የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ባህር ሃይል ልታቋቁም መሆኑን አስታወቁ፡፡ ጄኔራሉ ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀደም ሲል ባህር ሀይል የነበረው እንደሆነ ጠቁመው የባህር በር የለንም በሚል አስተሳሰብ እንደፈረሰ አስረድተዋል፡፡ አሁን ግን ዘመናዊና ጠንካራ ጦር ሃይል ለመገንባት እቅድ ስለተያዘ ኢትዮጵያ ባህር ሃይል ያስፈልጋታል ተብሎ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡ የባህር ሃይሉ በቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ የጦር ሰፈር እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ ጠንካራ ባህር ሀይል ኢትዮጵያ እንዲኖራት የወጠነው አገሪቱ ትልቅ አገር ስለሆነች መሆኑን ምክትል አዛዡ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ቃለምልልሳቸው ‹‹የባህር በር ባይኖረንም ለቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ቅርብ የሆንን አገር ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ አገራት በሱማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድና ኤርትራ የባህር ሀይል ጦር ሰፈር የገነቡበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እኛ ከጠረፍ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተቀምጠን የራሳችንን ባህር ሀይል ማስፈር እንችላለን›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ወደቦች በመጠቀም የወጪና ገቢ ንግድ እስካከናወነች ድረስ ባህር ሀይል ማቋቋም እንደማይከብዳት የተናገሩት ጄነኔራሉ በባህር ሀይሉ አቅም፣ መዋቅርና አሰፋፈር ዙሪያ ከሌሎች አገራት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑኑንም ጠቁመዋል፡፡ በቀይ ባህር አካባቢ በርካታ አገራት የባህር ሀይል ጦር ሰፈር እየገነቡ መሆኑን አስረድተውም ካለው ሁኔታ አንፃር ‹‹አያድርገውና ቀጣናዊ ቀውስ ቢፈጠር ባሕር ላይ ምንም ጉልበት ከሌለን እንጎዳለን›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ ቃለ ምልልስ ጄኔራል ብርሃኑ ቤተመንግስት ድረስ ታጥቀው ስለሄዱት ወታደሮች ተጠይቀው ሲመልሱ ‹‹ጥቂት ወታደሮች ሌላው የሠራዊት አባል ምንም መረጃ ሳይኖረው እነርሱ በጠነሰሱት ሴራ ቤተመንግሥቱን ለመበጥበጥና ጦር ሜዳ ለማድረግ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድንም ካገኙ ለመግደል ወጥነው ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ ስለኦነግ አስተያየት ሲሰጡ ደግሞ በኦነግ ውስጥ መከፋፈል እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ኦነግ ውስጥ የተፈጠረ አለመግባባት አለ፡፡ እርስ በራሳቸው ተነጋግረው ችግራቸውን እንዲፈቱ ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ እነርሱም ለመፍታት እየሞከሩ ነው፡፡ አሁን ጦርነትም የለም፡፡ አልፎ አልፎ እንደ ዲስፕሊን ጥሰት የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ትናንሽ ችግሮችን እኛም ድርጅቱም ለመፍታት በጋራ እየሰራን ነው፡፡›› ማለታቸው ታውቋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=nOka95WpYt4