በአገራችን ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ብሎም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለመረጋጋት እንዲኖር በደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ እና በፌዴራል መንግስት እየተካሄደ ያለውን የተዛባና ኢፍትሐዊ አሰራር ድርጅታችን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረትን በእጅጉ ስላሳሰበው ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ለማውጣት ተገዷል::
እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በአፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት ሥር ወድቃ ህዝቧ ለከፋ እንግልትና ሥቃይ በመዳረጋቸው መላው ሕዝብ ባደረገው መራር ትግል ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የተወሰኑ የለውጥ እርምቶች መጅመራቸው አብዛኛውን የአገራችን ሕዝቦች ያስደሰተና ተስፋ የጫረ ሆኖ ያለፈ ቢሆንም፤ ብዙም ሳይዘገይ ወደ ወጣንበት አስፊ ሁኔታዎች እየገባን እንገኛለን።
በዋናነት የለውጥ አቀንቃኝ ነን በሚሉ ከአሮጌው አፋኝና ጨቋኝ ኢህአዴግ አብራክ የተወለዱ ሃይሎች እየተከተሉት ባለው አግላይ፤ ለሰላማዊ እንቅስቃሴዎችና ጥያቄዎች ሳይሆን ለሁከት ፈጣን ምላሽ በሚሰጥና ሚዛኑን በሳተ የአመራር ፍልስፍና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ከድጡ ወደ ማጡ ተገፍቶ በመግባት ላይ ይገኛል።
መላው አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችንን በማሰለፍ እንደ ድርጅት ከተቋቋምንበት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተረጋጋና በሳል በሆነ ሥልት ህዝቡ የተነፈጋቸውን መብቶችና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ትግልና ጥረት ሥናደርግ ቆይተናል። በመሆኑም መላው ህዝባችን በየደረጃው ከሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች መካከል።
1: ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለራሱ አገዛዝና ብዝበዛ እንዲመቸው ከዚህ ቀደም በደርግ አገዛዝ ዘመን የካፋ አስተዳደር ይባል የነበረውን አስተዳደራዊ መዋቅር በማፍረስ ከ1500 ኪሜ በላይ በመጓዝ ሲዳማ ዞን ሀዋሳ እንዲተዳደር መደረጉ ከህገመንግስታዊ መብት አኳያ አግባብ ባለመሆኑ በአስቸኳይ ልታረም ይገባዋል በማለት ከ1985 ዓ. ም. ጀምሮ በየደረጃው አበቱታና ቅሬታ እያቀረበ መሆኑ
2: በጥቂት የህወሃት ባለስልጣናትና ጀሌዎቻቸው የተዘረፈው የአካባቢው የልማት ድርጅቶች ማለትም ቴፒ በበቃ ውሽውሽ ቡናና ሻይ ተክሎች ለህዝቡ እንዲመለሱ
3: በኢንቨስትመንት ሥም እየተካሄደ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ዝርፊያና ውድመት በአስቸኳይ እንዲቆም መጠየቁ
4: የመሰረተ ልማት መስፋፋትን በተመለከተ አካባቢው ለሃገራችን የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት የሆነው ቡና ሻይ ወርቅ ቅመማ ቅመም ማር ፍራፍሬ የተለያዮ የእርሻ ምርቶች በስፋት የሚመረት ቢሆንም እንደሌሎች አካባቢዎች ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠውና ያልለማ በመሆኑ ሚዛናዊና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚሉና ሌሎችም በርካታ አንገቢጋቢ ጥያቄዎች ሲቀርቡ እንደነበር የማያሻማ ሃቅ ሆኖ ሳለ ደኢህዴን እና የፌደራል መንግስት ግን እነዚህን ሥር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በማፈንና ወደጎን በመተው በምላሹ የተባባሰ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ እና አፈና ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ስለሆነም ድርጅታችን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት ደኢህዴንና የፌደራል መንግስት በሚከተሉት አንኳር ጉዳዮች ላይ አፋጣኝና መፍትሄ አዘል ምላሽ እንዲሰጥ በጥብቅ ያሳስባል።
ሀ) ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ እና ፍፁም ሰላማዊና ለሎችም አካባቢ ህዝቦች በመልካም ምሳሌነት ሊጠቀስ በሚችል አግባብ የመብት ጥያቄን እያቀረበ ያለውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ሃይልን እንደ አማራጭ በመጠቀም የመብት ይከበርልኝ ወይም ክልል ይገባኛል ከሚሉ ዞኖችና አካባቢዎች እኩል በማየት አካባቢውን በኮማንድ ፖስት ወታደራዊ ሃይል ሥር እንዲወድቅ ማድረጉ ህገ መንግስቱን በፍፁም የሚፃረርና የዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ በአስቸኳይ እርምት እንዲደረግና ለህዝቡ ጥያቄ አግባቢነት ያለው ምላሽ እንዲሰጥ።
ለ, የካፋ አስተዳደር አካባቢ ፈርሶ መዋቅሩ እንዲጨፈለቅ ከተደረገበት ማግስት ጀምሮ ህዝቡ በተከታታይ በሰላማዊ መንገድ ያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎን ምንም እንኳን ዘግይቶም ቢሆን በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች እራስን በራስ የማስተዳደር ይገባኛል ጥያቄን በሙሉ ድምፅ አጽድቀው ለደኢህዴን እና ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረቡ ሲሆን አሁን ያለው አመራርና አገዛዝ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ካለው ጥላቻና ንቀት እንዲሁም የተዛባ አመለካከት የሌሎችን ዞኖች ብቻ ለማጽደቅ በመሯሯጥ ላይ መሆኑ በእጅጉ የሚወገዝና የሚኮነን አሠራር በመሆኑ የምክር ቤቶቹ ድምጽ ሊከበር እንደሚገባው ድርጅታችን በአጽንኦት ይገልጻል::
5: በየደረጃው የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ከህዝብ ጥቅምና መብት ትይዩ ለምን ቆማችሁ በማለት የሚደረግ የግምገማ እና የስብሰባ ጋጋታ እንዲሁም ማዋከብ እንዲቆም።
6: የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ላለፉት አንድ ዓመት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች ሲፈናቀሉ እና የኢህአዴግ አመራሮች በጫሩት ግጭት በርካታ ሰዎች ሲገደሉ ምንም ግድ ያልሠጣቸው ነገር ግን ለእነርሱ የሚመቻቸውና ለአፈና አመራራቸው እንደመሣሪያ በሚጠቀሙባቸው ክልሎችና አካባቢዎች በወረዳና በቀበሌ ሣይቀር በየሣምንቱ መመላለስ ምቾት የሚሰጣቸው የለውጥ አመራሮች ነን ባዮች ይህ ኢ-ፍትሃዊና አሠራራቸው በፍጹም የተሳሳተና አግላይ መሆኑን ተረድተው በአካል ወደ ህዝቡ በመውረድ ይቅርታ እንዲጠይቁ ድርጅታችን በጥብቅ ይጥይቃል።
ስለሆነም ከዚህ በላይ የተገለጹት ችግሮች ቅዲሚያና ትኩረት የሚሠጣቸው ቢሆንም ከህዝቡ ህልውናና የመኖር ዋስትና ጋር በእጅጉ የሚገናኙ በርካታ ጥያቄዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም ወቅትና ግዜያቸውን ጠብቀው የሚንፀባረቁ መሆኑን እየጠቆምን ደኢህዴንና የፌደራል መንግስት እየተከተሉት ያለው የግጭትና የብጥብጥ ማንፌስቶ በፍጹም የማያዋጣውና ይልቁንም ሃገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስና ብጥብጥ የሚያመራ መሆኑን በቅንነት በመረዳት ከተሣሣተ አካሄዱ እንዲመለስ እንጥይቃለን።
መላው የድርጅታችን አባላትና ህዝባችን በተለመደው የጨዋነት ባህልና በተባበረ አኳኋን የጀመርነውን ሰላማዊና መራር ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልና ምሁራንና በተለይም በኢህአዴግ መዋቅር ሥር የምትገኙ ካድሬዎችና አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የህዝባችንን ህመም እየታመማችሁ ለተሻለ ትግል ራሳችሁን እንዲታዘጋጁ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት (ደምኢህህ) ጥሪውን ያቀርባል።
ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው የጨዋነትና የሠላማዊነት እሴታችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የክልል ጥያቄ ለእኛ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና የሰብዐዊና የህገ መንግስታዊ መብታችንን የመጠቀም ጉዳይ ነው፡
ትግላችን መራሪና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም በድል እንደምናጠናቅቅ ባለሙሉ ተስፋ ነን::
ሐምሌ 2011 ደምኢሕህ