ታዬ በክልሉ ያለውን ፣ መሰረታዊ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ለማንሳት ፈልጎ ነው ፣ ማይክ የተዘጋበት፣ እንዳይናገር፡፡
በክልሉ በተለይም በኦሮሞ ክልል በወለጋ አራቱ ዞኖች፣ በምእራብ እና ሰሜን ሸዋ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጦርነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ እንደዚሁም በቤኒሻንጉል ክልል የከማሺ ዞን፡፡ በኦሮሞ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፣ ጉጂ ዞን እና ም እራብ ጉጂ ዞን፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞንና በአማራ ክልል የስሜን ሸዋ ዞን ከኦነጎች ጋር በተገናኘ አለመረጋጋቶች አሉ፡፡
ብዙዎቻችን ኦነግ ሲባል አንድ ኃይል ይመስለናል፡፡ ያ ስህተት ነው፡፡ ቢያንስ ሶስት ኦነግ ነን የሚሉ፣ የኦነግን አርማ እየያዙ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አሉ፡፡
1ኛው በጃል መሮ የሚመራው ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን በዋናነት በጉጂና በቄሌምና ምእራብ ወለጋ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው፡፡ አቶ ዳዎድ ኢብሳን የፖለቲካ መሪው አድርጎ የሚቆጥር ነው፡፡ ይህ ቡድን ለርሱ የሚሰሩ፣ መረጃዎች የሚያቀብሉት መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ የርሱ ሰዎች አሉ፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ፣ መከላከያ ውስጥ፣ የኦሮሞ ክልል መንግስትና የኦሮሞ ክልል ልዩ ኃይል ውስጥ፡፡
2ኛው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ በኦሮሞ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የሚንቀሳቀሰው በአብዛኛው አክራሪ ሙስሊሞች ያሉበት፣ የነ ጃራናና ዋቆ ጉቱ አምላክዊዎች ያሉበት ነው፡፡ አንድ ወቅት ኢስላማዊ ኦነግ (IFLO) ይባሉ የነበሩት፡፡ ይህ ቡድን ከአርሲ/ባሌ/ሃረርጐ ሰንሰለቱን በአዋሽ በኩል፣ በአፋርና በአማራ ክልል መካከል ባለው ቀጭን መስመር አድርጎ፣ ወደ ከሚሴ እየተንቀሳቀሰ ሕዝብን የሚያሸብር ቡድን ነው፡፡ በአጣዬ፣ በካራቆሬ ጥፋቶች የሚፈጽመው ይህ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን በኦህዴዶች የተመሰረተ ባይሆንም፣ በኦህዴድ መዋቅር ውስጥ ባሉ፣ የአርሲና የባሌ አመራሮች የሚደገፍ ነው፡፡ በተለይም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የብልጽግና አመራሮች ከዚህ ቡድን ጋር በቁርኝነት የሚሰሩ ናቸው፡፡
3ኛ ኦህዴድ ያደራጀው የኦነግ ቡድን ነው፡ ይህ ቡድን ጋችና ሲርና በሚል ፣ በኦህዴድ ብልጽግና ውስጥ ባሉ፣ ቀን ቀን የብልጽግና ማታ ማታ የኦነግ ኮፍያ ባደረጉ በኦህዴድ አመራሮች የተደራጀ፣ የመንግስትን መዋቅር የሚጠቀም፣ በመንግስት ከፍተኛ የትጥቅና የሎጂስቲክ ድጋፍ የሚሰጠው ቡድን ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ቡድን በአብይ አህመድ የተገፋው የለማ መገርሳና የጃዋር መሐመድ መዋቅር የሚያንቀሳቀሰው ቡድን ነው የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ይህ ቡድን በዋናነት የሚንቀሳቀሰው በምእራብ ኦሮሚያ ፣ ምእራብ፣ ሰሜን ሸዋ ዞኖችና፣ በወለጋ ነው፡፡
እነዚህ የኦነግ ቡድኖች ካለባቸው አንዳንድ ትላልቅ ችግሮች መካከል፣ የታጠቁ፣ የተደራጁ ቢሆኑም ፡
1ኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሌላቸው ናቸው፡፡ 2ኛ ምን ለማሳካት እንደሚፈልጉ አላማቸው አይታወቅም፡፡ 3ኛ አንድ አካባቢ ማውደም፣ ማጥፋት፣ የጭምላ ጭፍጨፋ መፈጸም እንጂ፣ አካባቢዉን ተቆጣጥሮ፣ አረጋግቶ፣ ነጻ መሬት ፈጥሮ ቢያንስ በነርሱ ስር ሰላምና መረጋጋት መፍጠር የሚችሉ አይደሉም፡፡ ተራ ወንበዴዎችና ሽፍታዎች ናቸው፡፡ አሁን ሕወሃትን ውሰዱ፣ ቢያንስ መሬት ተቆጣጥሮ ቢከፋም ቢለማም እያስተዳደረ ነው፡፡ ነጻ መሬት ይዞ፡፡ የኦነግ ቡድኖች እንደዚያ አይደኩም፡፡ ጫካ፣ ለጫካ እየዞሩ ፣መከላከያ ለቀቀ ሲባል እየመጡ ንጹሃንን ሴቶችና ሕጻናት የሚገድሉ ናቸው፡፡
እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው የዶር አብይ አህመድ ኦህዴድ ብልጽግናዎች፣ ምን እንኳን ላይ ላዩን አንድ መስለው ቢታዩም፣ በውስጥ ግን ስር በሰደደ መልኩ መከፋፈላቸውን ነው፡፡ ከነ ጃልር መሮ ጋር የሚሰሩ አሉ፣ በራሳችው ፣ ጋችና ሲርና በሚል የኦነግ ኃይል አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አሉ፣ ከአክራሪ ሚስሊሞ ኦነጎች ጋር የሚሰሩ አሉ፣ ከኦነግ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የኦሮሞ ብልጽግናዎች አሉ፡፡ ይህ ክፍፍል ደግሞ ታች ባሉት አባላት ጋር ብቻ ሳይሆን በአመራሮች ደረጃም ያለ ክፍፍል ነው፡፡ በዋናነትም ከአውራጃ ጋርም የተገናኘ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ነው በኦሮሞ ክልል ያለው የመረጋጋት ችግር መፍታት ያልተቻለው፡፡ በክልሉ ያሉ የተለያዩ የኦነግ ቡድኖች በአንድ መልኩ ሆነ በሌላው መልኩ የመንግስት አካል ስለሆኑ ነው፡፡ መረጃዎች አስቀድሞ ስለሚደርሳቸው፣ መከላከያ ሲመጣ ይሸሻሉ፡፡ መከላከያ ሲሄድ ይነገራቸዋል ይመጡና የሽብር ተግባራቶቻቸውን ይፈጽማሉ፡፡
ለዚህ ነው በዶር አብይ አህመድ የሚመራው የኦህዱእድ/ብልጽግና መንግስት በኦሮሞ ክልል ያለው ችግር ማስቆም አይችልም የሚል እምነት ያለኝ፡፡ ለዚህ ነው ፌዴራል መንግስቱ ከኦህዴድ ነጻ ወጥቶ፣ ሁሉንም አቀፍ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት የምለው፡፡ ያኔ፡ ቢያንስ ለኦነግ የሚሰሩትን ከፌዴራል መንግስት ሃላፊነት ቦታ ላይ ማንሳት ስለሚቻል፣ በቀላሉ የኦነግ ታጣቂዎችን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በመንግስት የተማረሩ ታጣቂዎችን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር ይቀንሳል፡፡ ታጣቂዎችን የተቀላቀሉም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡