ዕዘኑ ለቀሪ

February 22, 2017

የመቅደላው ደባ ቋጠሮ
የተቀበረው በቂም ጓሮ
የምስጢሩ ገመና
ለሥልጣኑ ንግሥና
ከጠላት ጋር ወግኖ
በተቸረው ኃይል መቅኖ
መይሳውን አስገድሎ
ለመግዛት ተደላድሎ
በትረ መንግሥቱን ምራጭ ካሳ
የጨበጠበት ድርጊት ጠባሳ
ደረስጌን በውቤ ብሎ
የቂም ብድሩን ከፍሎ
የጎንደሮች መሬት ቁርሾ
የበደሉ ዋይታ ሙሾ
የግፉ ክፋት ገመና
ይደረደራል ገና
በበገና በበገና።

ያችን የሙታን እናት
አጉል ድከሚ ብሏት
ያለ ፋይዳ ከንቱ ልፊ
ዘርሽንም በዘር አጥፊ
ለማለት ይመስላል መለእክቱ
ነገረ ሥራው ኩነቱ።

ለባለ ቀኑ ድሎት
የማይጓደል አቅርቦት
ይረጋገጥ ዘንድ ታልሞ
የራሱን ኩራዝ አጨልሞ
በየመብራቱ ምሰሶ ስር
ዘብ መቆሙ ደብረታቦር
ምፀቱ ለገብርዬ… ለገልሞ
በአግራሞት አስደምሞ
የትንብቱ ቅላጼ መዋዕሉ
ለካስ ጊዜ ኖሯል ባለድሉ።

ለጎንደሮች መከራ
ለባለ ጊዜው ጮራ
ያብርሆት ነገን ሲዘራ
ጊዜ በይኖ ሁሉንም
ሲያበራና ሲያጨልም
ኩራት ለሚሰማት ለባለ ጊዜዋ
ለዕልቂት ዘማሪዋ
ሞቷን በቂም ቋጥራ
መቃብሯን ቆፍራ
ባለቀ ቀን ኗሪ
ልጡ ለተራሰው በዕዳዋ ተጧሪ
ለወራሿ ትውልድ እዘኑ ለቀሪ።
አብርሃም በየነ

Previous Story

በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ (የኦፌኮ አመራሮች የነአቶ በቀለ ገርባ) የቪዲዮ ማስረጃዎች መታየት ቀጥለዋል (የካቲት 13 2009)

Next Story

የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያለ ማስረጃ ክፍያ ተፈጽሟል አለ

Go toTop