አቶ በላይ ፍቃዱ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መሪ ከፍኖተ ነፃነት ጋር ያደረጉት ቆይታ

January 23, 2015

አቶ በላይ ፍቃዱ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን መምራት ከጀመሩ ሦስተኛ ወራቸውን ይዘዋል፡፡ ፓርቲው፣ ከኢህአዴግ በበለጠ የምርጫ ወንበር ተወዳዳሪዎችን አቅርቦ ወደ ምርጫ እንዲገባ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ የርሳቸውን ወደ ፓርቲው አመራርነት መምጣት ተከትሎ ከፍተኛ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው ሰዎች፣ ጋዜጠኞችና ሙያተኞች ፓርቲውን ተቀላቅለዋል፡፡ አሁን ከምርጫ ቦርድ በኩል ይህንን እንቅስቃሴ እና ስኬት ለመግታት ከፍተኛ ሴራ እየተሰራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አቶ በላይን የምርጫ ቦርድ ሀሳብ ምን እንደሆነ፣ ምርጫ ከመሳተፍ የሚታገዱ ከሆነ ፓርቲያቸው ምን ለማድረግ እንዳሰብ ከባልደረባችን ሰለሞን ስዩም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
———————————————
ፍኖተ-ነፃነት፡- ከምርጫ ቦርድ ጋር የገባችሁበት እሰጣ-ገባ በእጅጉ ጦፏል፤ ችግሩ ምንድነው?በላይ፡- አንድነት፣ ሙሉ በሙሉ የሚጠበቁበትን የህግ ግዴታዎች ተወጥቷል፤ ይሄም ሆኖ ምርጫ ቦርድ እውቅና ሊሰጠው አልፈለገም፤ በኛ እምነት የምርጫ ቦርድ አቋም ፖለቲካዊ ነው፡፡
ይሄን አቋም ለምን እንደወሰደ ጭምር መናገር ይቻላል፤ አንደኛ አንድነት ትርጉም ያለው ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚችልበት ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ስለሚገኝ ነው፡፡ ማንም እንደሚያውቀው ዓመቱ የኢህአዴግ መደምደሚያ ይሆናል የሚል ቁርጠኛ ውሳኔ አስተላልፎ እየተንቀሳቀሰው ነው፡፡ ደጋፊዎቹንም በዚህ አግባብ ቀርፆቸዋል፡፡ ስለዚህ ስርዓቱን የመከላከል ኃላፊነት የወሰደው ምርጫ፣ ቦርድ እኛን በዚህ መልኩ ከፉክክሩ ሊያወጣን ተነስቷል፡፡

ፍኖተ-ነፃነት፡- ምርጫ ቦርድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፓርቲው ለሁለት ተሰንጥቋል፤ አንደኛው የአመራር ቡድን በዲ አፍሪክ ሆቴል ጉባኤ ሲያደርግ ሌላው በቢሮው አድርጓል፤ ስለዚህ ካልታረቃችሁ እውቅና አልሰጥም እያለ ነው፡፡ ለመሆኑ አመራሩ ለሁለት ተከፍሏል?

በላይ፡- የዛሬ ሦስት ወር አካባቢ የደብዳቤ ልውውጥ ስንጀምር እንዲህ የሚል ነገር አልነበረም፡፡ በወቅቱ የጠየቁን ግልፅ ያልሆኑ ያሏቸውን ነገሮች ማብራሪያ እንድንሰጣቸው ብቻ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ፤ “የኮረም ቀጥራችሁን በደንብ ላይ አስገቡ” የሚል አንዲት ጥያቄ ብቻ ጠይቀውናል፡፡ “የአመራር መከፋፈል” የሚለው የመጣው አሁን ነው፡፡ ያ ደግሞ በተለያዩ ማደናገሪያዎች እኛን ከጨወታ ውጪ ማድረግ ስላልተቻላቸው ወደፖለቲካ ውሳኔ ዞሩ ማለት ነው፡፡ ከአንድነት ስራ አስፈፃሚ ውስጥ አንድም ሰው ተቃውሞ የለውም፡፡ አመራር ከሚባሉትም መካከልም አንድም ሰው የለም፡፡ ተቃውሞ አለን የሚሉ የአንድነት አባላት ቁጥርም ከአንድ እጅ ጣት አይበልጥም፡፡

ፍኖተ-ነፃነት፡- ምርጫ ቦርድ፣ “ላስታርቃችሁ፣ ካልታረቃችሁ ወደ ምርጫ አትገቡም” የማለት ህጋዊ ስልጣን አለው?

በላይ፡- ምንም አይነት ህጋዊ መሠረት የለውም፤ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ልዩነት አለው የተባለ ቢኖር እንኳ ፓርቲው ባለው የመተዳደሪያ ደንብና ተቋማት በኩል ነው መስተናገድ ያለበት፤ የብሔራዊ ዲሲፕሊን ኮሚቴ አለ፤ ብሄራዊ ም/ቤት አለ፤ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አለ፤ ከነዚህ ከዘለለ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ነው የሚሄደው፡፡ መንገዱ ይሄ ነው፤ ምርጫ ቦርድ ገብቶ የመዘባረቅ ስልጣን የለውም፡፡

ፍኖተ-ነፃነት፡- ሰሞኑን የኢሕአዴግ ልሳን በሆኑት፤ “EBC” እና “ራዲዮ ፋና” በኩል፤ “ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ችግሩን እንዲፈታ ያሳየው ሆደ-ሰፊነት እና የሰጠው ጊዜ ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ያለውን ከፍ ያለ ተቆርቋሪነት ያሳየ ነው” የሚል ስብከት ተጀምሯል? ምን ትላለህ?

በላይ፡- በመጀመሪያ ደረጃ፣ ምርጫ ቦርድ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲያብብ ይሰራል የሚል አቋም የለንም፡፡ ተቋሙ ብቻም ሳይሆን፣ ውስጡ ያለ አመራሮች ነፃ ሰዎች ናቸው ብለን አናምንም፡፡ በሆደ-ሰፊነት ሊያስተናግደን ቀርቶ፣ በአዋጅ የተሰጡንን መብቶች እየነጠቀን ነው፡፡ የተዓማኒነትም የአቅምም ችግር ያለባቸው ሰዎች ስብስብ ነው፤ ስርዓቱ ደግሞ ይህንን ይፈልገዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ቦርዱ የመደራጀት መብትን ፈተና ውስጥ ከቶታል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ምርጫ ቦርድ እና “የዴሞክራሲ ተቋማት” ባሉበት ሀገር፣ የፓርቲ ፖለቲካ መቼም ሊሰራ እንደማይችል አሳይቶናል፡፡ ትልቅ ተቋም ልትገነባ ትችላለህ፤ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ከመሀልህ ሶስት ሰው ብቻ አባብሎ ያፈርስብሃል፡፡ እኛ ከምርጫ ቦርድ የጠየቅነው ሆደ-ሰፊነትን ሳይሆን፣ የተሰጠንን የህጋዊ መብት አትጣሱብን የሚል ነበር፡፡ ያን ሊያደርግ ግን ፍቃደኛ አይደለም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ምርጫ ቦርድ ከእንግዲህ የማስተናግዳችሁ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለታችሁ (ያኮረፈው ቡድን)፤ አንድ ላይ ጉባኤ ስትጠሩ ነው የሚል አቋም ይዟል፤ ትጠራላችሁ?

በላይ፡- ጥያቄው ህገ-ወጥ ነው፡፡ አንድነት ጉባኤ የሚጠራበት አግባብ በደንብ ላይ አለ፤ አንደኛ በብሔራዊ ም/ቤት፣ ሁለተኛ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ ሶስተኛ 2/3ኛውን አባል ያስፈረመ ሰው፡፡ ከዚያ ውጭ ከነ እከሌ ጋር ጠ/ጉባኤ ጥሩ ማለት በራሱ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በመሆኑም ደንባችንንና ተቋማችንን በማፍረስ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር አንተባበርም፡፡ ስለዚህ ጠ/ጉባኤ አንጠራም፤ ቢጠራም እንኳ የምርጫ ቦርድ አቋም ፖለቲካዊ በመሆኑ የሚፈልጉት አመራር እስካልመጣ ድረስ በህጉ አግባብ አያስተናግዱንም ማለት ነው፡፡

ፍኖተ-ነፃነት፡- ጉባኤ ካልጠራችሁና ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን የሚያግድ ከሆነ ትበተናላችሁ ማለት ነው? ቀጣይ አቅጣጫችሁስ ምንድነው?

በላይ፡- ምርጫ ቦርድ በዚህ አግባብ መምጣቱ ትግሉን አንድ እርከን ከፍ ነው ያደርገዋል፤ ምክንያቱም የምናመራው ወደነፃነት ትግል ነው፡፡ ፡፡ ስለዚህ በአቋም ደረጃ፣ በፕሮግራም ደረጃ የምንታገልበት የነፃነት ጥያቄ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ትግሉ ከርዕዮተ-ዓለም የዘለለ የነፃነት ትግል ነው፤ በዚህ ደግሞ የግድ ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ነፃ እና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት መፍጠሪያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ ፕሬሶች፣ ፍርድ ቤት፣ በተሰጣቸው የህግ ማዕቀፍ ከገቡ የዛኔ ማንም በነፃነት ይፎካከራል፡፡ ስለዚህ አንድነት ኖረም አልኖረም፣ ይሄ ትግል ጥርጥር በሌለው ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ አሁን ሌላ አቋም ላይ ደርሰናል፤ እንዲህ አይነት “ምርጫ ቦርድ” ባለበት ሀገር የፓርቲ ፖለቲካ እንደማያዋጣ አቋም ይዘናል፡፡
ፓርቲ፣ ለስልጣን የሚታገል ኃይል ማለት ነው፤ ይህም በስርዓቱ አሸርጋጆች አውድ ውስጥ ይቆጠራል፤ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት በፓርቲ ደረጃ ያንን ማሰብ አይቻልም፡፡ እዚህ ሀገር መደራጀት አትችልም፤ በራሪ ወረቀት መበተን አይቻልም፤ የደህንነት ክትትሉ ልብህን ያወልቃል፡፡ ይህ ከሆነ በፓርቲ ፖለቲካ ስልጣን መያዝ ይቻላል የሚለውን እምነት መልሰን መላልሰን መጠየቅ አለብን፡፡ ጥያቄው የነፃነት ትግሉ እንዴት ይፋፋም? የሚል ነው፡፡ በመላ ሀገሪቱ ወደ 40 የሚጠጉ ቢሮዎች አሉን፤ ለነፃነት ትግሉ ድጋፍ መስጠት የሚፈልግ የትኛውም አካል ቢሮውን መጋራት ይችላል፡፡ ይህን አቋም የያዝነው ነውጥ-አልባ ትግል ብቸኛው የነፃነት መንገድ ነው የሚለውን በሰፊ ጥሞና ስለደረስንበት ነው፡፡ ከእንግዲህ የድሉ መንገድ ይሄ ነው፤ ለዚህ ነው ከምርጫ ቦርድ ጋር የገባንበትን ጭቅጭቅ እንደ ትልቅ ዕድልም፣ ድልም አድርገን የምናየው፡፡ ስርዓቱ እና ቀኝ እጁ የሆነው ምርጫ ቦርድ፣ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ደረጃ እርቃናቸውን ስለቀሩ፤ ለነፃነት ትግሉ ደጋፊዎቻችንን በማሳመኑ ረገድ ረድቶናል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ትግሉ የነፃነት ከሆነ፤ እንደ አንድነት እየተገፋ ያሉትን ፓርቲዎች ለማስተባበር ያረጋችሁት ጥረት አለ?

በላይ፡- ከምርጫ ቦርድ ጋር በመግባባት ለመስራት ያላደረግነው ጥረት አልነበረም፤ እነሱ ግን ፖለቲካዊ አቋም ይዘዋል፡፡ ስርዓቱም፣ ለአፈና በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ፈሰስ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ያለን አማራጭ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ከሌሎች የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር መተባበር የግድ ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በመጨረሻ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖራል?

በላይ፡- ምርጫ ቦርድና ሰዎቹ ከአንድ /የቀበሌ ካድሬ የማይጠበቅ ስራ እየሰፉ ናቸው፡፡ ሰብዕና የሌላቸው፤ ምርጫ ቦርድን ያክል ተቋም ሊመሩ ቀርቶ ቤተሰብ እንኳየሚመሩ አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛ የምርጫ ፖለቲካ ከእንግዲህ ያዋጣል ወይ የሚለውን ደግመን ደጋግመን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት እንዳየነው መንገዱ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በኔ በኩል፣ ነፃነት በሌለበት ሀገር ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ውጤታማ መሆን እንደማይችል አምናለሁ፡፡ ስለዚህ መተባበር ግዴታ ነው፡፡
አንድነት ቢኖርም ባይኖርም የነፃነት ትግሉ ግን በርግጠኝነት ይቀጥላል፡፡

 

Previous Story

This is it, the night of nights

Next Story

የመኢአድ ም/ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ፓርቲው ገለፀ

Go toTop