በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ታልታሌ ወረዳ ቡሌደንቢ ቀበሌ ሰዎች በበሬ ፈንታ ቀንበር ሞፈር ላይ አስረው በመጎተት ሲያርሱ – DW

April 25, 2022

ሃልካኖ ዱባ ነዋሪነታቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ታልታሌ ወረዳ ቡሌደንቢ ቀበሌ ነው፡፡ ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የነበረውና ሰዎች በበሬ ፈንታ ቀንበር ሞፈር ላይ አስረው በመጎተት ሲያርሱ በአይን መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ ከመዲናዋ አዲስ አበባ 650 ኪ.ሜ ገደማ ርቆ የሚገኝ ስፋራ ነው፡፡ ከዞኑ መናገሻ ያኣበሎ ደግሞ 100 ኪ.ም ገደማ በስተደቡብ አቅጣጫ የተሰየመ ወረዳ ነው፡፡ ሃልካኖ ዱባ ነዋሪነታቸውን በዚችው ታልታሌ ወረዳ ቡሌደንቢ ቀበሌ አድርገዋል፡፡ ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የነበረውና ሰዎች በበሬ ፈንታ ቀንበር ሞፈር ላይ አስረው በመጎተት ሲያርሱ በአይን የተመለከቱዋቸው ጎረቤታቸው መሆኑንም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡ “ያው እየተጋገዙ በራሳቸው ያረሱትን ሁሉንም አውቃቸዋለሁ፡፡ እዚሁ ጎረቤቴ ናቸው፡፡ በስም ሁላ ልገልጽልህ እችላለሁ፡፡ ሁላቸውም የሚያርሱበት በሬ የላቸውም፡፡ ያሉዋቸው ከብቶች ከፊሉ አልቋል ያሉትም እንኳን ለእርሻ ሊያገለግሉ በሰው ነው ተገፍተው እየተነሱ ሚሰማሩት፡፡ በመሆኑም የሚያርሱበት በሬ ስለሌላቸው ተደራጅተው እየተጋገዙ ከፊሉ ከኋላ ሲያርሱ ሌሎች ከፊት እንደ በሬ እየጎተቱ ማረስ ጀምሩ፡፡ ማረስ ያልቻለ ደግሞ እንዲሁ ያልታረሰን መሬት እየዘሩ ዘሩ እንዲሸፈን ከድርቁ የተረፉትን ከብቶች እላዩ ላይ እየነዱ ነው፡፡ ነገሩ ዳግም ላለመራብ አማራጭም የማጣት ነው፡፡”

አቶ ሃልካኖ እንደሚሉት አርሶ አደሮቹ አሁን እየዘሩ ያሉት ጤፍና በቆሎ ነው፡፡ በተደጋጋሚ የዘሩት በዝናብ እጥረት ምንም ጥቅም ሳይሰጥ መጥፋቱ ደግሞ ፈተናውን እንዳከበደባቸውም አብራርተውልናል፡፡ “አሁን እያረሱ ያሉት መሬት ከዚህ ቀደም ቢንስ 2 ወይም 3 ጊዜ ታርሶ እህል በዝናብ እጥረት ጠፍቶበታል፡፡ የዘሩት ዘርም ፍሬ ሳይሰጥ በተደጋጋሚ ጠፍቶበታል፡፡ በኛ አካባቢ ህብረተሰቡ ትልቅ የርሃብ ስጋት ውስጥ ነው ያለው፡፡ በርግጥ ሴፍት ኔትና በአከባቢው ያለ የአደጋ ስጋት መከላከል ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ አሁን በርሃብ ተጎድቶ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ባይኖርም እንደዚህ መዝለቅ እንደማይቻል ግን ሁሉም ሰው ተረድቷል፡፡”

መነጋገሪያ የሆነውን አርሶ አደሮቹ እንደ በሬ እየጎተቱ በማረስ ላይ ሳሉ ምስላቸውን በፎቶ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርፀው ያሰራጩት መምህር ዱባ ቡራ መጀመሪያ ነገሩን ሲያዩ ከመገረምም አልፈው በእጅጉ ማዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡ “ታውቃለህ እኔ እንዳጋጣሚ ወደማስተምርበት ትምህርት ቤት ስሄድ በዚያ አልፋለሁ፡፡ መጀመሪያ ሳያቸው በአጋጣሚ ስልክ አልያዝኩም ነበር፡፡ ከዚያን በቀጣይ ቀን ስልኬን ይዤ ሄድኩና ፎቶም አነሳኋቸው ቪዲዮም ቀረጽኩአቸው፡፡ ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ አንድ-25 ይሆናሉ፡፡ የሰው ልጅ በዚህ መልኩ መሬት ሲያርስ አይቼም ሰምቼም ስለማላውቅ በጣም ነው የተሰማኝ፡፡ ሲሆን ሲሆን ዓለማችን ከበሬ አልፋ በትራክተር ስታርስ እነዚህ ገበሬዎች በእራሳቸው እጅ ሲያርሱ ሳይ ተረበሽኩ፡፡ ለምንድነው ይሄን እንደ አማራጭ የወሰዳችሁት ብዬ ስጠይቃቸውም፤ ምን እናድርግ ያለን ከብት በሙሉ አልቀውብናል፡፡ በሚቀጥለው ኣመት ደግሞ ከዚህ የባሰ ችግር ስለምጠብቀን ተቀምጠን ከምናልቅ ነው አሉኝ፡፡”

Äthiopien | Dürre in der Borna-Zone

መምህሩ አክለውም በዚህ አካባቢ በበሬ ሲያርሱ የሚያውቃቸው አርሶ አደሮች መፍትሄ ያገኙ እንደሆነ ብሎ በማሰብ ምስላቸውንም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨቱን ነግረውናል፡፡ “ታውቃለህ ይህ ወቅት ለኛ የተሻለ ዝናብ ሚጠበቅበት የክረምት ወራታችን ነው፡፡ ሰሞኑን በተከታታ ደህና ዝናብ ጥሎልናል፡፡ መሬትም ረጥቦ ለእርሻ የሚበቃም ተገኝቷል፡፡ እንደሚታውቁትም በተልተሌ ወረዳ ብቻ ሳይሆን ቦሬና ዞን በሙሉ በነበረው ድርቅ ከብቶች አልቀው ህዝቡ አስከፊ ችግር ውስጥ ነው፡፡ እዚህም ያው ነው የተስተዋለው ነገር፡፡ ያለው በትራክተር ያርሳል እንጂ ምንም ለእርሻ የሚሆን ከብት የለም አሁን፡፡ አብዛኛውም አልቀዋል፡፡ ለዚህ ይመስላል እነዚህ ሰዎች አማራጭ ብለው በመውሰድ እራሳቸው የበሬ ቦታንም ተክተው ለማረስ የተገደዱት፡፡ አሁን የጀመረው ዝናብ ቀጣይነት ኖሮት ለሚቀጥለው ሶስት አራት ወራት እየተዘራ ያለው ካላፈራ ካሁን በኋላ ደሃ ያለው አይባልም ሁሉም ሊራብ ይችላል፡፡”

ቦረና ዞን ለተከታታይ የዝናብ ወራቶች ዝናብ ሳያገኝ በመቅረቱ እጅግ ብርቱ ድርቅ ከጎዳቸው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቁም እንስሳት ከሞቱባቸው አከባቢዎች መሆኑ ይታወቃል፡፡

ስዩም ጌቱ

ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

‹‹በትምህርት ሥርዓት ላይ መቀለድ በትውልድ ላይ መቀለድ ነው የሚል ስምምነት ያሰፈነ መፍትሔ ያስፈልገናል›› ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)

Next Story

ጎንደር ከተማ ላይ በግፍ የተገደሉት ወንድሞች ቁጥር ሶስት ደርሷል

Go toTop