(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ለአምስት ቀናት የሚቆይ አድማ መጀመሩን ቀድም ሲል ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም:: አድማውን ለማስተጓጎል ሕወሓት የሚመራው መንግስት ሃይል ለመጠቀም ቢሞክርም ሕዝብ ግን ከዓላማው አልመለስም እንዳለ ነው::
አድማው እየተደረገባቸው ካለባቸው ከተሞች መካከል ጅማ ስትሆን በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውና “ሆራይዘን ቡና” የተሰኘው ንብረትነቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለቤትነት ከሚተዳደረው ሁለትመቶ ሄክታር መሬት ላይ የተሰበሰበውን ቡና ሕዝቡ እየተከፋፈለው መሆኑን ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች ጠቁመዋል::
የሕወሓት ባለስልጣናት በስማቸውም ሆነ በዘመዶቻቸው ስም በርካታ ንብረቶችን የያዙ ሲሆን ልክ ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት “የሚበላውን ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” እንዳሉት ተቃውሞዎች ሲነሱ የነርሱ ንብረቶች ቅድሚያ ተጠቂ እንደሚሆኑ በተከታታይ ከሚደረጉ ሕዝባዊ አድማዎች ለማየት ችለናል::