ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ከኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ዛሬ ተነጋገሩ፡

December 21, 2018

ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ከኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ዛሬ ተነጋገሩ፡፡ ዶ/ር ወርቅነህ በፌስ ቡክ ገፃቸው ስለዚህ ጉዳይ ሲገልፁ ‹‹የኦሮሞ ጥናትን መሰረት የጣሉ ብቻ ሳይሆን በገዳ ስርዓት ለማጣቀሻ የበቁ አያሌ መፅሀፍቶችን የፃፉ እና ጥናቶችን ያደረጉ የገዳ ስርአት በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ የነበራቸውን ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ዛሬ በፅ/ቤት ተቀብለን አነጋግረናቸዋል።›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ ጨምረውም የገዳ ስርአት አባት ያሉዋቸው ፕ/ር አስመሮም ለኦሮሞ ጥናት ላደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ምስጋና እንዳቀረቡላቸው አስረድተዋል፡፡ ፕሮፌሰር አስምሮም በኤርትራና የኦሮሞ ህዝብ መሀከል ድልድይ መሆናቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለቀጣይ ጥናቶቻቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።

በዚህም ፕሮፌሰር አስምሮም ለገሰ በበኩላቸው ኤርትራዊ ይሁኑ እንጂ ልባቸውና ቀልባቸው ከቦረና ኦሮሞዎች ጋር ሆኖ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የቦረና ህዝብ ባህል መዋሸት፣ መስረቅና መግደልን ነውር ያደረገ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ ህብረተሰቡ ስለገዳ የበለጠ ዕውቀት እንዲኖረው በሌሎች ቋንቋዎች የተፃፉት ስራዎችም መተርጎም ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር አስምሮም የኦሮሞ ጥናትን መሰረት የጣሉ ብቻ ሳይሆን፥ በገዳ ስርዓት ለማጣቀሻ የበቁ አያሌ መፅሀፍቶችን የፃፉና ጥናቶችን ያደረጉ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=s58PBvypjSM

Previous Story

አርበኞች ግንቦት 7 በአዲስ አበባ ዋና ዋና አደባባዮች ቅስቀሳ ሲያደርግ ውሏል

Next Story

ደምስ በለጠ ከአገሩ ከወጣ ከ30 አመታት በኋላ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ በገባ በ21 ቀኑ በተኛበት አርፎ ተገኘ

Go toTop