ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ለ35 ዓመታት በሰራዊቱ ውስጥ የሠሩትና የምስራቅ እዝ አዛዥ የነበሩት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ከአዜብ መስፍን ጋር በጫት ንግድ ተሰማርተዋል መባሉን ‹‹ውሸት ነው›› አሉ፡፡ ዛሬ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለምልልስ የሰጡት ጄኔራሉ ይህን በተመለከተ ሲናገሩ ‹‹ከአዜብ ጋር ጫት ይሸጣል የተባለው ነገር ፈጸሞ ውሸት ነው፡፡ ሀረር የሰራሁት ለ13 ዓመታት ነው፡፡ ለአዜብ ጫት ካልሸጣቸሁ ብሎ የሀረርጌን አርሶ አደሮች ፈጃቸው ነው ያለው፤ ስለዚህ ይህን ባደርግ ኖሮ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረብ አለብኝ፡፡ ሁለተኛ፤ ከተጠቀሰችው ሴት ጋር አይደለም ጫት ልነግድ ከርሷ ጋር ሁለት ቀን ብቻ ነው ተገናኝተን ያወራነው፤ ጫትም አብሬ አልነገድኩም፡፡ ፈጸሞ ውሸት ነው፡፡ ያኔ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኜ አይደለም አሁን እንኳን ጫት አልነግድም፡፡ ይህን ስልህ ግን የሰራዊት አባል ሆነው የነገዱ የሉም ማለት አይደለም፡፡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ጫት አልነገድኩም፡፡›› ብለዋል፡፡
ተስፋዬ ገብረአብ በተደጋጋሚ በመፅሀፉ የጠቀሳቸው ጄ/ል ባጫ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁ በዚህ ቃለምልልስ የገለፁ ሲሆን ስለእሳቸው የፃፈው ሀሰት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹እርግጥ ነው ተስፋዬ ጥሩ ጸሀፊ ነው፡፡ እኔም አደንቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን ስለእኔ የጻፋቸው መቶ በመቶ ውሸት ናቸው፡፡›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ጊታር፣ ቤዝ ጊታር፣ ሊድ ጊታር፣ ሳክስፎንና ይጫወቱ እንደነበር የጠቆሙት ጄኔራሉ ድምጻዊ ግን እንዳልነበሩና የሙዚቃ ስራቸውን ከ1978 ዓ.ም በኋላ መተዋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ድምፃዊ እንደነበሩ በተስፋዬ መፅሀፍ የተገለፀውን በተመለከተም ‹‹ወደፊት ከተስፋዬ ጋር ተገናኝተን ቁጭ ብለን እናወራ ይሆናል፡፡ አስመራ ላይ ሆኖ የነገረው ሰው ዛሬ አዲስ አበባ ከእኛ ጋር አለ፡፡ ሰውየው ማን እንደሆነ አንድ ቀን እነግራችኋለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት ከሰራዊቱ የተገለሉት ጄ/ል ባጫ አሁን የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው የግል ስራ እየሰሩ መሆኑን ጋዜጣው አስረድቷል፡፡ ከሰራዊቱ የተገለሉት በማንነታቸው ምክንያት መሆኑን መናገራቸውንም በቃለምልልሱ ተመልክተናል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=rcbWeNfbu_o&t=32s