የህዝብን ጥያቄ መንግስት የጥያቄው ባለቤት ከሆነው ህዝብ በላይ አውቃለሁ ማለት አይችልም

July 3, 2022

የደቡብ ክልል አደረጃጀት ጥያቄ በተመለከተ አፈታቱን መንግስት በጥንቃቄና ለህዝቡ ክብር ባለው መንገድ ማስተናገድ እንዳለበት ደጋግሜ ማሳሰቡን አሁንም አልተወውም፡፡ የጥያቄውን ክልላዊ ገጽታ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ በጥቅል የዳሰስኩት ሲሆን ዛሬና ቀጥሉ በሚኖሩኝ ትዝብቶች የአንዳንድ ዞኖች/ብሔረሰቦችን ጥያቄ ገጽታ በተናጥል ለመነካካት እሞክራለሁ፡፡ ለዛሬ በወላይታ የክልል ጥያቄ ለመጀመር ይፈቀድልኝ፡፡

ስለ ጉዳዩ ብዙም ታሪካዊ ዳራ ማሰስ ሳያሰፈልግ ወላይታ ውስጥ ምላሽ እየጠበቀ ያለው የክልል ጥያቄ የሰፊው ህዝብ ጥያቄ መሆኑን የሚያስረዳ ከ2 ዓመት በፊት ህዝቡ በአደባባይ ፍላጎቱን የገለጸበት ቪዲዮ ከጹሑፌ ጋር በአስረጅነት አያይዤዋለሁ፡፡ ይህ ህዝብ ፊላጎት መሆኑን ካልተጠራጠርን ወይም ለጥያቄውና ጠያቂው ተገቢውን ክብር ካልነፈግን በስተቀር የአሁንም ሆነ የቀደመው ጠ/ሚ/ር እዲሁም ነቢያትም ሆነ ካህናት ቀጥታ ጥያቄውን ከመመለስ ውጭ የተሸለ የህዝብ ቀልብና ልብ የሚገዛ ዘለቀታዊ ፋይዳ ያለው አማራጭ ማምጣት አይቻላቸውም፡፡

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ከባቢ አየር ስር የክልል ጥያቄ ማለት ትርጉሙ የክብር ጥያቄ፤ የበጀት ጥያቄ፡ የደህንነት ዋስትና ጥያቄ፤ ዕኩል የመልማት ጥያቄ፤ የባህልና ቋንቋ ጥያቄ፤ የክልል መቀመጫ ማዕከል ጥያቄ ወዘተ ሁሉ በውስጡ አጭቆ የያዘ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑ ለማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ህገ-መንግስቱ ነው፡፡ እናም ገዢው ፓርቲና ጠ/ሚ/ሩ በአንድ በኩል ህገ-መንግሰቱን እንደ ዓይኑ ብሌን እየተከላከለ በሌላ በኩል ግን የወላይታ ብሔረሰብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ አንዳንዴ በግልጽ ሌላ ጊዜ በዘዴ ለማደብዘዝ የሚወስዳቸው አካሔዶች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ለዚህም ቢያንስ ቀጥሎ ያሉት ግልጽ ምክኒያቶቹ መጥቀስ ይቻላል፡፡

1) የክልል ጥያቄ የበጀት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ዝርዝር ማብራሪያ የሚያስፈልገው ነጥብም አይመስለኝም፡፡

2) የክልል ጥያቄ አሁን ባለው ህገ-መንግስትና ፖለቲካዊ ድባብ የብሔረሰቡ ደህንነት ዋስትና ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ ክልሎች ለደህንነታቸው መድህን አድርገው የሚያዩት የክልል ፖሊስና ልዩ ሀይል ነው፡፡ በዚህ አንጻር የወላይታ ህዝብ ከወገንተኝነት የጸዳና ደህንነቱን የሚከላከል የራሴ የሚለውን የክልል ልዩ ሀይል በማጣት ሰኔ 2010 ዓ/ም ራሱ ቁንጥር መንጥሮ በገነቧት አዋሳ ከተማ በጠራራ ጸሐይ እስከመታረድና በህይወት እስከመቃጠል ድረስ ከባድ መከራ ያስተናገደና የግፍ ሰላባ የሆነ ማህበረሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የራሱ ልዩ ሐይልና ክልላዊ ፖሊስ ማደራጀት ቢፈልግ ቅንጦት አይሆንበትም፡፡

3) አሁን ባለው ሁኔታ የክልል ጥያቄ ለወላይታ ህዝብ የክብር ጥያቄም ነው፡፡ የወላይታ የህዝብ ቁጥር ከአፋርና ቤንሻንጉል ህዝብ ቁጥር ድምር በላይ ነው፡፡ እንዲሁም ከጋምቤላ ቤንሻንጉል ጉምዝና ሐራሪ (ሶስት ክልሎች) ድምርም በላይ ነው፡፡ መንግስት መደሰት ወይም አለመደሰቱ ሳያስጨንቀው እንደ አፋር፤ ሐራሪ ወዘተ በራሱ ስም የሚጠራና ብሔረሰባዊ ክብሩን የሚያንጸባርቅ አሁን ያለው ህገ-መንግስት የሚፈቅድለት ክልል እንዲኖረው ማረጋገጥ አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በአህጉር ደረጃ እንኳ አፍሪካ ውስጥ ናምቢያ፤ ጋምቢያ ፤ቦትስዋና ፤ ጋቦን፤ ሌሶቶ የመሳሰሉት ሀገሮች የህዝብ ብዛታቸው ከ3 ሚሊዮን በታች ነው፡፡ ባጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ ወደ 15 ያህል ሀገራት የህዝብ ብዛታቸው ከወላይታ ህዝብ ቁጥር በታች ነው፡፡ ስለዚህ በአብላጫው ህዝብ ፍቃደኝነት ካልሆነ በስተቀር በዛሬዋ ኢትዮጵያ ወላይታ በዞን መዋቅር ዕርከን መታጠር ማህበረሰባዊ ክብሩን እንደማመጥን ህዝቡ ጥያቄ ቢያነሳ ማንም ሊያፍነው ሙከራ ማድረግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ይህ የሚለመን ሳይሆን የሚጠየቅ የህዝብ መብት ነው፡፡

4) አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወላይታ ውስጥ የክልል ጥያቄ የመልማት ጥያቄም ነው፡፡ ወላይታ ውስጥ ተቋማት ተንኮታኩተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አጋንፋው የሶዶ ሆስፒታል በብቃት እናቶች የማዋለድ አገልግሎት መስጠት እንኳን ተስኖት ዓለም በሰለጠነበት ዘመን እናቶች በወሊድ እየረገፉ ነው፡፡ ህጻናት ሰባዓዊ ክብር በጎደለው ሁናቴ እንደ ኮንትሮባንድ ሰልቫጅ በተሸከርካሪ ዕቃ መጫኛ ሥር እየተወሸቁ ተሰርቀው ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ይጋዛሉ፡፡ በአከባቢው ያለው ማህበራዊ ችግሩ ውስብስብ በመሆኑ ያንን የሚመጥን መዋቅር ይጠይቃል፡፡ መሰረተ-ልማትም እንዲሁ ነው፡፡ ወላይታ በክልል ደረጃ የተዋቀረ አደረጃጀት ቢኖረው፤ በወላይታ መጠን ሥራ አጥነት በሌላት ኢትዮጵያ የሀገሪቱ ጠ/ሚ/ር በአከባቢው እንዳስትሪ ፓርክ ይሰራ የሚለውን የህዝብ የመልማት ጥያቄ አያጠጥለውም፡፡ ትግራይ ውስጥ ከ70 ኪ/ሜ ርቀት ባነሰ አውሮፕላን ማረፊያ ባላት ኢትዮጵያ ወላይታ ብቻ ሳይሆን ዙሪያው ያለውን ሌላ ዞን ጨምሮ 5 ሚሊዮን ህዝብ ድረስ ሊያገለግል የሚችል አውሮፕላን ማረፊያ ጥያቄም በሀገሪቱ መሪዎች ደረጃ ከ115 ኪ/ሜ በታች እንዴት ሌላ አውሮፕላን ማረፊያ ይጠየቃል የሚባልለት ያህል አልባለ ጉዳይ ተደርጎ አይጣጣልም ነበር፡፡

5) ለወላታ የክልል ጥጣቄ የክልል ማዕከል/ ዋና ከተማም ጥያቄ ነው፡፡ ወላይታን በጥፍሩ፤ በጥሪቱና በጥረቱ ለዘመናት ከገነባው አዋሳ ተገፍቶ ባዶ እጁን ሲወጣ ያልተከላከለው መንግስት ከአሁን በኋላ ወላይታን ከዞኑ ወሰን ውጭ አንድ እንች ወደ ሌላ ማዕከል ሊግፋው ማለት ህዝቡ ላይ ጦርነትና እልቅት ማወጅ ይሆናል፡፡ ይህን እንደ መንግሰት ማሰብ የሚቻለው ጠ/ሚ/ር አብይ አዲሱን ቤተ-መንግስት እቅድ በማጠፍ በ4.9 ቢሊየን ብር አዲሱ ክልል በጋራ የሚጠቀምበት አዲስ የክልል ማዕከል በዚህ 5 ዓመት ውስጥ ገንብቶ ከሰጠ ብቻ ነው፡፡

ለማጠቃለል ሰሞኑን መንግስት በወላይታና ሌሎች የደቡብ ክልል ዞኖች ባሉት መዋቅሮች የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምላሽ ዙሪያ ዝግ ውይቶች እያካሄደ መሆኑን እታዘብን ነው፡፡ ውይይቱ መልካም ሆኖ ነገር ግን መጨረሻ ላይ የውይይቱ መቋጫ ተብሎ ይፋ የሚደረገው ውሳኔ ይህን በቪዲዮ ላይ የሚታየውን የሰፊው ወላይታ ህዝብ ስመት የሚጋፋ እንዳይሆን መንግስት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ የካድሬዎች ውሳኔ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ሊያንጸባርቀው አይችልምና ህዝብ ለግጭት የሚጋብዝ ውሳኔ ላይ እንዳይደረስ መንግስት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡

ሰሞኑን የሌላ ደቡብ ክልል ዞን/ብሔረሰብ የክልል ጥያቄ አጭር ዳሰሳ ይዤ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

Medhin Marcho

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

መስጠት ብቻ ወይንስ ስጥቶ መቀበል? (ጥሩነህ)

Next Story

ኢዜማ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን በድጋሚ መሪ አድርጎ መረጠ

Go toTop