የብሔራዊ ቡድናችን ውጤታማ ጉዞ ተገታ

October 13, 2013

http://www.youtube.com/watch?v=ywVIyL7ALg4&feature=youtu.be
(ስፖርት አዲስ) ለብራዚሉ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ለማለፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የመጨረሻ ማጣሪያ መጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋና ደጋፊዋ ፊት ሽንፈትን አስተናገደች፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ አስደናቂና ውጤታማ ጉዟ በናይጄሪያ ተገቷል፡፡
ዛሬ ከቀኑ በ10፡00ሰዓት የተደረገው የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ሦስቱ ግቦች ከዕረፍት መልስ የተገኙ ናቸው፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን ወስዶ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ 56ኛው ደቂቃ ላይ በሃይሉ አሰፋ ከመስመር ለማሻማት የላካት ኳስ አቅጣጫዋን ስታ ግብ ልትሆን ችላለች፡፡ ለናይጄሪያ ሁለቱንም ጎሎች በ67ኛው እና 89ኛው ደቂቃ ላይ ኤሚኒኬ አስቆጥሯል፡፡ ኤሚኒኬ የመጀመሪያውን ከረዥም ርቀት ላይ አክርሮ በመምታት ሁለተኛውን በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡
በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዕረፍት በፊት በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የነበረ ሲሆን አራት ያህል ሙከራዎችንም በሳላዲንና አዳነ አማካኝነት ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ በተለይም ሳላዲን ካደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች አንደኛዋ(24ኛው ደቂቃ ላይ ነው) የጎሉን መስመር ማለፍ ችሎ የነበረ ቢሆንም ዳኛው ሳያፀድቆት ቀርተዋል፡፡ በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ናይጄሪያ በተመሳሳይ አራት ያህል ሙከራዎችን ማድረግ ችላ ነበር፡፡ በተለይም አንደኛዋ ኳስ ጎል መሆን ሲገባት በተጨዋቹ ስህተት ግብ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ከእረፍት መልስ የኢትዮጵያ ቡድን በተመሳሳይ በኳስ ቁጥጥርና ግብ በማስቆጠር የበላይነቱን ማስጠበቅ ችሎ ነበር፡፡ ይህ ግን የሆነው እስከ 67ኛው ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ 67ኛው ደቂቃ ላይ ናይጄሪያ በኤሚኒኬ የአቻነት ጎል ማስቆጠር ከቻለች በኋላ የበላይነቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ችላለች፡፡ በ89ኛው ደቂቃ ላይም አይናለም ሃይሉ በአቋቋም ችግር ምክንያት በፈፀመው ስህተት ዳኛው የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት ኤሚኒኬ አስቆጥሯ ጨዋታው በናይጄሪያ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በሜዳዋ ባደረገችው ጨዋታ አራት ያህል ቢጫ ካርዶች ታይተዋል፡፡ ሁሉንም ካርዶች የተመለከቱት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ስዩም ተስፋዬ፤አዳነ ግርማ፤አዲስ ህንፃና አይናለም ሃይሉ ናቸው፡፡ የዛሬውን ጨዋታ የመሩት ካሜሮናዊው ዳኛ በ24ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰይድ ያስቆጠረውን ጎል ባለማፅደቃቸው ከተመልካቹ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገው ውጤታማ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጉዟ ዛሬ በተመዘገበው ውጤት ምክንያት የተገታ ይመስላል፡፡ ቡድኑ ከአንድ ወር በኋላ በሚኖረው የመልስ ጨዋታ በሁለት ግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻለ የማለፍ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ናይጄሪያን በሜዳዋ በወሳኙ ጨዋታ ማሸነፍ ከባድ የሚሆንበት ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በዚህ የዓለም ዋንጫ ከአራት ሀገሮች ጋር ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም ነበር፡፡ ይህም ጉዟ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያውና ውጤታማው ነበር፡፡ በአምስተኛውና የመጨረሻው ማጣሪያ ጨዋታ ግን በናይጄሪያ ያውም በዚህ ሁለት ዓመት አንድም ጊዜ ባልተሸነፈበት ሜዳ ሊሸነፍ ችሏል፡፡

ምንጭ፡ ስፖርት አዲስ ጋዜጣ

Previous Story

ይቺ ባንዲራ! – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

Next Story

በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ – እውነትና ከሕደት………(ከ ይድነቃቸው ከበደ)

Go toTop