“በሊቢያ የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር ነው” ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ

April 20, 2015

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ወገኖች አሰቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ዘግበዋል፡፡
ዘገባው ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሐን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡

አሰቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኃላፊነት በማይሰማቸውና በእነሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዘዋለች፡፡

ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤
እንደዚሁም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሣራ እንጂ ምንም ዓይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ

Previous Story

   ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን  የገቢ ምንጭ በማድረግ ይጠቀምበታል፦

Next Story

በደቡብ አፍሪካ ሰሞኑን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ግፍ በመቃወም በአሁኑ ሰአት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ፊትለፊት ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ኢትዮትዩብ በስፍራው ይገኛል በምስል እና ቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎችን ማቅረቡን እንቀጥላለን ተከታተሉን።

Go toTop