የቤተመንግስቱ እድሳት ስራ ተጠናቆ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓም ለጉብኝት ክፍት እንደሚሆንና ቅድሚ ጉብኝቱም ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት መሰጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አስታወቁ።
ለጉብኝቱ በወጣው መርሀ ግብር መሰረትም ሀሙስ መስከረም 29 እና አርብ መስከረም 30 ጠዋት ከመቶ አለቃ በታች የሆኑት የሀገር መከላከያ የሰራዊት አባላት እንዲጎበኙት ይደረጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሰአት ከመቶ አለቃ በታች የሆኑት የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
“ይህ የሚሆንበት ዋንኛው አላማ ሰላም ማስጠበቅ ከቻሉ ሀገራችን ባጭር ግዜ ወደ ብልፅግና የምትሸጋገር መሆኑን አምነው ተቀብለው ስራቸውን በስርአት እንዲሰሩ ለማድረግ ስለሚያስችል ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በማግስቱ ቅዳሜ ጠዋት ታላላቆችን ማክበር ኢትዮጵያዊ ባህል በመሆኑ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ጋር በመተባበር እድሜያቸው ከስልሳ አመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች የቤተመንግስቱን ፕሮጀክት እንዲጎበኙ ይደረጋል። ከሰአት ከመስተዳደሩ ጋር በመተባበር የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚጎበኙ ይሆናል።
ከፍለው ማየት የማይችሉትን አስቀድሞ በማስጎብኘት ኢትዮጵያ ለሀብታሙም ለደሀውም ለትልቁም ለትንሹም ለሁሉም ብሄር እኩል ማገልገል የምትችል የሁላችን እናት መሆኗን ከምንናገረውም በላይ የምናሳይበት ምልክት ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እሁድ እለት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር በመተባበር እንዲጎበኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
( ኢፕድ )