ጥር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. / January 23, 2016
በኮሎምቦስ ኦሃዮ የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ በአገራችን በኢትዮጵያ በተለይም በወልቃይት ጠገዴ ወቅታዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ቅዳሜ ጥር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. (January 23, 2016) በተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ በመገኘት በሰፊው ተወያይተናል። ስብሰባው ከመቸውም ለየት የሚያደርገው ወጣቶችና ሴቶች በብዛትና በንቃት መሳተፋቸው ሲሆን አባቶችም ሰለ ታሪካችንና ማንነታችን ሰፋ ያላ ገለጻ ሰጥተዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰለተቋቋመው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄን አንግበው ለፌደራል መንግስትና ለተለያዮ የመንግስት አካላት የወልቃይት ጠገዴ ሕገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በመሳሪያ ሃይል የተነጠቀው መብትና ማንነት ለማስመለስ ላይ ታች እያሉ ታላቅ ሰላማዊ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ስለዚህ ጉዳዩ በቀጥታ ስለሚመለከተን ኮሎምቦስ ኦሃዮም ሆነ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛት (ስቴትስ) የሚገኙ ወገኖች በመነጋገር በኢትዮጵያ ሰላማዊና ሕጋዊ ስርዓትን ተከትለው የህዝባቸውን የመብትና የማንነት ጥያቄያቸውን ምላሽ ለማስገኘት ለተቋቋመው ኮሚቴ ሙሉ ድጋፍ እንደምንሰጥ ተስማምተናል።
ምንም እንኳን ጥያቄው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ መንግስት በጽሁፍ አቤቱታ ብናቀርብም መልስ ተነፍጎን እስካሁን ቆይቷል። አሁን ግን በህገር ቤት የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለምንም ፍራቻ “እኛ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ትግርኛ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ያጎራባች ሕዝብ ቋንቋ ከመናገራችን ውጭ የራስችን ባህልና ወግ እንዲሁም ስነ-ልቦና ያለን ሕዝብ ወደ ጥንቱ ቦታችን በጌምድር ጎንደር (በአሁኑ አጠራር የአማራ ክልል) መመለስ አለብን፤ ህገ-መንግስቱም ይፈቅድልናል” በማለት ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍለው የሁላችንም ጥያቄ ይዘው ስለተነሱ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የካባቢው ተወላጆች በረስ ተነሳሽነት ለዚህ ኮሚቴ የሚያስፈለገውን የሞራልና መሰል ድጋፍ እንዲያስተባብሩ ሰባት (7) አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ አቋቁመዋል።
ሕበረተሰቡ በዚህ አጋጣሚ ባስተላልፈው መልዕክት የኢትዮጵያ መንግስት የነዚህ ወገኖች ጥያቄ ህገ-መንግስቱ የሚፈቅደውና ሰላማዊ እንደሆነ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸውና ከኃይል እርምጃ አና ተፅዕኖ እንዲታቀብ አሳስበዋል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!