ከዳዊት በጋሻው
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በካላባር ናይጄሪያን ለማሸነፍ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናገሩ ። በአዲስ አበባ 2ለ1 የተሸነፉት ዋሊያዎቹ ውጤቱን ለመቀልበስና በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ የተጠናከረ ልምምድ እያደረጉ ናቸው ። ተጫዋቾቹም በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ይናገራሉ።
የዋሊያዎቹ አምበል ደጉ ደበበ «ጥሩ ሞራል አለን፤ ጥሩ ዝግጅትም እያደረግን እንገኛለን » በማለት ልምምዳቸው በጥሩ መንፈስ እየተካሄደ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው።
«አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ እናደርጋለን ፤ ውጤቱንም የመቀልበስ አቅም አለን » በማለት የገለጸው አምበሉ፣ናይጄሪያን በሜዳው በማሸነፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ እንደሚሆኑም ያለውን ጽኑ ዕምነት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ቡናና የዋሊያዎቹ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በበኩሉ በጣም ጥሩ ልምምድ እየሰሩ እንደሚገኙና ያላቸውም አንድ ዕድል መሆኑን ጠቅሶ፣ በጣም ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው ነው ያስገነዘበው።
«ካላሸነፍን ማለፍ አንችልም ፤ ስለዚህ ለማሸነፍ ጠንክረን እየሰራን ነው» ያለው ጀማል፣ከሌላው ጊዜ የተለየ ልምምድ እያደረጉ እንዳልሆነም ነው ያመለከተው። «የጨዋታውም ልዩነት መጀመሪያ በአገራችን መጫወታችንና አሁን በናይጄሪያ ሜዳ ልንጫወት መሆኑ ላይ ነው » ብሏል ።
ሰው አገር ሄዶ ለማለፍ የግድ ማሸነፍ እንደሚገባም አመልክቶ፣ ያለፈው ሽንፈትም በኳስ ዓለም የሚከሰት እንደሆነ ውጤቱን ለመቀልበስ የሚችሉትን ያህል ሰርተው ህዝቡን እንደሚያስደስቱ ነው ያረጋገጠው።
እንደ አምበሉ ደጉ ደበበና ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው አገላለጽ ፤ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ወደ ብራዚል ለማቅናትና በታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስደሰት ይጥራሉ።
ዋሊያዎቹን በባለፈው የመጀመሪያ ዙር የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ቢሸነፉም ምርጥ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የተመለከተው የደቡብ አፍሪካው የስፖርት መገናኛ ብዙኃን ሱፐር ስፖርት « የአፍሪካ ባርሴሎና» በማለት እንዳወደሳቸው ይታወቃል። የጨዋታው የበላይም እንደነበሩ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የሌጎስና አቡጃ ተመልካቾች በናይጄሪያውያን ተጫዋቾች ላይ እምነት እንደሌላቸው መናገራቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ሲጠቁሙ ሰንብተዋል።
ዋሊያዎቹና አረንጓዴ ንስሮቹ የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ የጥሎ ማለፍ ጨዋታቸውን በደቡባዊ ምስራቅ የናይጄሪያ ከተማ ካላባር ላይ ህዳር ሳባት ያካሂዳሉ።