
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
የካቲት 23 ቀን፣ 1888 ዓ.ም የዛሬ 129 ዓመት ፤ የተደራጀ ኃይል ያለውን ፣ የኢጣሊያንን ሠራዊት ፣ የእናት አገሩ መደፈር አንገብግቦት የምኒሊክን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ፣ በአብዛኛው በትርና ጎራዴ ታጥቆ ፣ ከመላው ኢትዮጵያ ተሞ የመጣው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሠራዊት በታላቅ ተጋድሎ አደዋ ላይ አሸንፎታል ።
በዚህ ድል ምኒልክ እና ጣይቱ በመሪነት የሚጠቀሱ ዋንኞቹ መሪዎች ነበሩ ። መሪዎች በአንድ አገር በጎና መጥፎ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም ።
የአገራችንን የኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎችን መቅደላ ፣ ጉንደት ፣ ጉራዕ ፣ ዶጋሊ ፣ መተማ ፣ አደዋ ፣ ኡጋዴን ፣ ኤርትራ ላይ ያላቸውን ታላቅ አበርክቶ ታሪክ ያስታውሰናል ።
የቀደሙትን አባቶቻችንን የዘመናት ተጋድሎ ለታሪክ ትተን ፤ አፄ ቴዎድሮስ ፣ አፄ ዮሐንስ ፣ ዓፄ ምኒልክ አፄ ኃይለሥላሤ ፣ ጓድ መንግስቱ በመሯት ኢትዮጵያ እንኳ ባለ አገሩ ዜጋ በዘውግ ሳይከፋፈል በአንድነት እና በፍቅር ተሳስሮ ፣ ለአገሩ ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ ሚስቱን፣ ልጁን ፣ እናቱን ፣ አባቱን ፣ ወንድሙን ፣ እህቱን እና ዘመድ አዝማዱን ከውርደት ፣ ከባርነት እና ከአሰቃቂ ሞት አድኖል ። እነዚሁንም በመንበረ የአገሩን ዳር ድንበር በደሙ አስከብሯል ። ምንም እንኳን ከአደዋ ድልም በኋላ ፣ “ባህረ ነጋሽን ” ኤርትራ ” በማለት ጣሊያን ቢያስተዳድራትም ቅሉ ።
” ባህረ ነጋሽን ” የዛሬዋን ” ኤርትራ ” እስከ 1876 ዓ/ም ጀግናው ኢትዮጵያዊ ራሥ አሉላ አባ ነጋ ያስተዳድሯት እንደነበር ይታወቃል ። የያኔዋን ” ባህረ ነጋሽ ” የዛሬዋን “ኤርትራን ” አቶ መለሥ በወርቅ ሣህን ላይ በማድረግ ለሥትራቴጂክ ጠላቶቻችን የዛሬ 33 ዓመት እንካችሁ በማለት ፣ የሥልጣናቸው ማደላደያ ቢያደርጓትም ቅሉ ።
( ይህንን ስጦታ አሜሪካኖች እንኳ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ተቃውመውታል ። ቢያንስ በደርድር አሰብን ኢትዮጵያ መያዝ ነበረባት በማለት ። ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ለማልማት ከፍተኛ መዋለ ነዋይ ማፍሰሷ እና ከእርሷ ውጪ የወደብ ተጠቃሚ እንደሌለ ስለተገነዘቡ ነው ፤ ኢትይጵያን ወደብ አልባ ማድረግ ለኤርትራም እንደማይበጅ የተናገሩት ። የኢሣያስ ለሽንፈት ና ለውድቀት የሚዳርግ ጫዎታ እና ስግብግብነት በወቅቱ እንዳልጣማቸው ኸርማን ኮሆን በገደምዳሜ ተናግረው ነበር ። )
ኤርትራን ከእናቷ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሤራ ፣ እጅግ የሚያንገበግብ ፣ ለአገር ፍቅር መሞትን ከንቱ ና የከንቱ ከንቱ የሚያደርግ ታላቅ የቅኝ ገዢዎቻችን ሤራ ነበር ።
( ዛሬም የኤርትራ መንገጠል የንገበግበናል ። ከብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ቃጠሎው አልበረደም ። ለታላቋ ሉአላዊት አገር ኢትዮጵያ የባህር በር ሲሉ ዘራይ ደረስ ና አሉላ አባ ነጋ ከእስትራቴጂክ ጠላቶቻችን ጋር የሰሜኑንን ህዝብ አስተባብረው በጀግንነት ተዋግተዋል ። ጀግኖቾቹ አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰዋል ። ህይወታቸውን ሰጥተዋል ። እነዚህን ኩሩ እና ጀግና ኢትዮጵያዊያንንም የማይረሳ አገር ተረካቢ ትውልድ አገራችን ዛሬም አገሬ አላጣችምና ነው ንዴቱና ቁጭቱ እየበረታ የመጣው ።
በጥቅምና በብልጭልጭ ነገር የማይደለሉ ፣ አገራቸውን ከራሳቸው በፊት የሚያስቀድሙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም አሉ ።
ምዕሪብውያኑ ግን ዛሬም በጥቅም እየደለሉን ፣ ሰውነታችንን ዘንግተን ፣ ሟች መሆናችንን ክደን ፣ በጭፍን ጥላቻ እንድንገዳደል እያደረጉን ነው ።
በቁስ ሰቀቀን እና በሆድ ተገዝተን ፣ አፈር ለሚሆን ሰውነታችን እና ጥለነው ለምንሄደው ቁስ የበለጠ ተጨናቂ አድርገውናል ። ከአንድ መሐፀን የወጣ ወንድማችንን እንኳ እያስካዱን በጠላትነት እንድንተያይ አደርገውን በፀፀት ወደማቃብራችን ይሸኙናል ።
ለህዝብና ለሀገር እንዳንጨነቅ በማድረግ አገራችንን እና ህዝባችንን በምፅዎት ኗሪ ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ ረቂቅ ሴራቸውን እየተገበሩ ያሉትን ምዕራብውያን አና ሌሎችንም ትርፋቸውን ብቻ የሚያሰሉትን ቱጃሮች ይህ እሣት የሆነ ትውልድ ጠንቅቆ ያቃቸዋል ።
አደዋ ላይ እነዚህን አልጠግብ ባይ በዝባዥ ኃይሎችን ድል ለማድረግ መቻላችን ከነሱ ያላነሰ እንደውም የሚበልጥ አእምሮ እና ልብ እንዳለን የተገነዘብንበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳልና ።
በዛው ሞራል እንዳንቀጥል ግን በከፋፍለህ ግዛ መንገድ ፣ እንዴት በቋንቋ እንደለያዩን ፣ ከ1928 እስከ 1933 ፣ የአምስቱን ዓመት የተጋድሎ ዘመን ሤራቸውን በመመርመር መረዳትም ችሏል ።
ይኽንን እውነት እነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ፍንትው አርገው በግለ ታሪክ መፀሐፋቸው ፅፈውት አንብቧልና ።
( አንድ ሰው በቋንቋ ልዩነት ብቻ እንዲጠላ የማድረግ ሥነ ልቡና በተደራጀ መልኩ በዜጎች ልብ እንዲሰርፅ የተደረገው በአምሥቱ ዓመት የኢጣሊያን ወረራ ጊዜ ነበር ። መለሥም ” የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ? ” ሲል ይኼ ስነ ልቡና ተጠናውቶት ነው ። ይኸ አፍረሽ ስነልቡና ግን በቅኝ ገዢ አገሮች ውስጥ የለም ። በደቡብና ሰሜን አሜሪካም የለም ። በዛሬዋ ኢሲያ አህጉርም የለም ። ኧረ ከኢትዮጵያ በስተቀር ዛሬ በአፍሪካም የለም ። ሰው በቃ ሰው ነው ። ቋንቋ አይደለም ። ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓመት አስቀድሞ የነበረውን ዝርያ ከቶም ቆንቋ አይገደውም ነበረ ። ከ15 ሺ ዓመት አስቀድሞ የነበረው ደግሞ በምን ቆንቋ እንደሚግባባ አይታወቅም ነበር ። (ሁሌም አዲስ ለሆነ ሆድ ፣ ምቾትና ድሎት በማሰብ ብቻ የተፈጥሮን አመጣጥ መካድና የታሪክን እውነት በውሸት መተካት ከንቱ ተግባር ነው ። የራስን ትርክት ጎልቶ እንዲወጣ በማድረግ ዘላለማዊ ላልሆነ ምቾት ና ድሎት ሲባል የሚተገበር ከንቱነት ደግሞ በታሪክ ሁሌም የሚያሶቅስ ይሆናል ። )
ታሪክ ለሥመ ጥር እና አርቆ አሳቢ መሪዎች ፣ የሰጠው ክብር በዚህ ትውልድ እንደገና ሊታደስ ይገባዋል ።እኛ ኢትዮጵያዊያን በአደዋ ድል አማካኝነት የተጎናፀፍነው ድል ለአፍሪካ ነፃነትን ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣትን አጎናፅፏል ። የጥቁር የበታችነት እና ያለማወቅ ሐሰተኛ የነጮች ትርክት በኢትዮጵያዊያን የአደዋ ድል ነበር የተገለጠው ።
” ነጭ ኃያልና ሁሌም ተመላኪ ነው ” ብለው የሚያምኑ ቅኝ ገዢውች ጥቁር ኃያልና የአምላክ መገለጫ ክንድ እንዳለው የተገነዘቡት በአደዋ ድል ነው ።
ወደ አድዋ ፣ በሦሥት አቅጣጫ እየገሰገሰ የመጣው ፣ በሦሥት ጀነራሎች የተመራው የሠለጠነው የኢጣሊያ ጦር የተሸነፈው ያለአንዳች ስስት ፣ ደረቱን ለጥየት በሰጠው ጥቁር ኢትዮጵያዊ መሆኑ የጥቁሮች ትንሣኤ ነበረ ።
ይኽ ድል በዛን ወቅት የዓለምን ኃያላን ያስደገጠ ነበር ። በተቃራኒው መላውን ጥቁር ህዝብን ያስፈነደቀ ነበር ። መላው ጥቁር ህዝብ የፈነደቀው የነጭ የበላይነት አደጋ ላይ በመቀልበሱ ነው ። ” ጥቁርም ነጭን መግዛት ፣ ማሸነፍ መማረክና ምህረት ማደረግ ይችላል ። ” በማለት በጥቁሮቹ ኢትዮጵያዊያን ድል አማካኝነት ሥነ ልቡናው ታደሱ ለነፃነት መፋለም የጀመረው ከአደዋ ድል በኋላ ነው ።
ከድሉ በኋላ ፣ በጀነራል ባራቴሪ ፊት አውራሪነት የሚመራውን ጦር ያ በአገር ፍቅር ስሜት ልቡ የነደደው የኢትዮጵያ ባለ አገር አደዋ ላይ ድል ሲያደርገው የኢጣሊያን ህዝብ ለሚንሊክ ታላቅ የጀግና ክብር ሰጥቶ ነበር ።
የኢጣሊያንን ንጉስ ልጅ ( አልጋ ወራሹን ) በእንኮኮ በመሸከም ፣ ህዝቡ በአጀብ ከቦ ” ምኒልክ ለዘላለም ይኑር ! ” በል እያለ ፣ ቀኑንን ሙሉ በሮም አደባባይ እንዲጮኽ እንዳደረገ መላው ጥቁር ህዝብ ሲሰማ ደግሞ ፣ ያንን ጥቁር ንጉሥ አፄ ምኒልክን በእጅጉ ወዶታል ።