በተለያየ ጊዜ ተቃውሞው የበረታበት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ስልጣን መልቀቁን አስታወቀ፡፡ ዛሬ በቢሮው መግለጫ የሰጠው ሀይሌ ላለፉት ሁለት አመታት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ሲመራ እንደቆየ ገልፆ፣ በእነዚህ አመታት ውስጥ የተለያዩ ከበድ ያሉ ችግሮችን ከስራ አስፈፃሚው ጋር በመሆን ሲፈታ እንደቆየ አስረድቷል፡፡ ‹‹በተለያዩ ወቅቶች የፌዴሬሽናችንን የአሰራር ችግሮችን አንዳንድ ግለሰቦች ትልልቅ ተቋማትን መከታ አድርገው የፌዴሬሽኑንና የአለም አቀፍ አትሌቲክስ መርሆዎችን ለማስቀልበስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል›› ያለው ሀይሌ ጨምሮም ‹‹ይህም ጥረታቸው በትላንትናው እለት ማለትም ህዳር 2 ቀን 2011 ሲሉልታ ላይ በተደረገው የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ በየትም አለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ላይ የማይፈፀም ድርጊት እንዲፈፀም አድርገዋል፡፡›› ሲል በመግለጫው ተናግሯል፡፡ ድርጊቱ ምንም የማይበጅ ጎጂና አደገኛ ነገር መሆኑን ቀድሞ እንደተረዳ የጠቀሰው ሀይሌ ይሁንና ጉዳዩን በትእግስት እንደጠበቀው፣ ድርጊቱም ከፍተኛ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን አስረድቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ስልጣን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሱንና ስልጣኑን ከዛሬ ህዳር 3 ጀምሮ የእሱ ምክትል ለሆነችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ እንዳስረከበ ተናግሯል፡፡
ሀይሌን ለስልጣን መልቀቅ ያበቃው በትላንትናው እለት የተደረገውን ተቃውሞ በተመለከተ ዘሃበሻ ማጣራት አድርጋ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው 2ተኛው የሱሉልታ አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድር ተቃውሞ ያሰሙት የኦሮሚያ አትሌቶች እንደነበሩ ከምንጮች ለመረዳት ችለናል፡፡ የ8 እና የ12 ኪሎ ሜትር ሩጫንና የዱላ ቅብብልን ባካተተው በዚህ ውድድር አትሌቶቹ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ተቃውሞ እንዳሰሙ የጠቀሱት ምንጮች የመፈክሮቹን አይነትም በፎቶግራች አስደግፈው ልከውልናል፡፡ ትላንት በተቃውሞው ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ አሯሯጭ ሆኖ ወደ ውጭ ሃገር የተላከ አትሌትን ጉዳይ፣ ያሉት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በፍትሃዊነት ስለመጠቀም፣ ፌዴሬሽኑ ብር ባንክ ከዝኖ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ግንባታ ቸል ማለት እንዲሁም ለትጥቅ ብቻ እስከ 23 ሚሊዮን ብር ወጭ እያደረገ በስፖርት ትጥቅ እጦት ከስፖርቱ እየተገለሉ ያሉ ወጣቶችን አይቶ እንዳላዬ ማለፉ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ሰዎች ለጥቅማቸው ሲሉ አንጋፋ አሰልጣኞችን ማግለል ይቁም እና ሌሎችም በመፈክር መልክ ቀርበው ነበር ተብሏል፡፡
በቅርቡ የአለም ሻምፒዮናና የአገር አቋራጭ ውድድሮች የሚከናወኑ ከመሆኑ አኳያ የሀይሌን በዚህ ወቅት ስልጣን መልቀቅ ጊዜውን ያልጠበቀና ‹‹ለአገር ከማሰብ ይልቅ የግል ዝናን በማስቀደም ርካሽ ተወዳጅነት ለማትረፍ የተደረገ ውሳኔ ነው›› ብለዋል አንድ አስተያየት ሰጪ፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=2woW6QIeHHY