የታሰሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የደህንነቶች ቁጥር 126 ደረሰ | ጌታቸው አሰፋ የ እስር ማዘዣ ወጦበታል

November 12, 2018

ባለፉት ሦስት ቀናት ከየአቅጣጫው ታፍሰው ሰለታሰሩት ባለስልጣናት ቁጥር 126 አካባቢ መድረሱ ተገለጸ:: በታሰሩት እና እየተፈለጉ ባሉት የጦር መኮንኖች እና ባለስልጣኖች ዙሪያ በዛሬው ዕለት በቢሯቸው መግለጫ የሰጡት የፌዴታል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ እንደገለጹት እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት በጥቅሉ 126 አካባቢ ናቸው፡፡ ከእነዚህም 63 በሽብር ድርጊት፣ 27 በሙስና፣ 36 ደግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ናቸው። ከነርሱ ጋር አብሮምሊብሬ፣ የአክስዮን ደብተር፣ የቤት ሽያጭ ውሎች፣ ጦር መሳሪያዎች ወዘተ በኤግዚብትነት መያዛቸውን አብራርተዋል::

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በመግለጫቸው አሁን የታሰሩትና የሚፈለጉት ባለስልጣናት ሲፈጽሙ የነበረውን ግፍ አብራርተዋል:: በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አባላት መካከል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስውር እስር ቤት ግለሰቦችን በማሰር እና በማሰቃየት ተጠርጥረው የተያዙ እንዳሉ; አዲስ አበባ ውስጥ 7 ግፍ የሚፈፀምባቸው ድብቅ እስር ቤቶች እንደተገኙ በዚሁ ከተማ ዜጎች ከሰባት ወደማያንሱ ስውር ማሰቃያ ስፍራዎች ‘በአምቡላንስ እየተጓጓዙ!’ ጭምር ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር የገለጹት አቶ ብርሃኑ
በእነዚህ እስር ቤቶች ዉስጥ
“በሰብአዊ መብት ጥሰት ጠጠርጥረው ከተያዙ ግለሰቦች መሀል ግለሰቦችን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ እና ማሰቃየት፣ በአንቡላንስ እያፈኑ ሰዎችን መሰወር፣ ህገወጥ መሳሪያዎችን የራሴ ነው ብሎ እንዲፈርሙ ማድረግ፣ የብልት ቆዳዎችን በፒንሳ መሳብ፣ ጫካ ማሳደር፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ አፍንጫ ውስጥ እስክርቢቶ መክተት፣ ግብረሰዶማዊ ጥቃት መፈፀም፣ ሴቶችን መድፈር የመሳሰሉ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ፈፅመዋል።” ብለዋል::

“ጠላት ሀገር እንኳን በዚህ መልኩ አይዘረፍም!” ሲሉ ሜቴክ በሃገር ላይ የፈጸመውን ዝርፊያ የዘረዘሩት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን በተመለከተ “የውጪ ሀገር ግዥዎችን ያለጨረታ መስጠት፣ ግዥ አፈፃፀሙ ከኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች የድለላ ስራ ሰርተው የሚከፈላቸውና እነዚህ የውጪ ኩባንያዎችን የሚያመጡት ደላሎች በስጋ ዝምድና ለአመራሩ ቅርብ የሆኑ ናቸው። እነዚህ በድለላ ያሉ ሰዎች በሀገር ውስጥ ካካበቱት ሃብት በላይ ወደ ዉጪ ሃብት አሽሸዋል። ከመደበኛው ዋጋ እስከ 400% ተጨማሪ ዋጋ እየተጨመሪ ግዢ ይፈፀም ነበር።” ብለዋል:: አክለውም “የሀገር ውስጥ ግዢም በግልፅ ጨረታ መፈፀም ሲገባው እስካሁን በዚህ መልኩ የተፈፀመ የለም። ከኮርፓሬሽኑ አመራሮች ጋር የዝምድናና የጥቅም ትስስር ካላቸው ሰዎች በብዙ እጥፍ በተጋነነ ዋጋ ይገዛ ነበር። ከአንድ ድርጅት 21 ጊዜ፣ ከሌላው ደግሞ 15 ጊዜ ግዢ ተፈፅሟል። ከአንድ ድርጅት በአንድ ጊዜ ብቻ የ215 ሚሊዮን ብር ግዢ ያለጨረታ ተፈፅሟል።” ብለዋል::

“ከተቋሙ ተልዕኮ ውጪ የተፈፀሙ ግዥዎችም አሉ። ከዚህም ውስጥ የመርከብ ግዢ ይገኝበታል። በማይመለከተውም ስራ ገብቶ ወደ ንግድ ስራ አስገብቷቸዋል።” ያሉት አቶ ብርሃኑ ግዢዎቹ በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት መካከል የተከናወነ ነው ብለውታል::
ሰኔ 16 ዶ/ር አብይ አህመድን ለመግደል በመስቀል አደባባይ ስለፈነዳው ቦምብ እና የማን እጅ እንዳለበትም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሲያብራሩ
“የሰኔ 16 ቱ የቦምብ ጥቃት የተቀናበረው በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሞ ስለሆኑ በኦሮሞ ቢገደሉ ተብሎ ነው በሙከራው ኦሮሞዎች እንዲሳተፉ የተደረገው።” በማለት ትዕዛዙ ከቀድሞው የደህንነት ኃላፊ ቢሮ እንደወጣ ተናግረዋል:: “የቀድሞው የደህንነት ኃላፊ ሲሉ አቶ ተስፋዬ ኡርጌን ይሆን አቶ ጌታቸው አሰፋን እንደሆነ ሲጠየቁ ” የሚል ጥያቄ ሲጠየቁም “የመረጃ ደህንነት ኃላፊው ማን እንደሆኑ እያወቃችሁ አታድርቁኝ ።” ብለዋል::

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ በአጠቃላይ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ የሜቴክና ደህንነት አመራሮች እንዲሁም በሙስና የተያዙት ቁጥር 126 አካባቢ ሲሆን እስካሁንም ያልተያዙ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የተደበቁ መኖራቸውን ጠቁመዋል::

<<አሁንም የምንጠረጥራቸው ነገር ግን በሃገር ውስጥና በውጪ ተሸሽገው ያሉ አሉ። በውጪ ያሉትን መንግስታቶቹ አሳልፈው እንዲሰጡን በመነጋገር ላይ ነን። ሀገር ውስጥ ያሉት ደግሞ ራሳቸውን ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ የፍትህ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ እናቀርባለን>> ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ “ምርመራው ከ5 ወር በላይ ፈጅቷል። የዚህ ምክንያቱም በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን አስረን ከማጣራት አጣርተን ለማሰር ስለሞከርን ነው። ማንንም ተጠርጣሪ ሳንይዝ ነው ያጣራንው።” ብለዋል:: ስለታሰሩት ሰዎች ወንጀል ሲያብራሩም “በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መሀል የተሰጣቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ያለአግባብ ሀብት ያከማቹ፣ ሀብት ያሸሹ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ፣ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከሰቱ ብጥብጦች ያስተባበሩ ይገኙበታል።” ብለዋል::

የዘ-ሐበሻ የፖሊስ ምንጮች አቃቤ ህግ ክስ የሚመሰርተው በሶስት መዝገብ ሊሆን ይችላል:: የሙስናው እስረኞች የክስ መዝገብ ‹‹እነክንፈ ዳኘው›› የሚል ሲሆን የሰብአዊ መብት ጥሰቱ መዝገብ ደግሞ ‹‹እነጌታቸው አሰፋ›› የሚል መዝገብ መሆኑን ከፖሊስ ምንጮች ለመረዳት ችለናል፡፡ በዚህ መሰረት ጌታቸው አሰፋ ላይ የእስር ማዘዣ ተቆርጧል፡፡ ሆኖም ግን የቀድሞው የደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ እስካሁን እንዳልተያዙ የተገለጸ ሲሆን አንዳንድ የሕወሓት አክቲቭስቶች በሶሻል ሚዲያዎች ወደ እስራኤል መሄዱን እየተናገሩ ሲሆን ምናልባትም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ <አሁንም የምንጠረጥራቸው ነገር ግን በሃገር ውስጥና በውጪ ተሸሽገው ያሉ አሉ" ያሉት አቶ ጌታቸውን እና መሰሎቻቸውን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ:: አቶ ብርሃኑ "ወንጀለኛ ቡድንን፣ ሃይማኖትን፣ ብሄርን አይወክልም። ወንጀለኛ ራሱን ወንጀለኛወን ነው የሚወክለው:: የተጠረጠሩ ሰወች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ በተለየ ከሕግ ውጭ ሊያመልጥ የሚችል አንድም ኃይል ሊኖር አይችልም።" ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል:: - አሁን የደረሰን ዜና ላለፉት 3 ቀናት ተለቃቅመው ከታሰሩት የጦር መኮንኖችና የደህንነት ባለስልጣናት መካከል ከ60 በላዩ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ: በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ብርጋዴል ጀኔራል ጠና ጠረዲን ጨምሮከ27 በላይ በሙስና የተጠረጠሩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሰራተኞች እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ አነ ኖሃ አጽባሃን ጨምሮ 36 የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ናቸው፡፡ በሁሉም ላይ ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ትላንት ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ዘግበን ነበር፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=2woW6QIeHHY

Previous Story

የቀድሞው የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ታሠሩ | ቀድሞው የማእከላዊ ምርመራ ምክትል አዛዥ እየታደኑ ነው

Next Story

ሀይሌ ገብረስላሴ ስልጣን ለቀቀ

Go toTop