበበ እንዳሉት ሀገር ልትፈርስ የምትችለው በአላዋቂዎች ድፍረትና በአዋቂዎች ፍርሃት ነው። አላዋቂዎች፡ ደፋሮች ሆነው አንድ ላይ ተሰልፈዋል። ከቤታቸው የተደበቁ፡ በፍርሃትም ይሁን በአርምሞ ውስጥ የሰመጡ ብዙሃን ኢትዮጵያውያን አደባባይ የሚወጡበት ጊዜው ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ ነው። ምርጫው ግልጽ ነው። በህወሀት ለታጀቡትና የመጨረሻ ግባቸው ኢትዮጵያን ማፈራረስ ለሆኑ ለጀብደኛ ደፋሮች፡ ጽንፈኞች፡ የጥላቻ ሰባኪያን እጅ መስጠት አልያም ኢትዮጵያን ከቅርቃር ውስጥ ለማውጣት ትንቅንቅ ውስጥ ከሚገኘው የለውጥ ሃይል ጋር መሰለፍ። ከእነዚህ ሁለቱ ሌላ ምርጫ የለም።

የሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው። የጀርባ አጥንቱ ተሰብሮ፡ በአንካሴ እግሩ መቀሌ ላይ ቆሞ የእልቂት ጥሪ የሚያስተጋባው ህወሀት ቤተመንግስት የመግባት እድሉ ፈጽሞ የጠበበ ነው። ማድረግ የሚችለው እነዚህ ጽንፈኛ ብሄርተኞችና ጥላቻ አራጋቢ ተንታኞችን ከፊት አስቀድሞ የኢትዮጵያን ስቃይና ምጥ ማራዘም ብቻ ነው። ይህን ደግሞ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በስፋት ያደርገዋል። በኑዛዜ መግለጫው ላይም አጽኦንት በመስጠት ከጎኔ ተሰለፉ ሲል ተማጽኗል። በሌላ በኩል የለውጥ ሃይሉ ከመጋረጃው በስተጀርባ፡ በዝግታ አካሄድ፡ ድምጹን አጥፍቶ ጽንፈኝነት ድባቅ እየመታ ነው። የህወሀትን የጥፋት እግሮች እየተከታተለ በመቁረጥ ላይ መሆኑን እያየን ነው። አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ካልሆነ በቀር የለውጥ ሃይሉ ኢትዮጵያን ለማዳን ግልጽና ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። ፈተናው ቢበዛም፡ ማዕበሉና ወጀቡ ቢጠነክርም እየተንገዳገደና እየተወዛወዘም ቢሆን የጀመረውን መንገድ አለቀቀም። በእነዚህ ቀጣይ ሁለት ወራት የለውጥ ሃይሉ የቤት ስራውን በማጠናቀቅ አንዳች ውጤት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ፈጣሪ እግዚያብሄር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

Previous Story

የአማራ ክልል ደኅንነትና የጸጥታ ካውንስል የጋራ መግለጫና ውሳኔዎች – የአማራ ብሔራዊ ክልል የደኅንነትና የፀጥታ ካውንስል

Next Story

ለመሆኑ ምን ዓይነት ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ያለን?

Go toTop