በለገጣፎ የሚገኘው ካንትሪ ክለብ ዲቨሎፐርስ ወይም በተለምዶ ሲሲዲ ተብሎ የሚጠራው የቅንጦት መኖሪያ መንደር ባለቤት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ታዟል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=epx_GOJUaUQ
የመንደሩ ባለቤት ዶ/ር መሰለ ሀይሌ የተከሰሱት በቤት ገዢዎ ነው፡፡ ስድስት ያህል ገዢዎች በመንደሩ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት ለመግዛት ገንዘብ ከፍለው 10 አመት ቢጠብቁም ቤቱን ሊረከቡ ስላልቻሉ ወደ ክስ ማምራታቸውን ካፒታል የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ከሳሾቹ ከዚህ ቀደም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ተፈርዶላቸው ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ኩባንያው በ16 ወራት ውስጥ ቤቱን ሰርቶ እንዲያስረክብ ታዞ እንደነበር ያወሳው ጋዜጣው ኩባንያው ግን በጊዜ ገደቡ ማስረከብ አልቻለም ብሏል፡፡ ይህ የጊዜ ገደብ ካለቀ በኋላ የአራት ወር ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ቢጠብቁም ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ አራት ወር አልቆ አምስተኛ ወር በመግባቱ ከሳሾቹ አቤት ለማለት ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ወደ ፍርድ ቤት አምርተዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የኩባንያው ባለቤት ዶ/ር መሰለ ችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከሳሾቹ ከ10 አመት በፊት ቤቶቹን ለመግዛት የከፈሉት ከ1 ነጥብ 7 እስከ 3 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህን መኖሪያ መንደር ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ዶ/ር አብይ ማስጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡