ሲቲ ማታን ለማስፈረም ተዘጋጅቷል

June 9, 2011

ማንቸስተር ሲቲ ለቫሌንሲያው የመስመር አማካይ ሁዋን ማታ ዝውውር 22 ሚሊዮን ፓውንድ በማቅረብ ተጨዋቹን ለማስፈረም የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቅሏል፡፡ የኢስትላንዱ ክለብ በጉዳዩ ዙሪያ ከቫሌንሲያው ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ሎሬንቴ ጋር የተወያየ ሲሆን በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለቻምፒየንስ ሊግ ማለፉን ማረጋገጡም ዝውውሩን እንዲፈፅም ይረዳዋል፡፡ ሲቲ ላለፉት በርካታ ወራት ማታን ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ ሆኖም እርሱን ለማስፈረም የሚደረገው ድርድር ፈር መያዝ የጀመረው ክለቡ የአውሮፓውያን ታላቅ ውድድር ተሳትፎ ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡
ቫሌንሲያም ከስፔናዊው ኢንተርናሽናል ዝውውር 25 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘት እንደሚፈልግ አረጋግጧል፡፡ ሲቲ ለዝውውር ያቀረበው ሂሳብም ከባለቤት ክለቡ ፍላጎት ብዙም የራቀ ባለመሆኑ ሁለቱ ክለቦች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሊቨርፑልም ማታን ለማስፈረም ከሚፈልጉ ክለቦች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የክለቡ የፉትቦል ዳይሬክተር ዳሚዬን ኮሞሊም ለዝውውሩ 17 ሚሊን ፓውንድ አቅርበዋል፡፡ ቼልሲም የተጨዋቹ ፈላጊ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጂ ሲቲ ባለክህሎቱን ተጨዋች ለመውሰድ ከፍተኛ ዕድል እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ ኢስትላንዱ ክለብ ብቸኛው አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥረው ባርሴሎናም ለማታ ያለው ፍላጎት አለመቀዝቀዙ ነው፡፡ በዚህም የ23 ዓመቱ አማካይ በስፔን ለመቆየት እና ላለመቆየት ትልቅ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም የቀድሞ የቫሌንሲያ የቡድን አጋሩ ዴቪድ ሲልቫ ስለማንቸስተር ከተማ ህይወት ብዙ ነገሮችን ከነገረው በኋላ ሀሳቡን ወደ እንግሊዝ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ሲቲ ለማታ ዝውውር ያቀረበው ሂሳብ በቀጣይ ስኳዱን ለማጠናከር ያለውን እቅድ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲያውም የቶተንሃም ሆትስፐሩ አሰልጣኝ ሀሪ ሬድናፕ ሲቲ አስቀድሞ ራስ የሚያስይዝ ታላላቅ ተጨዋቾችን እንዳስፈረመ መረጃው እንደደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን በማንቸስተር ዩናትድም ጭምር የሚፈለገው የዩዲኔዚው የመስመር አማካይ አሌክሊስ ሳንቼ ዝውውር የሚደረገው ድርድር ተቋርጧል፡፡ ሲቲ ማታ እና የ22 ዓመቱን ሳንቼዝ አስፈርሞ ከሲልቫ፣ ኤዲን ዜኮ እና ማሪዮ ባሎቴሌ ጋር ሊያጣምራቸው ይፈልጋል፡፡ ካርሎስ ቴቬዝ ግን በመጪው ክረምት ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ አርጀንቲናዊው አጥቂ በኢንተር ሚላን እና ሪያል ማድሪድ በጥብቅ ይፈለጋል፡፡ ማታ ክለቡን ከተቀላቀለም የአዳም ጆንሰን እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ሲቲ ግን እንግሊዛዊውን ወጣት በቂ የመጫወት እድል እንደሚሰጠው በማሳመን በክለቡ እንዲቆይ ለማድረግ እቅድ ይዟል፡፡
ሲቲ በቤይንስ ዝውውር የፉክክሩ አካል ሆኗል
ኤቨርተን በመጪው ክረምት ሌላኛው ተጫዋቹ ሌይተን ቤይንስ ለማንቸስተር ሲቲ ላለመሸጥ ከፍተኛ ትግል ይጠብቀዋል፡፡ ሮቤርቶ ማንቺኒ ለእንግሊዛዊው ኢንተርናሽናል ያለው አድናቆት ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመጪው የውድድር ዘመን የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሚሆነው ቡድን አካል ሊያደርገው ቋምጧል፡፡ ሆኖም ኤቨርተን ፈጣኑን እና ድንቅ ካሶችን ወደ ግብ የሚያሻግረውን ተጨዋች ማስፈረም የሚፈልግ ክለብ 18 ሚሊዮን ፓውንድ ማቅረብ እንዳለበት አስታውቋል፡፡ ይህ ደግሞ ክለቡ በጆሊዮን ሊስኮት ጉዳይ ከኢስትላንዱ ክለብ ጋር የገባበትን አለመግባባት ዳግም እንዲቀሰቅስ በር የሚከፍት ነው፡፡
ሊስኮት ሲቲን የተቀበለው ከሁለት ዓመት በፊት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ዝውውሩ እንዲሁ በቀላሉ መፍትሄ አላገኘም፡፡ ይልቁን ሁለቱን ክለቦች ብቻ ሳይሆን ዴቪድ ሞይስ እና በወቅቱ ሲቲ አሰልጣኝ የነበረውን ማርክ ሂዩዝ ለግጭት ዳርጓል፡፡ በመሆኑም ሲቲ ለተከላካዩ ዝውውር ከፍተኛ የሚባል 24 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ተገዷል፡፡ አሁንም ሞይስ ከአራት ዓመት በፊት ከዊጋን ላይ በ6 ሚሊዮን ፓውንድ ካስፈረሙት የ26 ዓመቱ ቤይንስ ከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ ይጠብቃሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሲቲ ባለፈው ክረምት የፕሪሚይ ሊግ ልምድ ለሌለው የ25 ዓመቱ ሰርቢያዊ አሌክሳንደር ኮላሮቭ ዝውውር ሰላዚዮ 16 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣቱን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ ሲቲ በውሰት ለዌስትሀም የሰጠውን ዌይን ብሪጅ እንደሚሸጠው እርግጠኛ በመሆኑ ቤይንስን ለተተኪነት አጭቶታል፡፡

Previous Story

ዳልግሊሽ የዝውውር በጀቱን በጥንቃቄ ለመጠቀም አስቧል

Next Story

The world's enduring dictators: Meles Zenawi, Ethiopia

Go toTop