የከምባታ ህዝብ ነገ የተቃውሞ ሰልፍ ሊወጣ ነው

February 9, 2015

(ነገረ ኢትዮጵያ) የከምባታ ህዝብ ሆን ተብሎ መሰረተ ልማት እንዳይገነባለት በመደረጉና በተራድኦ ድርጅቶች የተሰሩት መሰረተ ልማቶች ስራ ላይ እንዳይወሉ በደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች እየተፈፀመበት የሚገኘውን በደል በመቃወም ነገ ማክሰኞ የካቲት 2/2007 ዓ.ም በዱራሜ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ የከምባታ ህዝቦች ኮንግረንስ ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የከምባታ ህዝብ በተመሳሳይ ጉዳይ ህዳር 26/2007 ዓ.ም ዱራሜ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጎ የነበር ሲሆን የነገው ሰልፍም የክልሉ መንግስት ችግሮቹን ለመቅረፍ ዝግጁ ባለመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከምባታ ውስጥ ሊሰራ የታሰቡና የተጀመሩ ስራዎችን የደኢህዴን ባለስልጣናት ወደተወለዱባቸው አካባቢዎች እንደሚታጠፉ የገለጹት አቶ ኤርጫፎ አንገጫ የተባለ ቦታ ላይ ተራድኦ ድርጅት የሰራው ሪፈራል ሆስፒታል ተሰርቶ ካለቀ በኋላ መገዘጋቱን እንዲሁም ቃጫ ቤሮ ወረዳ በተራድኦ የተሰራ ሆስፒታል ስራ ላይ እንዳይውል መደረጉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የሚሰሩ መንገዶች የባለስልጣናቱ ዘመዶች በኮንትራክተርነት ስለሚይዟቸው ይጠናቀቃሉ በተባሉበት ጊዜ እንደማይጠናቀቁና ለሙስና የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በሙስና እና በዝምድና ምክንያት መንገዶች እንዳይሰሩ የሚያደርጉት ባለስልጣናቱ ህዝቡ ጥያቄ በሚያነሳበት ወቅት ‹‹መሰረተ ልማት ስለሌላችሁ ወደ ከምባታ መጥቶ ለማልማት አልተቻለም፡፡›› የሚል መልስ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡
በከምባታ ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱና የደኢህዴን ባለስልጣናት ችግሩን ለመቅረፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ህዝቡ የሚፈጸምበትን በደል ለማሰማት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በዱራሜ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርግ ተገልጾል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ ህዝቡ ራሱን በማስተባበር የጠራው መሆኑም ተገልጾአል፡፡

Previous Story

ቤዛዊት ዘለቀ እንደጃፓኗ ቆንጆ ሆና ለጥላሁን ገሰሰ በዘፈን የሰጠችው ምላሽ (ያድምጡ)

Next Story

Hiber Radio: ኤርትራ በርካታ ታንኮችን እና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሱማሊያ ላንድ አስገብታለች መባሉና ማስተባበሏ.. ከኢትዮጵያ የሔዱ ቤተ እስራኤላውያን ለተለያዩ ህመሞች ስለመጋለጣቸው… በኬንያ ያሉ ጋዜጠኞችን መንግስት አፍኖ ለመውሰድ በተዘዋዋሪ መንገድ መግለጹ.. ሰማያዊ ፓርቲ ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ እንደ አንድነት ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈፅሙበት እየሰራሁ ነው ማለቱና ሌሎችም

Go toTop