የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የሚንስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት ባቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንደሚወስን ታውቋል። ምክር ቤቱ ነገ በረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ላይ ድምጽ ከመስጠቱ በፊት የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላ ሀገሪቱ ለ6 ወራት ያወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የሚንስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ያጸደቀው ከሦስት ሳምንት በፊት ነበር። ምክር ቤቱ ለነገው አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ላንድ ወር ዕረፍት በወሰደበት ሰዓት ነው።
1፤ መንግሥት የብርን ምንዛሪ አቅም በማዳከም የውጭ ንግድን ለማሳደግ የቀየሰውን አሠራር ዕጣ ፋንታ የሚወስን የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ዋዜማ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምንጮቿ ሰምታለች። የዳሰሳ ጥናቱ ብርን ከውጭ የንግድ አጋሮች የመገበያያ ገንዘቦች አንጻር የማዳከሙ አሠራር የመቀጠል አለመቀጠሉን ዕጣ ፋንታ የሚወስን ሲሆን፣ አካሄዱ ለሀገሪቱ አዋጭ ካልሆነ ብሄራዊ ባንክ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ይገደዳል ተብሏል። የብርን የምንዛሪ ተመን የማዳከም አሠራር ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ እንዲቀጥል የታቀደ ነበር። የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን መንግሥት የብርን የምንዛሪ አቅም ያዳክመው በዓለም ባንክ እና ዓለማቀፍ ገንዘብ ድርጅት ተጽዕኖ እንደሆነ ይናገራሉ። Link- https://bit.ly/34EX7jp
2፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ሂደቱ ለጊዜው ቆሞ በአካሄዱ ላይ እንደገና ውይይት እንዲደረግበት መጠየቁን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ራሄል ባፌ ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህንኑ ጥያቄ ያቀረበው፣ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ባስገባው ደብዳቤ ነው። ምክር ቤቱ የአገራዊ ምክክር ሂደቱን ግልጽ እና አካታች ለማድረግ እንዲቻል ምክር ቤቱ ምላሽ ሊያገኙ ይገባቸዋል ባላቸው ጥያቄዎች ዙሪያ እንደገና ውይይት እንዲደረግ የጠየቀው፣ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ 45 ፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ግምገማ ካደረጉ በኋላ እንደሆነ ተገልጧል።
3፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ትናንት እና ዛሬ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትናንት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ሳተርፊልድ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተመድ ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲሁም ከዓለማቀፍ ረድዔት ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ይወያያሉ ተብሏል። ሳተርፊልድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ፣ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ ያሁኑ ሁለተኛ ጊዜያቸው ይሆናል።
4፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከአፍሪካ ሀገራት ባንኮች ጋር የገንዘብ ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት ውስጥ መግባቱን ሪፖርተር አስነብቧል። ኢትዮጵያ አፍሪክሲም ባንክ የተባለው የፓን-አፍሪካ ባንክ በዘረጋው መርሃ ግብር ከታቀፈች የገንዘብ ተቋማትና ንግድ ድርጅቶች ለሚገበያዩዋቸው የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ብር ክፍያ መቀበል ወይም መፈጸም ይችላሉ። ባንኩ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ንግድን ማሳደግ እንዲችሉ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጥ እንደሚችልም ተገልጧል። መንግሥት ባንኩ ለኮሮና ወረርሽኝ ማገገሚያ ከመደበው ገንዘብ ብድር ለማግኘት ድርድር ላይ እንደሆነም ዘገባው ጠቅሷል። አፍሪክሲም ባንክ የተቋቋመው በአፍሪካ ሀገራት መካከል የንግድ ልውውጥን ለማፋጠን፣ አፍሪካዊያን ባንኮች የንግድ ልውውጥ ክፍያ ለመፈጸም በዓለማቀፍ ባንኮች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለማስቀረት እና የንግድ ልውውጥ ወጭን ለመቀነስ ነው።
5፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ባንኮች በሀገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ከውጭ ባንኮች ለሚጠብቃቸው ውድድር እንዲዘጋጁ ትናንት በንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር አሳስበዋል። ዐቢይ መንግሥታቸው የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እንዲሠማሩ እንደሚፈቅድ ጠቁመው፣ ንግድ ባንኮች የሰው ኃይላቸውን እና አሠራራቸውን አስቀድመው እንዲያዘምኑ ጠይቀዋል። የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴም ሀገሪቱ በሯን ለዓለማቀፍ ባንኮች መክፈቷ እንደማይቀር ቀደም ሲል አስታወቀው እንደነበር ይታወሳል። መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን መቼ ለዓለማቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ክፍት እንደሚያደርግ ግን እስካሁን በይፋ የገለጸው ነገር የለም።
6፤ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተያዘው ሳምንት ሐሙስ እና ዓርብ በቤልጂዬም ብራስልስ ከተማ እንደሚካሄድ አውሮፓ ኅብረት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። በመሪዎቹ የጋራ ጉባዔ የኮሮና ወረርሽኝ ክትባትን በተለይ አፍሪካ ውስጥ ማምረት በሚችልበት ሁኔታ እና በአፍሪካ የአረንጓዴ የምጣኔ ሃብት ሽግግር ማምጣት በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ምክክር ይደረጋል ተብሏል። አውሮፓ ኅብረት “ግሎባል ጌትዌይ” በተሰኘው መርሃ ግብሩ ስር በአፍሪካ በተለያዩ መስኮች ለሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንት 150 ቢሊዮን ዶላር ማጽደቁን ባለፈው ሳምንት ይፋ እንዳደረገ ይታወሳል።
7፤ በአሜሪካ የሚገኝ ሱማሊያዊያን እና ትውልደ ሱማሊያዊያን በሚኖሶታ ግዛት ያቋቋሙት ድርጅት አሜሪካ ለሱማሌላንድ ራስ ገዝ የሀገርነት ዕውቅና እንዳትሰጥ የሚወተውት የአሜሪካ ኩባንያ እንደቀጠሩ አፍሪካ ሪፖርት መጽሄት አስነብቧል። የሱማሌ ዲያስፖራዎች ባለፈው ሳምንት የቀጠሩት የፖሊሲ ወትዋች ኩባንያ “ካርል ቮን ባተን-ሞንታግ” ሲሆን፣ ይኼው ኩባንያ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ለሕወሃት ሲሰራ እንደቆየ ይታወቃል። የሱማሌ ዲያስፖራዎች የፖሊሲ ወትዋቹን ኩባንያ የቀጠሩት፣ ሱማሌላንድ በርበራ ወደቧን አሜሪካ ለወታደራዊ አገልግሎት እንድትጠቀምበት ፍቃደኛ መሆኗን መግለጧን ተከትሎ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]