አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፡ "ጠዋት ተነስቼ ጠላ ነበር የምጠጣሁ"

June 14, 2011

(አውራምባ ታይምስ)ጳውሎስ ኞኞ ይሰራበት በነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› አምድ የካቲት 1964 ዓ.ም. እትም ላይ ‹‹እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በብዛት የሌለው ስም የቱ ነው?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦለት፣ ‹‹ኞኞ ነው›› ሲል መልሷል። የተጠየቅከው አንተ ብትሆን ደግሞ ‹‹ማንዶዬ›› የምትል ይመስለኛል።
አዎ፣ ማንዶዬ የተለመደ ስም አይደለም። አባቴ የደቡብ ሰው ነው፤ የወላይታ። የስሙ አቻ የአማርኛ ቃል ‹‹ማንን ተክቼ›› እንደ ማለት ነው። አንተን የሚያስታውስ ‹‹እሁድ የእቁብ ጠላ›› የሚለውን ኮሜዲያዊ የሙዚቃ ስራን አይዘነጋም። የዘፈኑ የዜማና የግጥም ደራሲ ንጉሱ ረታ ይባላል። በወቅቱ ጠጪ ስለነበርኩ፣ ይመለከተኝ ስለነበር ለእኔ ሲሰጠኝ ደስ ብሎኝ ተጫወትኩት።
በርካታ ጣሳ ጠላ ትጠጣ እንደነበር ሰምቻለሁ።
ምን ያህል ትጠጣ ነበር?
ኦው! ጠዋት ተነስቼ ጠላ ነበር የምጠጣው። [ይጠጣ የነበረው ዶሮ ማነቂያ ውስጥ በሚገኘው ሾፌር ሰፈር ነበር።]
ጠዋት ከ40 በላይ ብርጭቆ ትጠጣ ነበር አሉ

ያኔ በብርጭቆ አይለካም እንጂ ከዚያ በላይ ጠጣ ነበር። ጠላ የምንጠጣው ጠዋት ጠዋት ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ካቲካላ፤ ጠጅ እንቀጥላለን። እስከ ምሽት ድረስ መጠጣት ነበር። [በወቅቱ
የሁለት ጣሳ ጠላ ዋጋ ስሙኒ ነበር።]
ከ60 ዓመት የሕይወት ተሞክሮህ አንፃር ስታየው፣ ‹‹ባልፈጠር ያመልጠኝ ነበር›› የምትለው ነገር ምንድን ነው?
መጠጥ ካቆምኩ 24 ዓመት ደፍኖኛል።
በፊት ብሞት መጠጥ ገደለው እንጂ እግዚአብሔር ገደለው አይባልም ነበር። ኖሬ ይህን በማየቴ ደስ ይለኛል። በመኖሬ ብዙ የሰው ፍቅር አግኝቻለሁ። ባልፈጠር ይህ የሕዝብ ፍቅር ከየት ይገኝ ነበር?
ከሰውነትህ አካላት መካከል ቢቀነስም አይጎዳኝ የምትለው አለ?
ሁሉም የሰውነት አካላት ጠቃሚ ናቸው። ኧረ! ይቀነስ የምለው የለም።
የፊት ገፅታህ ቁጡ ያስመስልሀል። ዝምታህም የሚያስጨንቅ አይነት ነው ልበል?
ብዙዎች እንደዚያ ይሉኛል። ከመናገር ይበልጥ ማዳመጥ ደስ ይለኛል። ብዙ ክርክር አልችልም። የማውቀውን ነገር እንኳን ‹‹አይደለም›› ቢሉኝ ከምከራከር ይልቅ አምኜ ብለያይ ብዬ ስለማምን
እተወዋለሁ። ዝም እና ኮስተር በማለቴ ብዙ ሰዎች የምጫወት አይመስላቸውም። ድሮ ድሮ ጠጅ ቤት ውስጥ ዝም ስለምል ተደባዳቢ መስላቸው ነበር። አንድ ሽማግሌ ከቀረቡኝ በኋላ፣ ‹‹ለፀብ የተዘጋጀህ እንጂ ተጨዋች ሰው አትመስለኝም›› ሲሉ ተዋውቄያቸው ለብዙ ዘመን ጓደኛ ሆነናል።
የ‹‹እኔ›› የምትለው መልካም ነገር ምንድን ነው?
በጎ ነገሮችን ለመስራት እሞክራለሁ። በጓደኞቼ ላይ አንዳንድ ችግሮች ሲመጡ በአቅሜ መተባበር እፈልጋለሁ። ሜሪ ጆይ የተራድኦ ድርጅት ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እሰጣለሁ። የቀይ መስቀል
አባል ነኝ። ይህን መሰል በሆኑ በጎ ሥራዎች ላይ ብካፈል ደስተኛ ነኝ።
የመኖሪያ አካባቢ በድርቅና በመሰል ችግሮች ሳቢያ ‹‹ለኑሮ አመቺ አይደለም›› ሲባል
ሰፈራ ይደረጋል። የሙያ ሰፈራ ቢኖር ወደ ምን መስፈር ትፈልጋለህ?
ወደ ሌላ ሙያ ብዘዋወር መስራት የምችል
አይመስለኝም። እንደገና ልጅ ብሆን ግን
እግር ኳስ ተጨዋች ብሆን ደስ ይለኛል።
ከሰራኸው ቲያትር ውስጥ እንደው ቢቻልና
በተመሳሳይ ሰዓት ‹‹ተዋናይ ሆኜ ብትሰራው፣
ተመልካች ሆኜ ባየው›› ብሎ ያስመኘህ አለ?
በ1964 ዓ.ም ‹‹ጤና ያጣ ፍቅር›› የሚል
ሙዚቃዊ ድራማ ሰርተን ሲጠናቀቅ
የነበረው ጭብጨባ በጣም ከፍተኛ ነበር።
ተመልካችም ሆኜ የማየው ቢሆን እሱን
መርጥ ነበር። ሌላው ቀርቶ በፊልም
ተቀርጾ እንኳን ባየው ደስ ይለኝ ነበር፤
ግን አልተደረገም።
ምላሽ ባለማግኘትህ ብቻ አምነህ የተቀበልከው
ነገር አለ?
አለ። እሱም በመስሪያ ቤታችን (በአዲስ
አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ) ያለውን
የሠራተኛ ደረጃ አመዳደብ ነው። አንድ
ጊዜ ኤክስፐርት ያደርጉሀል፣ ሲፈልጉ
ተዋናይ ያደርጉሀል። እናም ሳላምንባቸው
ብዙዎቹን ነገሮች ተቀብያለሁ። ‹‹ለምን?››
ብትለኝ እነሱ ማሟላት አለብህ የሚሉኝን
የትምህርት ሰርተፍኬት ስለማላሟላ ነው።
እኔ ትምህርት ያቆምኩት 7ኛ እና 8ኛ
ክፍል ላይ ስለሆነ ያሉኝን መቀበል ነው።
በችሎታ /በሙያ ፈትነው ኤክስፐርት፣
ተዋናይ ስድስት ተብዬ ነበር። እንደገና
በቢ.ፒ.አር ተራ ተዋናይ ተብዬ ወደ
ታች ስወርድ በዚህ ምክንያት ጡረታ
ወጥቻለሁ። [ጡረታ 1,067 ብር ያገኛል]
ባለፈው ሰኞ የጥበብ ‹‹ባለሙያዎች››
ከጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ባደረጋችሁት
ስብሰባ ላይ አንተ የተሳተፍክበት ተውኔት
አቅርባችኋል። ‹‹ልቤን የጭብጨባ ቡፌ
አጥግቦት ሆዴ ባዶ መሆኑን እያወቅኩ
ይኸው እስከዛሬ ዘለቅኩ›› የሚል የጥበብ
ሰዎች ኑሯችሁ አሳዛኝ መሆኑን የሚገልፅ ቃለ
ተውኔት ከአፍህ ወጥቷል። ይህ መሰል ነገር
ተደጋግሞ ይነሳል። እናንተ የሙያው ፀባይ
ታዋቂ ያደርጋችኋል፣ ጭብጨባ ይቸራችኋል።
አንድ የሕክምና ዶክተር፣ አካውንታንት፣ ሥራ
አስኪያጅ አይጨበጨብላቸውም እንጂ ትልቅ
ነገር ይከውናሉ። የእናንተ ታዲያ ምን ስለሆነ
ነው ተደጋግሞ የሚነሳው?
የቴሌቪዥን ድራማ፣ ፊልም እና ሌሎች
የጥበብ ውጤቶችን ስንሰራ የሚከፈለን
ገንዘብ አነስተኛ ነው። ይህ እንዲሆን
ያደረገው ደግሞ የቅጂ መብት በአግባቡ
አለመከበር ነው። በእኛ ሥራ ምንም
ነገር ሳይሰሩ ትልቅ ሀብታም የሆኑ
ሰዎች አሉ። አሁን በህይወት የሌለ
አረብ አገር ይኖር የነበረ አንድ ጓደኛችን፣
‹‹የሚገርማችሁ የእናንተ ድራማ
ሲተላለፍ እዚያ እሸጥ ነበር። ገንዘቡ
የቤት ኪራይ ለመክፈል ይረዳኝ ነበር››
ብሎኛል። እሱ ግልፅ ስለሆነ ነገረን እንጂ
ብዙዎች ተጠቃሚ የሆኑ አሉ። ይህ
ደግሞ ተገቢውን ህይወት እንዳንመራ
አድርጎናል እንጂ፣ ‹‹እኛ ከሌላው ህዝብ
የተለየን ነን›› ማለት አይደለም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን
ፓትርያርክ ሙሉ መጠሪያ ስማቸውን
ታውቀዋለህ?
[እየሳቀ] አታስቸግረኝ … በእውነት
ጥራ ብትለኝ አልችለውም። [እንደምንም
ሞክረው ብዬው ዝግ እያለ ቀጠለ] ብፁዕ
አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ አክሱም
ወይጨጌ እንደዚህ የሚል አለበት እና
አዎ እንደዚያ ነው …·ረ ይጠፋኛል።
[ለማንኛውም ፋንቱ እኔ ልሞክር…
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት
ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር
ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፣… ኦው!
ፋንቱ የቀረ ካለ ተባበረኝ፤ እንሞላዋለን፣
ስለ ትብብርህ አመሰግናለሁ።

Previous Story

የኢህአዴግ ፓርላማ ግንቦት 7ን ‹‹አሸባሪ ቡድን›› ሲል ወሰነ

Next Story

Eritrea Volcano Disrupts East Africa Air Travel

Go toTop