የጥቅምት ሀያ አራቷ ቀን በርግጥም ጥቁር ማክሰኞ ናት። የጥቁሯ ማክሰኞ ውሎ አዳር ግን የአንዲት የጀምበር ምህዋራዊ ሽክርክሪት ውጤት አልነበረም።
ለዘመናት ተሰላስሎ፣ ተዘርቶ፣ ተኮትኩቶ፣ አፍርቶና ተወቅቶ የተበላ የጥላቻ ልክፍተኞች ሂሳባዊ ስሌት ውጤት እንጂ።
አንዲት ጥንታዊት አገር ለመበታተን ህዝቦቿን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ተቆጣጥሮ፣ ትውልድን በጥላቻ መርዞ፣ የጥፋት ድግስ የቀመረ አሸባሪ ቡድን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የጥላቻ ልክፍተኛ አሸባሪው ቡድን በሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ግፍና ሰቆቃ ለመግለጽ ግን ለብዙዎቻችን ቃላት ይቸግራል።
‘ቡድን ከፋባት እንጂ አልከፋችበትም፤ ለገሰች አልነፈገችውም፤ ግን ከውጭ ጠላት ጋር ተባብሮ ለማፍረስ መሞከር ከምን የመነጨ ይሆን?’ በማለት ይጠይቃሉ።
የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ጭካኔ፣ ጥላቻ “ኢትዮጵያ ምን ብታደርገው ይሆን?” በማለት ለሁሉም ጥያቄ የሆነ መልሰ ቢስ ጥያቄ ያነሳሉ።
የሽብር ቡድኑ ለዘመናት በጥላቻ ኮትኩቶ ያሳደገውን ወጣት በማነሳሳት ኢትዮጵያን አስወግቷል፤ ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትን በፕሮፓጋንዳ በማሰለፍ ወላጆችን ያለጧሪ አስቀርቷል፤ የታዳጊዎችንም ተስፋ አጨሟል።
በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ድጋፍ ተመልሶ ወደ ስልጣን ለመምጣት የተቀናጅ ጥቃት ቢፈጽምም፤ ድርጊቱ ኢትዮጵያዊያን አስቆጥቶ ቡድኑ አከርካሪው ተሰብሮ ለስምንት ወራት ዋሻ ለዋሻ ሲሽሎከሎክ መቆየቱ ይታወሳል።
ማይካድራ ላይ አማራ ማንነት ያለችውን ዜጎች ጨፍጫፊዎችን ጨምሮ ከአሸባሪው ቡድን ጋር በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት ያደረሱ ታጣቂዎች መካከልም ወደ ሱዳን ሸሽተው ቆይተዋል።
ዳሩ ግን በሱዳን ከሚገኙ የሽብር ቡድን አመራር አባላት ዳግም ተመልምለው “በአሸንፈናል” ፕሮፓጋንዳ ሰክረው፤ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ቆርጠው አገራቸውን ማድማት የተመለሱ የቡድኑ አባላት እርምጃ ተወስዶባቸዋል፤ተማርከዋልም።
በጥላቻ ልክፍተኞች ሰለባ ሆነው ከተያዙት መካከል አንዱ የ21 ዓመቱ ቸኮል በርሔ ነው።
ለወላጅ እናቱ ብቸኛ የሆነው ቸኮል የጥቅምት ሃያ አራት ክስተትን ተከትሎ በድሃ እናቱ ተነጥሎ በችኮላ ወደጦር ሜዳ እንዲጋዝ ተገደደ፤ ኑሮውን አሸንፎ የመለወጥ ህልሙም ከንቱ ቀርቷል።
ቸኮልና ጓደኞቹ በውጊያ ተሸንፈው ወደ ሱዳን ቢሸሹም ከሰፍራው ከሚገኙ የአሸባሪው ሕወሃት አመራር አባላት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የመገናኛ ራዲዮን ተሸክመው በወልቃይት በኩል ወደ ትግራይ ሊገቡ ሲሉ ተማርከዋል።
በከሃዲው የአሸባሪው ሕወሃት ቡድን ‘በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት አንገታችንን እንድንደፋ አድርጎናል’ የሚለው ቸኮል፤ በአሸባሪ ቡድኑ ስብከት ተታለው በታጣቂነት በመሳተፋቸውም መጸጸቱን ይናገራል።
በተመሳሳይ ከአሸባሪው ቡድኑ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ከተማረኩት ውስጥ አለምሰገድ ተስፋዬ፣ ሀጎስ ተክለሃይማኖትና አቤል ብርሃኑም አገራቸውን በመውጋታቸው ተጸጽተዋል።
የሕወሃት ቡድን ህጻናትን ጨምሮ የድሃ ልጆቹን ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑን የሚናገሩት ምርኮኞቹ፣ ‘ወላጆቻችን የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ አናውቅም፣ ስለኛም ወላጆቻችን አያውቅም’ ይላሉ።
ምርኮኞቹ የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባው በክህደት ቢወጋም እያደረገላችው ያለው እንክብካቤ ግን እንዳስደነቃቸው ገልጸው፤ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ አያያዝ ችግር እንዳልገጠማችው ተናግረዋል።
ምንጭ ፦ ኢዜአ