ሀ/ መግቢያ
የሀገራችን ኢትዮጵያ የታሪክ ገድሏ በአንክሮ ሲታይ በተደጋጋሚ ታሪካዊ ወቅቶች ጨካኝ የሆኑ መሪዎች በመንግሥትነት እንደተፈራረቁባት የሚታወቅ ነው። በእነዚህ መንግሥታት ዘመንም ከሕዝቡ መካከል እነዚሁን ጨካኝ መንግሥታት ቀዳሽና አወዳሽ ግለሰቦች እንደነበሩ ረጅሙ የሀገራችን ታሪክ በግልጽ ያስረዳናል።
ቀረብ ባለውም ጊዜ ብናይ፤ ከ70 ዓመት በፊት በዘመናዊ ጦር መሣሪያ ተደራጅቶ ከፍተኛ የሠለጠነ ሠራዊት አዘጋጅቶ ከወረረን ፋሽስት ጣሊያን ጋር ያሴሩና የሀገርን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ቅጥረኛ ከሃዲ ባንዳዎች እንደነበሩ ይታወቃል።
በእነዚህ ጨካኝ መንግሥታት መካከል ያለው የጋራ አማካኝ ባህሪ ሲታይ፤ በሀገር ክብርና ኩራት፣ በብሔራዊ ጥቅም፣ በግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ወደ ኋላ የማይሉ ምንም የማያወላውል አቋም እንደነበራቸው ታሪክ ይመሰክራል።
ሆኖም ግን፣ ላለፉት 22 ዓመታት ሀገራችንን የሚገዛው የፋሽስቱ ወያኔ ገዥ ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የጨካኝ ጨካኝ ገዥ ቡድን ነው። ከለየላቸው የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማሴርና በማበር የኢትዮጵያን ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥሏል። ወያኔ ከፈጸማቸውና ከሚፈጽማቸው አያሌ ክህደቶችና ወንጀሎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ብንጠቅስ፥
• ሀገራችንን የባሕር በር አልባ አድርጓታል፤
• ከፍተኛ የተፈጥሮ ክምችት ያለውን ለም የድንበር መሬታችንን ለሱዳን አስረክቧል፤
• የሀገራችንን ዝናና ክብር አዋርዷል፤
• ወገኖቻችንን ከቀያቸው በግፍ በማፈናቀል ለም መሬታችንን ለባእዳን ከበርቴዎች ቸብችቧል፤
• በሕዝባችን ላይ የዘር ማጥፋት ከፍተኛ ወንጀል ፈጽሟል፣ በፈጸምም ላይ ይገኛል፤
• ንጹሃን ዜጎቻችንን በጠራራ ፀሐይ ረሽኗል፤ እያረሸነም ነው፤
• ሕዝብን ከሕዝብ በማለያየት መርዘኛና አደገኛ የሆነ የጎሳ አስተሳሰብን አሰራጭቷል፤
• የሀገራችንን ሃብትና ንብረት ዘርፏል፣ እየዘረፈም ነው፤
• የልማት ፀር የሆነውን ሙስናን እንደ አንዱ ፖሊሲው ይዞ አስፋፍቷል፤
• ሀገራችንን ለከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጓል፤
• የሕዝባችንን ኑሮ የምድር ሲዖል ስለአደረገዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ወጣት ወገኖቻችን ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል፤
• በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ዘመቻ አካሂዷል፤ እያካሄደም ነው፤
እኛ በኦሃዮ ኮለምበስ ከተማና አካባቢው እንዲሁም በአጎራባች ከተሞችና ስቴቶች የምንኖር ኢትዮጵያውያን በዛሬው ዕለት መስከረም 4 ቀን 2006 ዓ.ም. (September 14, 2013) የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ መድረክ በኮለምበስ፣ ኦሃዮ በራማዳ ሆቴል (Ramada Hotel) በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተን፥
• ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና አንድነት በሀገራችን ላይ እንዲሰፍን ከፀረ-ኢትዮጵያዊዉ ወያኔ ጋር ሲታገሉና ሲፋለሙ በታላቅ ጀግንነት የተሰውትን ወገኖቻችንን በክብር በማስታወስ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ፀሎት አድርገንና
• በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ገለጻና ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጋበዙትን፥
1ኛ/ ዶ/ር ኑሮ ደደፎ ፥ በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ )
ከፍተኛ አመራር አባል፤
2ኛ/ አቶ ተክሌ የሻው ፥ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ሊቀ-መንበር፤
3ኛ/ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፥ የኢኮኖሚ ሊቅ እና
4ኛ/ ዶ/ር መሳይ ከበደ፥ የፍልስፍናና ሥነ-መንግሥት ሊቅ
ገለጻና ማብራሪያ ካዳመጥንና ጥልቀት ያለው የጋራ ውይይት ካካሄድን በኋላ እንዲሁም ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ አደገኛ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ በማጤንና በመገንዘብ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፥
ለ/ የአቋም መግለጫ
1. በወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በኢትዮጵያዉያን መካከል በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በአካባቢ ወገንተኛነት ላለፉት 22 ዓመታት የተረጨዉን አደገኛ መርዝ ለማምከንና ለማጥፋት በሁሉም ብሔረ-ሰቦችና ሐይማኖቶች መካከል የሚደረገዉ መግባባትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እያበበና እየጠነከረ እንዲወጣ እንታገላለን።
2. በአማራዉና በኦሮሞዉ ሕዝብ መካከል በኢትዮጵያዊነት የማያወላዉል የቆየው ስሜት፣ አንድነትና ማሕበራዊ መስተጋብር የበለጠ እንዲጠነክርና ይህም ሁኔታ ለሀገራችን መረጋጋት፣ ሰላምና ዕድገት መሠረት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ትግል እናደርጋለን።
3. ፀረ-ኢትዮጵያዊዉ ወያኔ የገዢ ቡድን ከፋፍለህ ግዛውን መርዘኛ ፖሊሲውን ለማራመድ በሃይማኖት ተቋማትና በሙያ ማህበራት ጣልቃ እየገባ የሚያካሂደውን እርስ በእርስ የማበጣበጥ ሴራ በጥብቅ እናወግዛለን።
4. በወያኔ እስር ቤት እየማቀቁ የሚገኙ የፓለቲካ፣ የሕሊናና የሃይማኖት እስረኞች፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን።
5. ወያኔ በልማት ስም እያወደማቸው ያሉ የታሪክ ቅርሶችና የገዳማት ይዞታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል። በተለይም እንደ ዋልድባ፣ አሰቦትና ዝቋላ በመሳሰሉ ገዳሞችና እንዲሁም በነዚህ ሥፍራዎች በሚኖሩ አባትና እናት መናንያን ላይ እየተፈጸመ ያለዉ ማፈናቀልና ጭፍጨፋ እንዲሁም የገዳማት ማፈራረስ እናወግዛለን። በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን።
6. የፀረ-ኢትዮጵያዊዉ ወያኔ ገዥ ቡድን አመራር አባላት የነበሩና አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉት በሀገር ላይ ክህደት የፈጸሙ፤ በሕዝብ ላይ እልቂት ያካሄዱና የሀገርን ሀብትና ንብረት የዘረፉ ስለሆነ፤ አንዳንዶቹም እነዚህን ከፍተኛ ወንጀሎች ከፈጸሙ በኋላ ከሀገር እየሸሹ በአሁኑ ወቅት የነፃነት አምባ የሆነችውን አሜሪካ መጠለያ ዋሻ እያደረጓት በመገኘቱ፤ ሥልጣን ላይ ያሉትንና እነዚህ የሸሹ ወንጀለኞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ስለሚፋረዳቸዉ በአስቸኳይ አንድ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ወንጀለኞች ተከታታይ ኮሚሽን ተቋቁሞ አስፈላጊ የድምጽ፣ የምስልና መሰል ዶኩሜንት ማስረጃዎች ሰብስቦ የእነዚህን ሀገር-ከሃዲ ወንጀለኞች ጉዳይ በዓለም-አቀፍ የፍትህ መድረኮች ላይ እንዲታይ የሚያደርግና ሕጋዊ እርምጃዎች የሚያስወስድ ኮሚሽን እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን፣ ንቅናቄዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትንና ምሑራንን አበክረን እንጠይቃለን።
7. ከጉራ ፈርዳና ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉት፤ ሐብትና ንብረታቸዉ የተዘረፉትና የወደመባቸዉ የአማራ ተወላጆች እንዲሁም የአማራዉን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ በረቀቀ መንገድ በሕክምና ሥም የተደረገዉንና እየተደረገ ያለዉን ደባ፤ በወገናችን የኦሮሞ ሕዝብና በሌሎችም ኢትዮጵያዉያን ላይ በየጊዜው የሚደረገውን ጭፍጨፋና ግድያ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለሆነ፤ ለዚሁ ድርጊት የወያኔ ገዥ ቡድን አባላትና አጋሮቻቸው በታሪክና በሕዝብ ተጠያቂ ከመሆናቸው በላይ፤ የትም ቦታ ቢሸሹና ቢሸሸጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አድኖ ለፍርድ እንዲሚያቀርባቸው ከወዲሁ እንዲያውቁት በጥብቅ እናሳስባለን።
8. ለመኖር ብቻ ብላችሁ የፀረ-ኢትዮጵያዊዉ ወያኔ ገዥ ቡድን ሥርዓትን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርታችሁ በማገልገል ላይ ያላችሁ ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ነገ ጠዋት በታሪክና በሕዝብ ተጠያቂና ተወቃሽ ከመሆናችሁ በፊት፤ ከወያኔ ጋር የምታካሂዱትን የጥፋት ዘመቻ ትብብር እንድታቆሙና ለወገኖቻችሁና ለልጆቻችሁ ስትሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንድትቆሙ እናስገነዝባለን።
9. በክህደት ተወልዶ በክህደት ያደገዉ ፀረ-ኢትዮጵያዊዉ ወያኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ሆኖ በምስጢር ከሀገሮች ወይም ከዓለም-አቀፍ ድርጅቶች ወይም የንግድ ተቋማት (ኩባንያዎች) ወይም ግለሰብ ነጋዴዎች ጋር የተዋዋላቸውና የተፈራረማቸው ማንኛውም ዓይነት ውሎች፣ ስምምነቶች፣ ደንቦች ወዘተ… በሙሉ አሁንም ሆነ ወደፊት እንደ ሕጋዊ ውሎችና ስምምነቶች ቆጥረን ልንቀበል እንደማንችል መንግሥታትን፣ ዓለም-አቀፍ ድርጅቶችንና ማህበራትን እንዲሁም የዓለም ሕብረተሰብን ከወዲሁ ልናሳውቅ እንወዳለን።
10. ፍትህ፣ ርትዕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገንባት አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን እናምናለን፤ ይህንኑን እውን ለማድረግም እንታገላለን።
11. በየጊዜው የተፈጠሩና የሚፈጠሩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅቶች፣ ንቅናቄዎችና የሲቪክ ማህበራት አንድነትና ትብብር ሊሰምር የሚችለዉ የጋራ መርሐ-ግብር በተላበሰ መልኩ፤ በማዕከል ደረጃ የሚወጣን የድርጊት ዕቅድ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደሆነ እያመን፤ ሀገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ንቅናቄዎች በሩቅ ከመተያየት በቅርብ በመቀራረብ በጋራ የሚሰሩበት ወሳኝ ወቅት አሁን ነዉ። ስለሆነም፤ የወያኔን ግብአተ-መሬት ለማፋጠንና ከዛም በኋላ የፖለቲካ ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈለግ በአጽንዖት እናሳስባለን።
ድል ለታላቁ ኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ በነፃነቷ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ መድረክ
በኦሃዮ ኮለምበስ ከተማ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ
ላይ የተገኘን ሀገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያን
መስከረም 4 ቀን 2006 ዓ.ም.
(September 14, 2013)
ኮለምበስ፣ ኦሃዮ፣ አሜሪካ