በ20 ሚሊየን ብር የተገነባው ስታዲየም በሁለት አመቱ ተደረመሰ

October 24, 2013

በደቡብ ኦሞ ጂንካ ከተማ በ2003 ዓ.ም የተሰራ ሁለገብ ስታዲየም መፍረሱ ተሰማ ሲል ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘገበ፡፡ ስታዲየሙ ለ13ኛው የአርብቶ አደር ጉባኤ ወደ ዞኑ ላቀኑት የቀድሞ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ጉብኝት እንዲደርስ ተብሎ የተወጠነ እንደ ነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም የዋለው የአርብቶ አደር ቀን በስታዲየሙ እንዲከበር ለማድረግ ስራው ሙሉ በሙሉ በ20 ቀናት ውስጥ እንደተጠናቀቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከተጠናቀቀበት ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ አመት እንዳገለገለ የዛሬ አመት ገደማ ከክቡር ትሪቡኑ በስተቀኝ የሚገኘው ብሎክ እንደወደቀ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ከተከሰተ ከአመት በኋላ ጥላ ፎቁና ክቡር ትሪቢዩኑ ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ላይ ሙሉ በሙሉ ለመፍረስ ችሏል፡፡
አደጋው ሲከሰት በጥበቃ ላይ የነበሩ ሶስት ፖሊሶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል እንደሚገኙ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት በእለቱ በስታዲየሙ የአውደ ርዕይ ዝግጅት እንደነበርና አደጋው በቀን ገጥሞ ቢሆን ከፍተኛ እልቂት ይከሰት እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ስታዲየሙ ሲሰራ ክቡር ትሪቢዩኑና ጥላ ፎቁ “ይርጋለም ኮንስትራክሽን” በተባለ ተቋራጭ መሰራቱ ታውቋል፡፡ ለስቴዲየሙ ግንባታ 20 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉ ታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የዞኑ የስፖርት ሰብሳቢ አቶ ስጦታው ጋርሾ “በጉዳዩ ላይ አስጠያየት መስጠት አልፈልግም” በሚል ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳር አቶ ሞሎካ ውብነህ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በስልካቸው ያለመስራት ሳይሳካ ቀርቷል ሲል ጋዜጣው ዘገባውን አጠናቋል።

Previous Story

የጌታነህ ትሬዲንግ ባለቤት ራሳቸውን በሽጉጥ ገድለው እንዲሞቱ የተደረገበት ምስጢር ከ4 ዓመት በኋላ ወጣ

Next Story

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አንድን ጳጳስ ከስልጣን አነሳ

Go toTop