የምኒልክ ሐውልት ክስ* – ከሠረቀ ብርሃን

የካቲት 2016 ዓ.ም.

*መጀመሪያ በ 2001 ዓ/ም የወያኔውን አገዛዝ ፀረ-ኢትዮጵያነት ለማሳየት ተፅፎ፣ በዚህ ባንዳ ቡድን የተጀመረው አገር የማጥፋትና ታሪክ የመደለዝ ተግባር በብልፅግና ዘመን እንዴት እንደቀጠለና እንደተባባሰ ለማመልከት ተከልሶ የቀረበ፡፡

አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት የሃገሪቱን አመራር ለአደጋ አጋልጠህ የሞትና የአካል ጉዳት አድርሰሃል የሚል ክስ ተመስርቶበት ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑ ታወቀ፡፡  ክሱ የተመሰረተው ባንድ የወያኔ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን መሆኑ ሲወራ ከሰነበተ በኋላ፣ በቅርቡ ከሳሹ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡  ይህን ክስ የተለየ የሚያደርገው፣ ከዚህ በፊት ሐውልቱ ላይ በርካታ ክሶች ቀርበው ደፍሮ የሚነካካው ጎበዝ በመታጣቱ ሳይሳካ ቀርቶ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሞት አግኝተው ፊት ለፊት ሊጋፈጡት መወሰናቸው ነው፡፡  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ የተሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንቦት 20/ 2000 ዓ/ም ከምርቃና በኋላ ለጨብሲ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ አሜሪካ ለመልካም አስተዳደራቸው ማጠናከሪያ በሸለመቻቸው ብረት ለበስ ታንክ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚዘዋወሩበት ወቅት ዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት አካባቢ ሲደርሱ ፈረሰኛው ምኒልክ ፊት ለፊታቸው በመጋረጥ ታንካቸውን ለማሳለፍ በመከልከሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደፊት ለማለፍ ባደረጉት ጥረት ሐውልቱ ቦታውን አውቆ መንገድ ሊለቅላቸው ባለመፍቀዱ ፊት ለፊት ተላትመው በሰው ነፍስና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡  ሐውልቱ በዚህ ሃፍረት የለሽ ግትርነቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታንክና መሠረቱ ሲላተሙ ባደረሰው ጉዳት በስሩ አሰባስቦ ላቆያቸው አሥራ-ሶስት ጎዳና ተዳዳሪዎች ከባድ የመቁሰል ጉዳትና ለአንድ መንገደኛ ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ሲሆን፣ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተወዳጅ ታንክ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን አድርጓል፡፡

በአደጋው የታጋዮች አምላክ እንደጦር በሾለው ጭራው ጠብቋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የደረሰ ከባድ ጉዳት ባይኖርም፣ ሁለት ቦታ ተሰንጥቆ የተፈጠረው ምላሳቸው ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ ረዘም እንዲል ምክንያት ሆኗል፡፡  ይህን አደጋ በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ለወደርየለው ገምድል አንደኛ ችሎት ሐውልቱ ላይ ክስ መስርተዋል፡፡

ወያኔያዊ ዲሞክራሲን ሃገሪቱ ላይ ለማስፋፋት በሚያደርጉት ጥረትም የፍርድ ሂደቱን ሕዝብ በግልፅ መከታተል እንዲችል በማድረግ የወያኔን ገምድል ሕግ የበላይነት፣ የሳቸውንም አስተዳደር አስፈሪነት፣ ፍትሕ አልባነት፣ አስመሳይነትና መልቲነት ለማሳወቅ አጋጣሚውን ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ለዳኛው በመግለፅ፣ ጉዳዩ በአስመሳይ የወያኔ ዳኞች ታይቶ፣ አጥፊው ማን እንደሆነ በግልፅ ስለታወቀ፣ በወያኔ ፍታብሔር-ገምድል ሕግ መሰረት ቅጣት እንዲቀበል መመሪያ ሰጥተዋል፡፡  በተጨማሪም የሳቸውንና የባልደረቦቻቸውን የአስተዳደር ጠባብነት፣ አይን ያወጣ አድሎአዊነት፣ ሁሉን እናውቃለን ባይነትና ትጉህ ባንዳነት ኢትዮጵያውያን በደንብ ስላልገባቸው በቅጡ እንዲረዱት፣ ፈረንጆች ደግሞ ላይ ላዩን መጋለብ የሚወዱ በመሆናቸውና ጥቅማቸው ከምንም ነገር እንደሚበልጥባቸው ስለተረዱ አንዲደናገራቸው ችሎቱ በግልፅ አደባባይ እንዲከናወን ማንንም ሳያማክሩ እንደ ሁልጊዜው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ራሳቸው መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምኒልክ ሐውልት ላይ ክስ የመሰረቱበትን ምክንያት ከዚህ እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፤

1ኛ/ ሀገር ለማጥፋት ስቅለበለብ ከፊቴ በመጋረጥ መንገዱን ዘግቶ ለግጭት ስለዳረገኝ፣

2ኛ/ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር አሁን ባለችበት ሁኔታ ለማቆየት የተጣለውን መሰረት በማስቀመጥ የመበተን፣ የማጋጨትና የማተራመስ አላማዬን ያሰናከለ በመሆኑ፣

3ኛ/ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በማደርገው ያላሰለሰ ጥረት ሕዝብን በማነቃቃትና የተስፋ ጭላንጭል በመሆን ለአጥፊ ጥረቴ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ በመገኘቱ፣

4ኛ/  ፓስታ በሹካ እየበላሁ እንቁላል ስገብር ለመኖር የተፈጠረልኝን ጥሩ አጋጣሚ አድዋ ላይ ባጭር ስለቀጨብኝ ከስሼዋለሁ ብለዋል፡፡

የምኒልክ ሐውልት ጠበቃ በበኩሉ ደንበኛዬ አርፈው በቆሙበት ከየት መጣ ሳይባል ለብዙ አመት በሰላም በኖሩበት ቦታ ያልታሰበ ግጭት የደረሰባቸው መሆኑንና በስራቸው አሰባበስበዋቸው የነበሩ ሰዎችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንዝህላልነት ለከባድ መቁሰልና ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡  የቆሰሉትን ሰዎች የጎዳቸው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አይን አልባ ታንክ ነው በማለት ስሞታውን ሲያሰማ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ ደግሞ ሰዎቹ ከወደሰሜን ለቂም በቀል እያጓራ በመጣው ታንክ ከመገጨታቸው በፊት በረሃብ ተጎሳቁለው የደከሙ መሆናቸውንና ሐውልቱ ሥር ተጠልለው አብረው ከመኖር ተበታትነው መሞት አንደሚሻላቸው ከአደጋው በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀውላቸው ነበር ሲል ያስረዳል፡፡  የሐውልቱ ጠበቃ እንደሚለው ከሆነ ግን ተባብረው ታንኩን ለማገድ ሲከላከሉ እንደቆሰሉና ከመሃከላቸው ግንባር ቀደም በመሆን ሲከላከል የነበረው ‹‹ባሕር በር›› በመባል የሚታወቅ ሰው ደግሞ እንደሞተ አስረድቷል፡፡

በአደጋው የሞተው ይህ ሰው ከመሞቱ በፊት ታንኩን ለማስቆም ጥረት ማድረጉን ታዛቢዎች ሲናገሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ እንደሚለው ከሆነ ግን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ አጋር የነበረና ቀደም ብሎ ሐውልቱን ከሳቸው ጋር ተማክሮና ተባብሮ ቦታ ለማስለቀቅ ከተስማማ በኋላ በወላዋይነት ወዲያና ወዲህ ሲልፈሰፈስ ሳያስበው በተፈጠረው ግጭት ለሞት በቅቷል ሲል አሳውቋል፡፡

የምኒልክ ሐውልት ጠበቃ ግን የሰውየው አሟሟት ለየት ያለ ነው በማለት፣ ግለሰቡ የተገደለው ሐውልቴን አላስነካም፣ ከጓደኞቼ አትገንጥሉኝ፣ አንድ ላይ ነን በሚልበት ጊዜ ታንኩ ጊዜ ሳይሰጥና ያሰበውን ሳይናገር ድምፁን አፍኖ እንደጣለው ያስረዳል፡፡

ፍርድ ቤቱ የከሳሽ ተከሳሽን ማስረጃ አጣርቶ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለፈረንጆች ማስመሰያ ከሰማ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማተራመስና የማጋጨት ሥራ ስለሚበዛባቸው የፍርድ ሂደቱ ኃላፊነታቸው ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጥርባቸውና ያሰቡትን ከማድረግ እንዳያውካቸው በማሰብ አስቸኳይ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በሐውልቱ ሥር በዋለው ችሎት የወደር የለው ገምድል ዳኛ በሰጡት ውሳኔ፣ ሐውልቱ ወንጀለኛ መሆኑ በበቂ ማስረጃ ተረጋግጧል በማለት ከዚህ የሚከተለውን ብይን ሰጥተዋል፡፡ በመጀመሪያ ይህን ችሎት ባደባባይ ያደረግነው ላንተ ክብር እንዳልሆነ እንደትረዳው በማለት ሐውልቱን የጎሪጥ እያዩ ከገሰፁ በኋላ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀጥተኛ መንገድ ዘግተህ ሥራቸውን በማስታጎልና አደጋ በማድረስ ለአሥራ ሶስት ሰዎች ከባድ መቁሰልና ለአንድ ሰው መሞት ምክንያት ስለሆንክ አንተነትህን ከሚያመለክቱ ማንኛውም አይነት መረጃዎች ተፍቀህ፣ ለተመልካች ግልፅ እንዳትሆን ዙሪያህን በፎቆች ተጋርደህ፣ ሕዝብ እንዳይኮራብህ ተደብቀህ፣ ሲያዩህ የሌለህ መስለህ፣ ታሪክ እያለህ እንደሌለህ አንገትህን ደፍተህ ደብዛህን ለማጥፋት የሚያመች ጊዜ እስክንፈጥር ድረስ በዚህ ሁኔታ እንደትኖር ተወስኖብሃል ብለዋል፡፡  በተጨማሪም የይግባኝ መብት ለእንዲህ አይነቱ አይን ያወጣ ወንጀል እንደማይሰጡ መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ወያኔ ‹‹ደብዛህን ለማጥፋት የሚያመች ጊዜ አስክንፈጥር ድረስ›› ብላ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ስትንፈራገጥ ከርማ አሁን የራሷ ደብዛ እየጠፋ ነው፡፡  ተቅለስልሶና ሕዝብን አታሎ ሥልጣን የያዘው ቀን የወጣለት ብልፅግና ደግሞ በጎሰኛ አስተምህሮ ራሱን ወጥሮ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ባለው ምኞት የምኒልክን ሐውልት ለማፍረስ ሲግደረደርና የአዲስ አበባን ሕልውና በመፈታተን የታላቋ ኦሮሚያን ቅዠት ለማስፈፀም ሲውተረተር እየታየ ነው፡፡  በተጠናወተው የአእምሮ መዛባት ደዌ፣ የመንፈስ ስብራትና የዝቅተኝነት ቁስል የተነሳ የሚሰቃየው ተማርኩ ባይ ዘውገኛ ክፍል ራሱን የቱን ያህል እንደሚጠላ ከዚህ ክስተት መገንዘብ ይቻላል፡፡  ምኒልክ ያቀናውን አገር እየመሩ የምኒልክን ገድል ማንጓጠጥ፡፡  ምኒልክ የተቀዳጀውን ወሳኝ ድል እያከበሩ ምኒልክን አግልሎ በቦታው ያልነበሩ እንጭጮችን ማግነን በራስ የመተማመን ችግርና እውነትን ላለመቀበል የሚደረግ ያልበሰሉ ሰዎች ግር ግር  ነው፡፡   ሐውልት ለማፍረስ፣ ሕዝብን ለመዋጥና ታሪክን ለመደለዝ ከመሞከር ይልቅ የሁሉንም አስተዋፅኦ በመገንዘብ ሃገሪቱ ላይ የተመዘገቡ ድሎችም ሆኑ በደሎች፣ ቁም ነገሮችም ሆኑ ኪሳራዎች እያንዳንዱ ሕብረተሰብ የሚጋራቸው መሆኑን ማሰብ ይጠቅማል፡፡

እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሰፊ ሃገርና ትንንሽ ሃገራትም በመሃከላቸው ልዩነት አላቸው፡፡  ይህን ያህል አገር በመልክኣ ምድር፣ በአየር ንብረት፣ ባሰፋፈርና በሌሎች መለኪያዎች ስብጠርጥር ባለበት ሁኔታ ሁሉንም ህብረተሰብ ላንድ አላማ አሰልፎ ዉጤት ማምጣት መቻል ትልቅ ስብእና ይጠይቃል፡፡  ይህን አለማድነቅ፣ በዚህ ገድል መከፋትና የተሰራውን ላጥፋ፣ ታሪክ እያዛባሁ የሕዝብን ሰላም ላደፍርስ  ማለት ሕመምተኝነት ነው፡፡

እሰቲ አኛን ባትሰሙን ሌሎች ያሉትን አንብቡት፡

 

…But the core message of Adwa was clear. It was a national epic, the founding event in the modern life of the nation.  The stately northward march of Menlik and Taytu not only consolidated their rule but called upon the Ethiopian people – Tigrians, Shoans, Oromo, Wolayta, and others – to set aside their differences and, in recognizing a common nationhood.  Nations, if they are to endure, are defined not by religion, ethnicity, or race but by the scale at which freedom can reliably be defended.  Only on the scale of Ethiopia itself could resistance have succeeded. 

Jonas,  Raymond 2011  The Battle of Adwa; African Victory in the Age of Empire. The Belknap Press of Harvard University Press.  Cambridge, Massachusetts. London, England.

The victory of Adwa was a great achievement for Ethiopia, since its emperor had been able successfully to mobilize men and resources throughout his vast domains to overcome a powerful enemy.  The subsequent diplomacy revealed Menlik as an astute and wily statesman; his carefully designed, non committal foreign policy consolidated his battlefield success, safeguarded Ethiopia’s position on all sides, and won territorial and economic concessions from his powerful neighbors.  Ethiopia’s improved international standing and recognition permitted Menlik to embark on a period of nation building. 

Marcus, Harold G. 1994 University of California Press.  Berkeley and Los Angeles, California

ከላይ በተጠቀሰው መልክ በአድናቆትና በአድምሞ የተገለፀን ገድል ሰበብ እየፈለጉ ለማራከስ፣ ለማደብዘዝ፣ ለማጣጣልና ለመሰረዝ መሞከር ሊመነጭ የሚችለው በምቀኝነት ከተወጠሩ ህሊና ቢስ የአእምሮ ድኩማን ብቻ ነው፡፡ የአያት ቅድም አያቶቻችሁን ትብብራዊ ተጋድሎ ማራከስ መሆኑ ሊገባችሁ እንዳይችል በምቀኝነት ስሜት የተደፈነው፣ እውቀትን ሳይሆን አውዳሚነትን የቀሰመው እእምሯችሁ ሊፈቅድላችሁ አልቻለም ፡፡ በምንም መልክ ብታስቀምጡት አድዋ ሲታወስ ምኒልክና ጣይቱ መታወሳቸውና የገድሉ መሪዎች መሆናቸው መወሳቱ  የማይቀር ነው፡፡  በነሱ አስተባባሪነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ድል አስመዝግቧል፡፡ ይህ ሃቅ በምንም አይነት የማደብዘዝ ጥረት ሊፋቅ የሚችል አይደለም፡፡ ስለአዲስ አበባም ሲታሰብ የሁለቱን ሰዎች አስተዋፅኦና ኢትዮጵያን አንድ በማድረጉ ሂደት ከተማዋን የሁሉም ኢትዮጵያዊ መናኅሪያ ለማድረግ የተጫወቱትን ሚና ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ፣ በቅናት በዝቅተኝነትና በእልህ ስሜት መርገፍገፉን ተውትና የጋራ ውርሳችሁን አክብሩት፡፡ አናከብርም የምትሉ ከሆነ ደግሞ ታሪክ አትከልሱ፡፡ እናንተ ለመጥላት፣ ለማፍረስና ያልነበረ ትርክት ለመፈብረክ ከተነሳሳችሁበት ስሜት በበለጠ ሁኔታ ይህን ታሪክ ለማቆየት ለማስታወስና ማንነቱን ለማደስ ቆርጦ የተነሳ ትውልድ እንዳለ ባትዘነጉ የተሻለ ይሆናል፡፡  ለማፍረስ ሰትልመጠመጡ መፍረስም እንዳለ አትዘንጉ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በአድዋ መንፈስ ተነሳስተን በአብይ አህመድ የሚመራውን የዘረኛ መንግስት እናስወግድ – አቶ መርሻ ዮሴፍና ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

Go toTop