ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
(የካቲት 25፣ 2017) March 4, 2025
ባለፈው ቅዳሜ በፈረንጆች አቆጣጠር በ01.03.2025 ዓ.ም እናቶቻችንና አባቶቻችን በአደዋ ላይ ከ129 ዓ.ም በፊት በወራሪውና አገራችንን የቅኝ ግዛት ሊያደርጋት በፈለገው የኢጣሊያን ኢምፔሬያሊስት ኃይል ላይ የተቀዳጁትን ድል አስመልክቶ በውጭ አገርም በተለያዩ ከተማዎች ሆነ በአገራችን ውስጥም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የአደዋን በዓል እንደገና ስናከብር ባለፉት 50 ዓመታት ህዝባችንና አገራችን ያሳለፉትን መራራ ሁኔታ ከፊታችን ድቅን እያለ “እንዴት እንደዚህ ሊሆን ቻለ” ? እያልን ራሳችንን በመጠየቅ መንፈሳችንን ያስጨንቀናል። በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት ህዝባችን ያሳለፈው፣ አሁንም እየኖረ ያለውና ሙሉ ነፃነቱን እንዲገፈፍ ያደረገውን እጅግ አሰቃቂ አገዛዝ ስናወጣና ስናወርድ ይህንን በዓል በተደበላለቀ ስሜት ነው ያከበርነው። በአንድ በኩል እናቶቻችንና አባቶቻችን በኢጣሊያን ላይ የተቀዳጁትን ድል ሲያኮራንና በሄራዊ አገር ለመመስረትም የወሰዱትን የተለያዩ እርምጃዎችን ስናደንቅ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ድልና በአንድ አገር ውስጥ በነፃነት መኖርን እንደዋጋ ባለመቁጠርና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆንና የተለያዩ ሰበቦችን በመፈለግ በመንግስት መኪና ላይ የተቀመጡትም ሆነ በነፃነት ስም የማያስፈልግና በከፈቱት ህዝብን ጨራሽ ጦርነት የተነሳ ቁጥራቸው የማይታወቅ ወገኖቻችን በመገደላቸው በጣም አዝነናል፤ ብዙዎችም ተሰደዋል፤ ከቀያቸውም በመፈናቀል በየሜዳው በመበታተን በተደራጀ መልክ እንደማህበረሰብ እንዳይኖሩ ለመደረግ የበቁት ትክክለኛ ቁጥራቸውን ለማግኘት ያስቸግራል። ይሁንና በግምት ከቀያቸው የተፈናቀሉት ወደ ሁለት ሚሊዮን ሲጠጋ፣ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል። እነዚህ ሁሉ እ-ሰብአዊ ድርጊቶች በመደመር ጭንቅላታችንን ረብሸውታል። ይህ ሁሉ ግፍ የተፈጸመውና የሚፈጸመው ደግሞ በዚያች አገር ውስጥ በተወለዱ፣ ባደጉና በተማሩ ጥቂት ኤሊት ነን በሚሉ ሰዎችና የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን አወቃቀር አስቸጋሪነት በሚገባ ባልተረዱና ለመረዳትም በማይጥሩ ኢትዮጵያውን ሰዎች አማካይነት ነው። በዚህ የተደበላለቀ ስሜት ስናከብር ሁልጊዜ በጭንቅላታችን ውስጥ የሚብላላው ጥያቄም ሆነ ነገር ለመሆኑ እናቶቻችንና አባቶቻችን በተቀዳጁት ድል ደስታ መሰማቱ ብቻ ሳይሆን ዋናና ተከታታይ የሆነው የዚህ ድል መልዕክት ምንድነው? የመጨረሻ መጨረሻም ዋና ዓላማውስ ምንድነው? የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው መነሳትና መመለስም ያለባቸው ጥያቄዎች። እነዚህ ጥያቄዎች ከጭንቅላት አልፈው በሃሳብ ደረጃ ወደ ውጭ በመውጣት በዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ አስተሳሰብ ተወያይተን ያወቅንበት ጊዜ አልነበረም። በአደዋ ላይ የተገኘውን ድል አስመልክቶ በየዓመቱ በሚከበረው በዓል ላይም ይህንን አስመልክቶ በስነስርዓት ለመወያየትና ትንተናም ለመስጠትና በጭንቅላትም ውስጥ ለማስቀረጽ የተቻለበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። በሌላ ወገን ግን በአደዋ ላይ የተገኘውን ድልና እንዴትስ ተገኘ በሚለው ላይ በጣም አጥጋቢ ጥናቶች ቀርበዋል፤ በቪዲዮም መልክ ተቀርጸው ታይተዋል። እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ የሆኑትን ያህል፣ በሌላው ወገን ግን ከስልጣኔ፣ ሁለ-ገብ ከሆነ ዕድገት አንፃር መቅረብ ያለባቸው ነገሮች ያልቀረቡም የሚል ዕምነት አለኝ። ክዚህም ባሻገር የሰው ልጅ ማለት ምን ማለት ነው? በዚህች ዓለም ላይስ ሲፈጠርስ ተልዕኮው ምንድን ነው? አንድ ሰው ሰው ለመሆኑ የሚገለጸው ምን ምን ዐይነት ባህርዮችን ሲያሟላና በተግባርስ ሲመነዝር ነው? የሰው ልጅ ማንነት የሚገለፀው አንደኛ ሌላውን በመግደል? ወይስ ደግሞ አንዱ ሌላው አዛኝ መሆኑንና በመፈቃቀርና በመተባበር አንድን ስራ በጋራ ሲሰሩና አገርንም በተጠና መልክ በጋራ ሲገነቡ ነው? ባጭሩ ከሰውነቱ ወይም ከቁመናው ባሻገር የሰውን ልጅ በምን መልክ መግለጽ ይቻላል? በተለይም አደዋ ላይ የተቀዳጀነው ድል የኋላ ኋላ ላይ በሰብአዊነት፣ በመተጋገዝ፣ በመፈቃቀር፣ አንደኛው ሌላው በማሰብ ለምን ሊገለጽ አልቻለም? እናቶቻችንና አባቶቻችን በአደዋ ላይ ተጋድሎ ሲያደርጉና ድልም ሲቀዳጁ ያሰቡትና የገመቱት የሰብአዊነትን፣ የመፈቃቀርንና፣ አንደኛው ለሌላው ጠላቱ ሳይሆን እንደወገን በመተያየት በመከባበርና በመተባበር በዚያን ጊዜም የነበረውንና ተከታታዩን ትውልድ ሊያስተናግድ የሚችል ጠንካራ ህብረተሰብ ለመመስረት ነበር። በመሰረቱ የአደዋን በዓል በየዓመቱ ስናከብር እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በማንሳት መወያየት ነበረብን። ዛሬም እንደትላንትናው በእነዚህ መሰረታዊና አንገብጋቢ ነገሮች ላይ አልተወያየንም፤ ፍላጎትም ያለ አይመስለኝም።
እንደሚታወቀው አንድ የውጭ ኃይል አንድን አገር ለመውረር ሲመጣ የጠቅላላውን ህዝብ ነፃነት በመግፈፍ፣ ለብዙ መቶ ዓመታት በተለያዩ መልኮች የሚገለጹና የዳበሩ^ ባህሎችንም በመደምሰስ የብዝበዛ መዋቅሩን በመዘርጋት የጥሬ-ሀብትን እየቆፈሩ ወደ አገሩ ለመውሰድ ነው። በዚያው መጠንም የስልጣኔውን መነሻና መድረሻ በማጥፋት እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ነፃ ሰው እንዲኖር ለማድረግ ሳይሆን ተገዢውና ባርያው በማድረግ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የአፍሪካ አገሮችን ቅኝ-ግዛት ለማድረግ የተነሱት የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት በራሳቸው ምድር ውስጥ ሰፋ ያለ የምሁራዊ እንቅስቃሴ አካሂደዋል። በተለይም ከሬናሳንስ ወይም ከመንፈስ ተሃድሶ አንስቶ እስከ ኢንላይተንሜንት ድረስ የተካሄደውን የጭንቅላት ስራና የገዢ መደቦችንም መንፈስ በመግራት አርቆ አሳቢ እንዲሆኑ ለማድረግ የተደረገውን ትግል ስንመለከት በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡ አገዛዞች የዚህን ሁሉ የምሁራዊ እንቅስቃሴ ትርጉም በመረዳት ብርሃኑንም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲንፀባረቅ ለማድረግ መጣር ነበረባቸው። በመሰረቱም ሊበራሊዝም፣ በህግ የበላይነት መተዳደርን፣ በደንብ የተዋቀረና ሀብትን ፈጣሪ የሆነን የገበያ ኢኮኖሚን የሚጠላ ማንም አገር ወይም ህዝብ የለም። በእነዚህና በሌሎች እንደተፈጥሮ ሳይንስ በመሳሰሉት ዕውቀቶች አማካይነት ነው ማንኛውም አገር ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በመላቀቅ በሰላምና በነፃነት ለመኖር የሚችለው። ይህንን በሚገባ ከጭንቅላታቸው ጋር ያላዋሃዱትና ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያልተላቀቁት የምዕራብ አውሮፓ መሪዎች፣ በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ብቅ ብቅ ያሉት የካፒታሊስት አገሮች መንግስታትና ካፒታሊስቶችም ጭምር የአፍሪካን ህዝብ ወደ ኋላ የቀረ አስመስለው በመገመት፣ አንዳንዶች መሪዎችን በማታለል፣ እንደኛ የመሰለውን አገር ደግሞ በቀጥታ በመውረር የቅኝ ገዢ ለማድረግ ጥረዋል። በእናቶቻችንና በአባቶቻችን ከፍተኛ ተጋድሎ በአገራችን ላይ የተደረገው የቀጥታ ወረራ ቢከሽፍምና የመጨረሻ መጨረሻም ድል ብንቀዳጅም፣ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ለብዙ ዓመታት በቅኝ ግዛት ስር በመማቀቅ በዕድገት እንዳይራመዱ ተደርገዋል። ከቅኝ-ግዛት በፊት የነበራቸው የስራ-ክፍፍል፣ የገበያ ዕድገትና መንግስታዊ አወቃቀር እንዳለ በመፍረስ በቅኝ-ግዛት ስር እንዲወድቁ የተደረጉት የአፍሪካ አገሮች የኋሊት ጉዞ እንዲያደርጉ ተገደዋል። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ይህ ዐይነቱ የቀጥታ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ወደ እጅ አዙር የቅኝ-ግዛት አስተዳደር በመለወጥ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑ ልዩ ልዩ መሰናክሎች ስለተተከሉባቸው ያላቸውን የተትረፈረፈ ሀብት አውጥተው በመጠቀም ከድህነት እንዳይላቀቁ ለመሆን በቅተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም በተንሰራፋው የብዝበዛ ሰንሰለትና ኢ-ሳይንሳዊ በሆነና የተሟላ ሀብትን የማይፈጥር የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተደጋጋሚ ተግባራዊ በማድረግ በልዩ ልዩ የሚገለጹ ቀውሶች ውስጥ በመግባት አገሮቻቸውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ እንዳይገነቡ ለመደረግ በቅተዋል። ከተማዎችንና መንደሮችን በስነ-ስርዓት በመገንባት ወደ ውስጥ ያተኮረ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ እንዳይገነቡ ተደርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ያሏቸውን የሰው ኃይልና የጥሬ-ሀብት ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ የሰለጠኑ ተቋማት እንዳይገነቡ ታግደዋል። አንዳንድ የአፍሪካ አገር መሪዎች ራሳቸው በፈለጋቸውና ለህዝባቸው በሚስማማ መልክ አገሮቻቸውን ለማዋቀርና ህዝባቸውን ሊመግብ የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት ሲነሱ በሴአይኤና በተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ የስለላ ድርጅቶች በመገልበጥና መሪዎችም በመገደል በአንፃሩ ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አሽከር ለመሆን በፈለጉና በተዘጋጁ ሰዎች ተተክተዋል። ፓትሪስ ሉብምባ በመገደል በሴሴኬ ሞቡቱ ተተክቷል። ሞቡቱም ካገለገለና እንደ ሎሚ ተሟጦ ከተጣለ በኋላ ኮንጎ ዛየር እስካሁን ድረስ ሰላም ሰፍኖባት በፍጹም አያውቅም። በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ በነፃነት ስም የሚያወናብዱ ኃይሎች አገሪቱን የጦርነት አውድማ በማድረግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዲገደልና እንዲሰደድ ለመደረግ በቅቷል። ይህ ሁሉ ሴራ የሚያረጋግጠው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ የጥቁር ህዝብ በምንም ዐይነት በሰላም እንዳይኖር ነው የሚፈልጉት። የተሟላ ሰላም የሌለው ህዝብና አገር ደግሞ ጤናማ አገርና ህብረተሰብ ለመገንባት በፍጹም አይችልም።
ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ይህ ሁኔታ ባይፈጠርምና በመጀመሪያው የአፄ ምኒልክ አገዛዝ ዘመናት ለብሄራዊ አገር መመስረት አንዳንድ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም እነዚህና የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን በዘመናዊነት ስም ተግባራዊ የሆኑት የጥገና ለውጦች ጠቅላላውን ህዝብ ከድህነት ሊያላቅቁት በፍጹም አልቻሉም። መንደሮችና ከተማዎችም በስርዓት ሊገነቡና የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ እንዲለውጡ ለማድረግ አልተቻለም። በተጨማሪም የሰለጠኑ ልዩ ልዩ መንግስታዊ ተቋማትም ለመገንባት ባለመቻላቸው በየቦታው ተትረፍርፎ የሚገኘውን ሀብት በማውጣት ለጠቀሚታ ወይም ለፍጆታ ለማድረግ በፍጹም አልተቻለም። አንድ ህዝብ ሰው መሆኑን የሚገነዘበውና ጭንቅላቱም ክፍት በመሆን ፈጣሪ ለመሆን የሚችለው ከተማዎች በስርዓት ሲገነቡ፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎች ሲያብቡና፣ የንግድ እንቅስቃሴም ሲዳብር ብቻ ነው። የልጣኔም ታሪክ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። አንድ ህዝብ ለዝንተ-ዓለም በእርሻ መስክና በጥሬ-ሀብት ማውጣት ላይ ብቻ ከተሰማራና የኑሮውንም ፍልስፍና በእነዚህ ነገሮች ላይ ካደረገ ሰፋ ባለመልክ ሊያስብ አይችልም። በዚህ ላይ ደግሞ የህዝቡን መንፈስ የሚያነቁ፣ ማንነቱን እንዲያውቅ የሚያደርጉ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ካልተዘረጉ አንድ ህዝብ አሳቢና ፈጣሪ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ስለሆነም በአፄ ምኒልክም ሆነ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመናት ለተወሰነ ዕድገት የሚያመቹ ልዩ ልዩ ነገሮች ተግባራዊ ቢሆኑም እነዚህ የጥገና ለውጦች ግን ወስጠ-ኃይላቸው ደካማ ስለነበረ ጠቅላላውን ህዝባችንን ሊያንቀሳቅሰውና አገሩን በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ በፍጹም አላስቻሉትም። በተለያዩ ጊዜያት ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ላይ ለማሳሰብ ወይም ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት በአንድ አገር ውስጥ የሚደረግ መሰረታዊ ለውጥ ሁል-ጊዜ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የሚደገፍና፣ ይህ በመቀጣጠል ብዙ ምሁሮችን ሲይዝ በአገዛዞች ላይ ግፊት ሲፈጠር በዚያን ጊዜ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። ከአውሮፓ ታሪክ ውስጥ በተለይም ከጀርመንም ሆነ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ የለውጥና የዘመናዊነት ሂደት ልንማር የምንችለው ይህንን ሀቅ ነው። በጀርመን ምድር የተደረገው መሰረታዊ ለውጥ፣ ካለ ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ካለሁለቱ ወድንማማቾች አሌክሳንደር ሁምቦልድትና ቪልሄልም ሁምቦልት፣ ካለሺለርና ጎተ…ወዘተ… ወዘተ በፍጹም ሊታሰቡም አይችሉም ነበር። እነዚህ ጥቂት ምሁራን ጭንቅላታቸውን ክፍት በማድረግ ራሳቸውን በማስጨነቅና የስልጣኔንም ትርጉም ለመረዳት ቀን ከሌሊት ለመስራትና ለማስተማር ባይችሉ ኖሮ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማቲማቲክስ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የኢንጂነሪንግ ዕውቀቶች ባልተፈጠሩና በጣም ኋላ-ቀር የነበረውን ህዝባቸውን ኑሮውን በመለወጥ አሳቢና ፈጣሪ እንዲሆን ለማድረግ ባልተቻለ ነበር። እነዚህ የተዋቁ ፈላስፋዎችና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችም ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተከፈቱትንና የተስፋፉትን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመግባትና በመማር፣ እንዲሁም በተቋቋሙት ቤተ-መጻህፍቶች የተደረደሩ መጽሀፎችን በማንበብና በተሻለ መልክ በማስፋፋት ነው የጠለቀ ዕውቀትን በማግኘት ህብረተሰብአቸውን ለመለወጥ የቻሉት። በሌላ አነጋገር፣ በአውሮፓ ምድር ለስልጣኔና ለተሻለ ኑር፣ እንዲሁም እንደ ህብረ-ብሄር ለመቆም የተጀመረው ስራ ከእኛው ጋር ሲወዳደር የሶስት መቶና የአራት መቶ ዓመት ልዩነት አለው። በአውሮፓው ምድር የመጀመሪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በጣሊያን ምድር በ14ኛው ክፍለ-ዘመን የተዘረጉ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአውሮፓ ምድር በልዩ ልዩ ከተማዎች ዩኒቨርሲቲዎችና ቤተመጻህፍቶች ተቋቁመው አዳዲስ አሳቢና ፈጣሪ የሆነ ትውልድን ለማፍራት ችለዋል። በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ብቻ በጀርመን ምድር ብቻ ወደ አርባ የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች ሲኖሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። ልዩነቱንና ተፅዕኖውን ለመረዳት ከባድ አይሆንም። ባጭሩ ለማለት የምፈልገው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በአገራችን ምድር አገራችንን እንደህብረ-ብሄር በዘመናዊነት መሰረት ለመገንባት የተጀመረው በጣም ዘግይቶ ነበር ማለት ይቻላል። ስለሆነም አፄ ምንሊክም ሆነ፣ የኋላ ላይ ደግሞ አፄ ኃይለስላሴ ዘመናዊነትን ሲያስገቡ ሀ ብለው መጀመር ነበረባቸው። በዚያው መጠንም በቀደሙና ዕውቀትን ጥንታዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማስፋፋት በማይፈልጉ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ለመታለልና ትክክለኛውን የስልጣኔ መንገድ ለማግኝት አስቸጋሪ እንደሚሆን መረዳቱ ከባድ አይሆንም። በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ጭንቅላትን በሚሸፍንና የትክክለኛውን የስልጣኔ ፈለግ ለማስያዝ የማይችለው ኢምፔሪሲስታዊ የሚባለው ትምህርት በመስፋፋቱ በተለይም እንደኛ የመሰሉ አገሮች በተሳሳተ ትምህርትና ለስልጣኔ በማይመቸውና ትክክለኛ በሆነው መልክ የተዋቀረውንና ያለውን የዕውቀት ልዩነት ልመረዳት እንዳይችሉ ለመደረግ በቁ። ይህ ዐይነቱ የዕውቀት መዛነፍም በተለይም በኢኮኖሚክስ ላይ ያየለና አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባት ሳይሆን ንጹህ በንጹህ ወደ ገበያ መድረክነት በመለወጥ የሰው ልጅ እየተንቀዠቀዠ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። የዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚክስ ትምህርት አፍላቂዎች አንዳንድ የአውስትርያ ምሁራን ሲሆኑ፣ በአነሳሳቸውም የካፒታሊዝምን ዕድገት ከታች ወደ ላይ በመመርመር ሳይሆን በጊዜው የነበረውን ክስተት በመውሰድና በማስፋፋት ነው። ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ይህ ዐይነቱ ኒዎ-ክላሲካል የሚባለው የኢኮኖሚክስ ትምህርት በአሜሪካና በተቀሩ የአውሮፓ አገሮች በመስፋፋት ከህብረተሰብ አወቃቀርና ከታሪክ አንፃር የተዘጋጀውን ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቸውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት እየገፈተረው በመምጣት የበላይነትን ለመቀዳጀት ቻለ። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚክስ ትምህርትም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ጭንቅላት በመሸፈንና በማቴሪያል ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ አንድን አገርና ህዝብ ተራ ተበዝባዥ እንዲሆኑ ማድረግ በቃ። በታሪካዊ የኢኮኖሚክስ ዕውቀት፣ ኢኮኖሚክስ ከፍልስፍና፣ ከተፈጥሮ ሳይንስና ከማቲማቲስ፣ ከሳንይስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ከባህላዊ ግንባታ ተነጥሎ በፍጹም አይታይም። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ሁለንታዊ በሆነ መልክ ለማሰብ የሚያስችል ኃይል ስላለውና፣ ማንኛውም ነገር ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ስለሚገነዘብ ነው። በአንፃሩ የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ በቁንፅል መልክ እንድናስብ የሚያደርግና ህብረተሰብና ሰው ምን ማለት እንደሆኑ ሊያስገነዝበን የሚችል አይደለም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ በተሳሳተ መልክ የተዋቀረው የኢኮኖሚክስ ትምህርት የስውን መንፈስ በተሳሳተ መልክ የሚቀርጽና አታላይ የሚያደርግ ነው። በዚያው መጠንም አንድን አገርና ህዝብ የሚያታለልና ክሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ የሚያደረግ በረቀቀ መልክ የተዘጋጀና ተግባራዊም የሚሆን ነው። ለዚህም ነው እንደኛ ባለው አገር ውስጥ የማያቋርጥ ጦርነት የሚካሄደውና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ፍዳውን እያየ እንዲኖር የተገደደው። ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚክስ ትምህርት በራሱ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ ኤሊቲን ሲያፈራ፣ በዚያው መጠንም ድሀነትና ኋላ-ቀርነት እንዲስፋፉና ስር እንዲሰዱ ለማድረግ ተችሏል።
ከዚህ ስንነሳ በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታቸው የተሸፈነ በጥቂት ኤሊት ነን ባዮች የሚካሄደው ጦርነት ለተሟላ ዕድገት፣ ለሰላም፣ ተከባብሮ ለመኖርና አገርን በሳይንስና በቴክኖሎጂ መሰረት ላይ ጥበባዊ በሆነ መልክ በመገንባት ለተከታታዩ ትውልድ እንዳይተላለፍ ከፍተኛ ዕንቅፋት ሊፈጥር ችሏል። ያለፉትን 50 ዓመታት ታሪካችንን ስንመለከት በአብዛኛው መልኩ የሚደረገው ትግል አገርን በፀና መሰረት ላይ ለመገንባትና ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማስወገድ የተከበረች አገር መገንባት ሳይሆን ዕልክ ውስጥ በመግባትና ይህንን ዐይነቱን የአልበገርም-ባይነት ባህርይ እንደ ቫይረስ ከአንዱ ትውልድ ወደሌላው በማስፋፋትና በማስተላለፍ የስልጣኔው መንገድ እንዲጨልም ለማድረግ ተችሏል። በዚህ ዐይነቱ ዕልክ አስጨራሽ ጦርነትና ግብግብ የስንት ወጣት ህይወት ተቀጠፈ። ስንቱስ በመሰደድና በየበረሃው በመንገላታት ህይወቱ በአውሬ እንዲቀጠፍ ተደረገ። የአብዮትን ትርጉም ባልተረዱ አብዮተኞች ነን ባዮች ስንቶችስ እናቶቻችንና አባቶቻችን በበዝባዥነት በመፈረጅና ወደ ድህነት በመገፍተር የመጨረሻ መጨረሻ ማንም ሳይጦራቸው እንዲሞቱ ተደረጉ። ስንትስ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስሮች በመፈራረስ አንደኛው ለሌላኛው እንዳያስብ ተደረገ። ባጭሩ ባለፉት ሃምሳ ዓመታትና ዛሬም በአገራችን ምድር የሚካሄደው ህዝብን አዋካቢና ገዳይ ጦርነት ጭንቅላታቸው በቂም በቀል መርዝ በናሉና በጥራዝ-ነጠቅ ዕውቀትም ጭንቅላታቸው በተመረዘ ኃይሎች አማካይነት ነው። በተለያየ መልክ ጭንቅላታቸው በደንብ ባልተኮተኮተና ባልተገራ ጥቂት ሰዎች የሚካሄደው አገርንና ታሪክን አፍራሽ ጦርነት በቀላሉ መቋጫ የሚገኝለት አይደለም። በተለይም ከትግራይና ከኦሮሞ የተውጣቱ “ኤሊቶች” በመፈራረቅ በሰፊው ህዝባችን ላይ የሚያካሂዱት ጦርነት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ መቆም ያለበትና እነዚህም ኃይሎች ከስልጣን አካባቢ መወገድ ያለባቸውና በማንኛውም ተቋማት ውስጥ ገብተው እንዳይሰሩ መታገድ ያለባቸው ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን በፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ በመሆን ተገቢውንና ፍትሃዊ የሆነ ፍርድን ማግኘት አለባቸው። እንደ ንጹህ ዜጋ አሁንም በፖለቲካ ስም የሚያወናብዱበት ምንም ምክንያት የለም። ፖለቲካ የሚባለው ነገር ቅዱሳዊ ሃሳብ ስለሆነ የማንም ወንጀለኛ መሳሪያ በመሆን የአንድ አገር ህዝብ ዘለዓለሙን ፍዳውን እያየ መኖር የለበትም። ማንኛውም ግለሰብ ነፃ ሆኖ የተፈጠረ በመሆኑ በነፃነት መኖሩም ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው። አንዱ በሌላኛው ላይ የመጨፈርና የማሰቃየት መብት የለውም። የመንግስትም ዋናው ተግባር የእያንዳንዱን ግለሰብ ነፃነትና መብት ማስከብር ሲሆን፣ በአገሩ ውስጥ ደግሞ የፈለገው ቦታ በመኖር ማንኑትን ሊገልጽ በሚችልበት ሙያ በመሰማራት ቤተሰቡንና የሚኖርበትም ማህበረሰብ ለማገልገል ነእንዲችል አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። አንድ ህዝብ ለዝንተ-ዓልም በጋጠ ወጤዎች እየተሰቃየና እየተገደለ የመኖሩ ጉዳይ እንደ ተፈጥሮ ህግ መቆጠር የለበትም። እነዚህን ኃይሎችና ከውጭ ሆኖ የሚጠመዝዛቸውን ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል ከአገራችን ምድር እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የአደዋ መልዕክትና ምንነት ሙሉ በሙሉ ሊተገበሩ የሚችሉት።
የአደዋ ዋናው መልዕክትና ዓላማውም ህዝባችን ነፃነትን ከተቀዳጀ በኋላ በተለያየ መልክ በተሸረበ ሴራ ባርያ ሆኖ ለዝንተ-ዓለሙ ፍዳውን እያየ እንዲኖር ማድረግ አይደለም። እናቶቻችንና አባቶቻችን አደዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ዋናው መልዕክትና ዓላማው ሰብአዊነትን፣ ርሁርህነትን፣ አርቆ አሳቢነትን በማስፋፋትና በዚህ መንፈስ በመታነፅ ለሁሉም የምትሆን የተከበረች አገር መገንባት ነው። ለዚህ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ በጣም ወሳኝ ነው። ይህ ዐይነት ሁኔታ በሌለበት አገር አንድ ህዝብ ነፃነቱን አስከብሮና ተከብሮ ሊኖር በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅና ለዝንተ-ዓለሙ የውጭ ኃይሎች አሸከርና እነሱን በመለመንና በመለማመጥ እንዲኖር አጥብቀው የሚሰሩና በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ በተደረጃም ሆነ ባልተደራጀ መልክ የሚሰሩ ቁጥራቸው የማይናቅ ኢትዮጵያውያን መስል ኃይሎች አሉ። ለብሄረሰብአችን መብትና ነፃነት እንታገላለን ከሚሉት ጎጠኛ ኃይሎች ባሻገር የኢትዮጵያን ህዝብ አንቀው በመያዝ እንደነቀርሳ በሽታ የሚሰረስሩት በኤሊት ስም የሚነግዱና በምንም ዐይነት የዲሞክራሲ ስብዕናና ተልዕኮ የሌላቸው ኃይሎች ከፍተኛ ወንጀል ሰርተዋል፤ በመስራትም ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ኃይሎች ትላልቅ ሰዎች በመምሰልና ወጣቱን በማታለል ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ለብሄራዊ ነፃነት የሚደረገውን ትግል ጠንቅቆ እንዳያውቅ ለማድረግ በቅተዋል። እንደሚታወቀው የአደዋ መልዕክትና ዋና ዓላማ የተሟላ መገለጽን(Enlightenment) ተግባራዊ ማድረግ ነው። መገለጽ ማለት ደግሞ ጥያቄ መጠየቅ፣ ራስን ማወቅ፣ አርቆ በማሰብ ኃይል መመራት፣ ከራስም ባሻገር ለሌላው በማሰብ ሰብአዊነት ያለበት ማህበረሰብ መመስረት ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የተገለጸለትና በተገለጸላቸው ሰዎች የተያዘና የሚመራ የመንግስት መኪናና ልዩ ልዩ መንግስታዊ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ አገር በእርግጥም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትና ተከታታይነት ሊኖረው የሚችልና ህዝቡን ሊያስተናግድ የሚችል የተሟላና በብዙ መልክ የሚገለጽ ኢኮኖሚ ሊገነባ የሚችለው። በአንፃሩ በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ የሚሯሯጡና የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም የሚለማመጡ፣ ወይም ደግሞ አሜሪካ ሆይ “በኢትዮጵያ ውስጥ ስትራቴጂያዊ ጥቅም አለህ” የሚሉ ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባና ህዝባችንም የተሟላ ነፃነትን እንዳይቀዳጅ የሚታገሉ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎችም የዓለም አቀፍን ስም በተከናነቡ፣ ይሁንና ደግሞ በተለይም በኢትዮጵያና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ድህነትንና ጥገኝነትን በሚያስፋፉ ተቋማት ስር ሲሰሩ የነበሩና አሁንም ካለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ለመኖር አንችልም ብለው ቃል ኪዳን የገቡ ናቸው። ስለሆነም በኢትዮጵያ ምድር የአደዋን ተልዕኮና ዋና ዓላማ ለማሳካት ከተፈለገ ትክክለኛውን የሳይንሱንና የፍልስፍናውን መንገድ መከተል ያስፈልጋል። በፖለቲካ ስም የሚነግዱትን፣ ይሁንና ደግሞ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያላቸውን ኃይሎች በሚገባ ጠንቅቆ ማወቅ ያፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አፄ ምኒልክና ጀግኖቻቸው አደዋ ላይ የተቀዳጁት ድልና ተልዕኮው በተሟላ መልክ ሊተገበሩ የሚችሉት። መልካም ግንዛቤ!!
[email protected]
www.fekadubekele.com