የአማራ ድምፅ ራዲዮ ዋና አዘጋጅ ደምስ በለጠ ከአገሩ ከወጣ ከ30 አመታት በኋላ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ በገባ በ21 ቀኑ በተኛበት አርፎ ተገኘ::
የጋዜጠኝነት ስራውን ገና ተማሪ እያለ በሞስኮ ራዲዮ የአማርኛ ዝግጂት ክፍል የጀመረው ፤ ደምስ በለጠ ከ2016 አም ጀምሮ የአማራ ድምፅ ራዲዮ ሲያዘጋጅ ነበር። ደምስ ከረጅም ጊዜ የውጪ አገር ቆይታ በኋላ በፈረንጆቹ አቆጣጠር እሁድ ዲሴምበር 2 ቀን ኢትዮጵያ ገብቶ ነበር።
ከዛሬ 30 አመት በፊት ፤ ለትምህርት ወደ ሩሲያ ተልኮ ፤ ትምህርት ላይ እያለ በኢትዮጵያ የመንግስት ለወጥ በመደረጉ ፤ ይማርበት ከነበረበት አገር ከሩሲያ ወደ አሜሪካም ተሰድዶ ፤ ከትምህርት ዘመን በኋላ ያለውን ጊዜውን በሰሜን አሜሪካ አሳልፏል።
ደምስ በለጠ በአሜሪካ ስደት ላይ በቆየባቸው ጊዚያት ፤ በተለያዩ የራዲዮ ጣቢያዎች በጋዜጠኝነት ሰርቷል ። በተለይ በታሪካዊው የምርጫ 97 የቅንጅት ጊዜ የመጀመሪያውን “ንጋት” የተባለውን የኢንተርኔት ራዲዮ በመጀመር ፤ በአለም ላይ የተበተነውን ኢትዮጵያዊ በተመሳሳይ ሰአት ላይቭ በቀጥታ ዝግጂቱ ሲያገናኝ እንደነበር እናስታውሳለን::
ደምስ በለጠ በዚህ ብቻ ሳይገታ ፤ ከ2005 አም ጀምሮ እስከ 2012 የአውሮፓውያን ዘመን ድረስ ፤ ወደ ኤርትራ በመመላለስ ፤ በጊዜው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ይባል የነበረው ድርጅት ያደርግ የነበረውን ትግል ሲደግፍ ነበር::
ደምስ በለጠ በተለይ ተቺና አስተማሪ የሆኑ መጣጥፎቹን በተለያዩ ድረገፆች እያወጣ ያስነበበን ሲሆን ፤ በዘሃበሻ የሚወጡ ፅሁፎችንም በተገቢው መንገድ በንባብ በማቅረብ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው የሚለውን መርህ በተግባር ያሳየ ጋዜጠኛ ነበር::
https://www.youtube.com/watch?v=FKORGOIm5_E&feature=youtu.be