1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የቀድድሞውን የውሃና መስኖ ሚንስትር ስለሺ በቀለን የሕዳሴ ግድብና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዋና ተደራዳሪ እና አማካሪ አድርገው እንደሾሟቸው ጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። የቀድሞው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ ደሞ የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ፣ ተፈሪ ፍቅሬ በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ፣ ተስፋዬ ቤልጅጌ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ እና ለገሠ ቱሉ የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
2፤ የአሜሪካው ጆ ባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራዩ ግጭት ጦር መሳሪያ አጓጉዟል በማለት ሲኤንኤን ያወጣው ዘገባ በጣም አሳሰቢ ነው ማለቱን ሲኤንኤን ዘግቧል። ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ዓለማቀፍ የአውሮፕላን በረራ ሕግጋትን እንደሚጥስ እና በዓለም ላይ የመንገደኞች አውሮፕላን ደኅንነትን አደጋ ላይ እንደሚጥል አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደነገሩት ዘገባው ጠቅሷል። የአሜሪካ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል ቶም ማሊኖስኪ በበኩላቸው፣ የዘገባው እውነተኛነት ከተረጋገጠ የአየር መንገዱ ሃላፊዎች የማዕቀብ እና ቅጣት ዒላማ መሆን አለባቸው በማለት ተናግረዋል። ማሎኒስኪ የጆ ባይደን አስተዳደር በትግራይ ክልል ዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም? በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ በመገፋፋት ላይ ያሉ ናቸው።
3፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ትናንት በትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። ሆኖም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ የተናጥል ማዕቀብ ሳይጥል ቀርቷል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት 7 የተመድ ሠራተኞችን ከሀገር ያባረረበትን ምክንያት እንዲገልጽላቸው ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር የጠየቁ ሲሆን፣ ካሁን በፊትም ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አቅርበው ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ሩሲያ በበኩሏ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ለመፍታት አሁንም አቅም እንዳላት ጠቅሳ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ግጭቱንና ሰብዓዊ ዕርዳታውን ፖለቲካዊ ማድረጉ አፍሪካ ኅብረት ግጭቱን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ይጎዳል ስትል አስጠንቅቃለች። ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ማስተጓጎልና ዕርዳታ ጫኝ ካሚዮኖችን ለሌላ ዕላማ መጠቀምን እንደምትቃወም ሩሲያ አክላ ገልጻለች።
4፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ ሃላፊዎችን ለምን ከሀገር እንዳባረረ የማሳወቅ ግዴታ እንደሌለበት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አጽቀ ሥላሴ በትናንት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። ከሀገር የተባረሩት ግለሰቦች በትግራይ ክልል በርሃብ ያልሞቱ ሰዎችን እንደሞቱ አድርገው ሪፖርት በመጻፍ፣ እንደ ዳርፉር ያለ ቀውስ እንፈጥራለን እያሉ የተንቀሳቀሱ፣ የተረጅዎችን ቁጥር በማጋነን እና ለሕወሃት በመወገን በሌሎች በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ተጠምደው የቆዩ መሆናቸውን አምባሳደር ታዬ አብራርተዋል።
5፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት የሚደርስባትን ጫና ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት እስራዔል እንድትደግፍ እንደጠየቁ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ደመቀ ይህንኑ ጥያቄ ያቀረቡት በእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ልዩ ልዑክ አምባሳደር ቫርሊ ሻሮን ከተመራው ልዑክ ጋር ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት ነው። ልዩ ልዑኳ መልዕክቱን ለመንግሥታቸው እንደሚያደርሱ ቃል ገብተዋል።
6፤ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ስም በሰብዓዊ መብቶች፣ ርሃብ እና ድህነት ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን የሚደግፍ ፋውንዴሽን እንደተቋቋመ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። ፋውንዴሽኑን በፕሮፌሰሩ የሙት ዓመት መታሰቢያ ላይ የተቋቋመው፣ በ13 የቤተሰብ አባላት እና ወዳጆቻቸው አማካኝነት እንደሆኑ ዘገባው ገልጧል። ፕሮፌሰር መስፍን በድርቅ፣ በድርቅ ተጋላጭነት እና ርሃብ ዙሪያ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉ ሲሆን፣ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ መስራች እና የረጅም ጊዜ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ነበሩ።
7፤ አውሮፓ ኅብረት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መቀሌ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን በአውሮፕላን እንዳጓጓዘ በድረገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የዕርዳታ በረራውን ያስተባበሩት ኅብረቱ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን እንደሆኑ የገለጠው መረጃው፣ ባሁኑ በረራ አልሚ ምግብን እና ለሆስፒታሎች የሚከፋፈሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቶችን ጨምሮ 10.6 ቶን ዕርዳታ መቀሌ ላይ እንደተራገፈ አመልክቷል።
[ዋዜማ ራዲዮ]