በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ከአሸባሪው ቡድን ጋር መሳተፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ እና የኢትዮጵያውያ ዝርያ የሌላቸው ነጮች እና ጥቁሮች ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተሳትፈው መስዋትነት መክፈላቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት።
የሕወሀት የሽብር ቡድን የከፈተውን ጦርነት እና ጦርነቱን እየመራበት ያለው ህዝባዊ አካሄድ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ያሳየው ድጋፍ የሚበረታታ እንደነበር አስታውሰው በቅስቀሳ የመጣውን የህዝብ ኃይል ለማስተናገድ በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት እንዳልነበር፤ አሁን ላይ ከዛ ሁኔታ እርምት ተወስዶ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ እየተሰራበት እንደሆነ ገልፀዋል።
አጠቃላይ ህዝቡ ለሠራዊቱ ያለው ድጋፍ አሁን ካለው በላይ ሊጠናከር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የገጠመችው ጦርነት ከአንድ ወገን ጋር ብቻ እንዳልሆነ በመረዳት ዋጋ ለመክፈል ያለውን ፍቅር በተግባር ሊገልጽ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ)