የፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ዘጋቢዎቹ ዴቪድ ፒሊንግ እና ሊዮኔል ባርበር በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮንና ቤተመንግስቱን እንደጎበኙ በዛሬ ዘገባቸው ጠቅሰዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=9K1EwuewSOA
በ40 ሺህ ሄክታር ላይ ባረፈው በዚህ ቤተመንግስት ከውጭ ጋዜጠኞች ጋር ዶ/ር አብይ አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ ለአንድ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ በቃለምልልሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በተረከቡ የመጀመሪያው ቀን ፅህፈት ቤታቸው እንዲታደስ ትእዛዝ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሰረትም በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ጨለማ የነበረውን ውስጣዊ ዲዛይን በነጭና ብርሃናማ ቀለም ቀይረው ወደዘመናዊነት መለወጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህን ያደረጉትም ፅህፈት ቤቱን ወደፊትን የሚያሳይ ለማድረግ አስበው እንደሆነ ገልፀውም ‹‹በርካታ ኢትዮጵያዊያን ትላንትን ያያሉ፡፡ እኔ ግን ነገን ነው የማየው›› ብለዋል፡፡ ቤተመንግስቱንም ወደገነትነት የመቀየር ውጥን እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያን ታሪክ የሚገልፅ ዲጂታል ሙዚየም እየገነቡ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትንሹዋ ኢትዮጵያ ተመስሎ የሚሰራው ይህ ፓርክና የእንስሳ መኖሪያ 250 እንስሳት እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከበርካታ መሪዎች ጋር ሲነፃፀር ትላልቅ ነገሮችን ሰርቻለሁ›› ያሉት ዶ/ር አብይ እስካሁን የሰሯቸው ግን ከሚያልሙት ውስጥ አንድ ፐርሰንት እንደማይሞላ ለጋዜጠኞቹ ገልፀዋል፡፡
ሀይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ የተደረገው ስብሰባ ሁለት ቀናት የፈጀና የሞቀ ክርክር የተደረገበት እንደነበር ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህወሀቶች ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም ለመመረጥ መቻላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ ‹‹እነሱ እኔን ማጥቃት ሲጀምሩ እንደማሸንፍ ተረዳሁ፡፡ የእነሱን ተቃውሞ ችላ ብዬም የሹመት ንግግሬን መፃፍ ጀመርኩ›› ብለዋል፡፡
ከተመረጡ በኋላ ቅሬታቸውን ለመግለፅ ፅህፈት ቤታቸው ድረስ በመጡ ወታደሮች የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው የተናገሩት ዶ/ር አብይ ስለሁኔታው ሲያወሱ ደግሞ ‹‹ወታደር መሆኔን አሳይቻቸዋለሁ፡፡ አንድ መጥፎ ነገር ቢፈጠር ከእናንተ ውስጥ አምስትና ስድስቱን ከመግደሌ በፊት አትገድሉኝም ብያቸው ነበር›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ቃለምልልስ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠረ ያለው ግጭት ከህገ መንግስቱ የመነጨ እንደሆነ ተናግረው ህገ መንግስቱን የመቀየር ሀሳብ እንደሚደግፉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ የተጨበጠ ለውጥ ማምጣት የሚቻለውም በሚቀጥለው አመት በሚደረገው ምርጫ ህዝባዊ ድጋፍ ካገኙ በኋላ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር አብይ አሁን ያለውን የምርጫ ስርአት መሪዎች በቀጥታ ወደሚመረጡበት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ስርአት መቀየር እንደሚፈልጉም አስረድተዋል፡፡ ስለትግራይ ክልል በተጠየቁበት ወቅት ደግሞ ‹‹ትላንት በመቀሌ አደባባዮች ሲሰድቡኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ወድጄዋለሁ፡፡ ዲሞክራሲ ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ህዝቡ ካልፈለጋቸው በደስታ ስልጣን እንደሚለቁ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ‹‹እዚህ ረጅም ጊዜ እንደማልቆይ እርግጠኛ ነኝ፡፡ መቼ እንደሆነ ባላውቀውም ከዚህ ወንበር መልቀቄ አይቀርም›› ብለዋል፡፡