ሰሞኑን የሰጡት ቃለመጠይቅ በማነጋገር ላይ ስለሆነ ከማውቀው ከተረጋገጠ ታሪክ በመነሳት ልጽፍልዎ በቅቻለሁ::
በመሰረቱ የአሁኗ የትውልድ ከተማዬ አዲስአበባ የቀድሞ ስሟ ፊንፊኔ እንደነበር የታሪክ ጠበብት ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ በ1926 የጻፉትና በቄስ ባድማ ዘንድ በስደቱ ዘመን በአደራ ቆይቶ በ1999 በሴንትራል ማተሚያ ቤት የታተመው መጽሃፍ ይመሰክራል:: የተወለድኩበት ስፈር የዛሬው ፍልውሃም ደክሃራራ መሆኑን ‘የፊንፊኔ አድባር’ በማለት ትመርቅ የነበረችው የማይጨው አርበኛ አያቴ ስትጠቅስ ሰምቻለሁ::
ከዚህ በመነሳት የከተሞችን ስያሜና ወቅታዊ ባለቤቶችን ታሪክ ስቃኝ ጄነቫ በሲዊዘርላንድ መጀመሪያ ቫይኪንግ ኖርዊጂያኖች የሰፈሩባት ቀጥሎ ጀርመኖች ሲሰፍሩባት ቆይቶ በ15ኛ ክ/ዘመን ፈረንሳዮች በብዛት ስለሰፈሩባት ቋንቋዋ ፈረንሳይኛ ሆኗል ከተማዋን ግን ኖርዊጂያኖች ከጀርመኖችና ከፈርንሳዮች ጋር በመጣረስ የዘራቸን ከተማ ነች አይሉም ይልቁንስ የጄነቫ ህገ-መንግስት በግልጽ ያሰፈረው የሁሉም ነዋሪዎቿ ከተማ መሆንዋን ነው::
ከሁሉ በፊት የኒዮርክ ነባር ህዝብ ቀይ ህንዶች መሆናቸው አይዘነጋም:: ቀይ ህንዶች በአሜሪካ አቦርጆኒያዎች በአውስትራሊያ የዘራችን ከተማ ብለው በሌሎቹ በመጤዎቹ ላይ የፋነኑበትን አላነበብኩም በማንም ያልደረሰ በደል ቢደርስባቸውም ዛሬ ያሉት ቅሪቶቻቸው በመጤዎች ላይ ክፋትን አይናገሩም:: ብዙ ስምምነቶች ከሰፋሪዎች ጋር ያደረጉት ለመጣሱ አያሌ መጽሃፍት ይመሰክራሉ::በተመሳሳይ መልኩ ኒዮርክ ላይ መጀመሪያ በ17ኛ ክ/ዘመን የሰፈሩት ደች የተባሉት ኔዘርላንዶች ሲሆኑ ቆይቶ እንግሊዞች በመጠናከር ስለሰፈሩባት ከተማዋ በእንግሊዝኛ ስም ያላት ሲሆን የደች ዘር ወይም የእንግሊዝ ዘር ተወላጆች የዘራችን ከተማ አይሏትም::
ወደ ቀድሞዋ ፊንፊኔ የዛሬዋ አዲስ አበባ ስንመጣ ሁለቱ ቅድም አያቶቼ ከአርሲ በምርኮ ሰሜን ሸዋ ሴት በማግባት የተገኘሁበት ቅድም አያቴና ወለዮ ያገባች ሌላ ሴት አያቴ ከከፊቾ ቢመጡም ሁሉም የጋራ ከተማችን ብለው ያስተላላፉልኝን ይዤ መቀጠል እንጂ ከተማዋ የኦሮሞ መብት ነች ብል ማፈሪያ ሆናለሁ::
ስለዚህ ይህ የሰሞኑ መግለጫዎ “የዓለምን ትኩረት የሳበች ፊንፊኔ ከተማ ኦሮሞ ክልል” ብለው የሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ማስተባበያ ካልተሰጠበት የክፍለ ዘመኑ ደካማ አመክንዮ ይሆንቦታልና በጥልቅ ያስቡበትና መልስ ይሰጡበት ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ::
ፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው ከሚድ ዌስት አሜሪካ
ሚያዝያ 2014 April 2022