“ አባይ ማለት አባት ማለት ነው ። አኛ ኢትዮጵያዊያን በቁልምጫ ስንጠራው ። “ መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

July 9, 2021

ኢትዮጵያዊያን አባይን አባታችን ፤ አባ፤ አባዬ ፤ አባይ ፤ በማለት በእውነተኛ ሥሙ ዛሬ እየጠሩት ነው  ። አባትነቱን በተግባር በማሥመሰከሩ ።

” አባት ” በኢትዮጵያዊያን ባህል ውሥጥ ታላቅ ክብር አለው ። “አባት ሣለህ አጊጥ ፤ ጀንበር ሳለች ሩጥ ።” ይላል ሥነ _ቃላችንም  ።  የአባት  ክብር  የመነጨው ከተሸከመው ኃላፊነት አንፃር ነው ። የመሰረተውን ቤተሰብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሞላት ጠንክሮ የመስራት ግዴታ አለበት ። የተሻለ ኑሮ ቤተሰቡ እንዲኖር ቁር ና ሀሩሩ ሳይበግረው ፣ ሌት ተቀን መልፋት ይጠበቅበታል ። ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ ግን ቤተሰቡ ሊፈርስ ፣ ልጆቹ ጎዳና ሊወጡ ይችላሉ። እናም አባይ ብለህ የምታቆላምጠው እንዲህ አይነቱን ለቤተሰቡ ሟች የሆነውን አባት ነው ፡፡

” አባይ ፤ አባዬ ” ለኢትዮጵያዊያን ዛሬ የቁልምጫ ሥም ነው ። ጠበቅ  አድርገው ፣ በፍቅር የሚጠሩት ሥም ። “አባይ!  አባይ ‘__አባዬ ! _ የእኔ ውድ አባት ። ” እንደማለት ። እናም አባይ ዛሬ እና አሁን ፣ የኢትዮጵያውያን አባት መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው ። በተባረኩ ልጆቹ እየታገዘ።

ዛሬ ኢትዮጵያ አገሬ በውስጥና በውጪ እጅግ የተባረኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአባይ ልጆች  እንዳሏት ፣ ለወዳጆቿ ና ለጠላቶቿ በተግባር እያሳየች ነው ። እፍኝ የማይሞሉትን የነጭ ቱጃሮችና የእኛዎቹን ቅጥረኛ በንዳዎች ፣  የሐሰት ፕሮፖጋንዳ  አክሽፈው ፤ በአደባባይ እውነታችንን በማሳወቅ ፤ የጠላቶቻችንን ሴራ በማጋለጥ የእውነትን ብርሃን ለዓለም ህዝቦች በማሳየት ከኢትዮጵያዊያን ጋር የሚያሰልፉ ፡፡

” ናይል የግብፅ ሥጦታ ሊሆን ይችላል  ። አባይ ግን የኢትዮጵያዊያን አባት ነው ። አባይ እያልን የምናቆላምጠው ፡፡ ” በማለት ፣ ዓለምን ሥለ አባይ እውነተኛ ማንነት የሚሳውቁ  ። …

እውነት   ነው ።አባይ የኢትዮጵያውያን አባት ነው ። አባይ ከፈጣሪ የተሰጠን መጋቢያችን ፤ አባታችን  ነው ። ትላንት ግብፆች ከእኛ ሄዶ  ሰው ላረጋቸው ለመጋቢያቸው ለእኛ አባት ፣  በጎ አድራጎት በቢሊዮን በዶላር የሚቆጠር ብር ሊከፍሉን ይገባ ነበር ። እነሱ ግን ያጎረሳቸውን ጣት ደግመው ደጋግመው ከመንከስ ውጪ አንድም ቀን አመሥግነው እንኳን አያውቁም ። የኢትዮጵያን አፈር እየጠራረገ በመውሰድ ያጎረሳቸውን  አባታችንን ሲያመሰግኑና ልጆቹን ለመካስ አንዳችም በጎ ጥረትም  በታሪክ አጋጣሚ እንኳን አላደረጉም  ። ደጋግመው በሱዳን በኩል  በጦር ሊያስፈራሩን ፤ በኃይማኖት ሽፋንም ሊያቄሉን ግን በተደጋጋሚ መጣራቸውን ታሪክ ዘግቦታል ።

የዛሬውም የግብፅ በአባይ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ  ሰበብ ፣ የምታሥነሳው አቧራ ደግሞ ፣ አንዳችም ሣይንሣዊ መሠረት የሌለውን የክፋት ና የተንኮል  አድራጎቷን የሚያሳብቅ ነው ። ግብፅ ይህንን ተደጋጋሚ የተንኳል መንገድ የምትከተለው ፣   ” ኢትዮጵያ በልፅጋ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ ።” የሚሉ መሪዎች ሥላሏት ነው ።እነዚህ መሪዎቿ ሰማይ ጥግ በደረሰ ምቀኝነት እና በሥግብግብነት ሴራ ላይ ያጠነጠነ ተንኮላቸውን ለሱዳን መንግሥትም አጋብተዋል  ። ምንም እንኳን የሱዳን መንግሥት እንደ ግብፅ መንግሥት ባይቀጥፍም ።

የግብፁ የውሃና መስኖ ሚኒሥቴር በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፊት ቀጥፈዋል ። ይህ ቅጥፈት የሚያመለክተን የግብፅን መንግሥት የተንኳል ና የምቀኝነት  አረማመድ ነው ። አባይ ወይም ናይል ውሃው ተርፎ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የሚገባ ሆኖ ሣለ ” አሥዋን ግድባችን  ውሃ አጥቶ ሀይቅ ሆነ ። ” ብለው በአደባባይ ሲናገሩ   የሰማ ሁሉ ፤ የግብፅ  የአባይ ዲፕሎማሲ በቅጠፈት የተሞላ መንገድን የሙጥኝ እንዳለ   ይገነዘባል ።

ኢትዮጵያ ዛሬም በትህትና አብረን እንልማ ፤ በትብብር እንደግ ፤  የሁላችንም አገር ዜጎች በእኩልነት ይበልፅጉ ነው ። ይህንን ቅን አመለካከትና በጎ አሥተሳሰብ  የግብፅ መንግሥት ለፖለቲካ ግቡ ሲል  ፈፅሞ አይቀበለውም ። ለዚህም ነው ሁሌም በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የግብፅን ህዝብ የሚያደናግረው ።

ግብፅ ቀና መንግሥት ቢኖራት በፈጣሪ ውሃ እንዲህ አትሥገበገብም ነበር ።ስግብግብ እና ብልፅግና ጠል መሪዎች ባይኖሯት ኖሮ ፤ የአባይ ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይቀየር እና ዛሬም  አሥዋን የተሰኘ ግድቧ ፣ ጢም ብሎ ሞልቶ ፣ ” ሐይቅ ሆነብኝ ፡፡ ” በማለት በሐሰት አታወራም ነበር ።የእግዘብሔርን ውሃ ያለሥግብግብነት ከተጠቀምን እኮ አባይ ለሁላችንም በቂ ነው ። እንኳን ለግብፅ ለሜዲትራኒያን ባህርም ይተርፋል ።

የግብፅ መንግሥት ይህንን አሳምሮ ያውቃል ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ብልፅግና ፈፅሞ የማይሹ ለብዝበዛቸው ብቻ የሚያሥቡ የምእራቡ ና የአሜሪካ ቱጃሮች ድብቅ አጀንዳን ለማራመድ ሲል በውሸት ፕሮፓጋንዳው ዘልቆበታል ። አሳሪ ሥምምነት እያለም የቅኝ ገዢዎች ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ይጮሃል ። አሳሪ ሥምምነት ሳይፈረም የኃይል ማመንጫው ውሃ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት መሞላት የለበትም ። ” እያለ  ያሻጥራል ።

ይህ አሳሪ የሆነ በሻጥር ና በተንኮል የተቀነባበረ የሥምምነት ሃሳብ ፣ ለኢትዮጵያዊያን ብልጽግና የማይመች ልማታችንን የሚያደናቅፍ የሴራ እቅዶች በአያሌው የተጎነጎኑበት ነው ። ኢትዮጵያ ይህንን አሳሪ የሚለውን ቃል በራሱ አትቀበለውም ።እንኳን ለትፈርም ይቅርና ! ታሥራ የማታቅን አገር በሉአላዊነቷ ጣልቃ ገብቶ ፤ በራሷ ወንዝ “ ካላሰርኩሽ ?! ፈላጭ ቆራጭ ካልሆንኩብሽ ?! “ ማለት ትልቅ ድፍረት እንደሆንም በዲፕሎማሲ ቋንቋ ደጋግማ ገልጻለች ። በራሷ ልጆች የሰራችውን የኃይል ማመንጫ ግድብ ግብጽ ፤ ” እንደፈለኩ  ልክፈትና ልዝጋ ! ” ማለት በራሱ ግብዝነት ነው ። ይህንን የግብዞች መንገድ ለመከተል የሚፈልግ ልብ ግን ኢትዮጵያዊያን አልፈጠረባቸውም ና የግብጽ ሃሰብ ከንቱ ነው ። አንቀበለውም ፡፡

አባይ ፤ አባት ፤ አጉራሽና አልባሻቸን ለመሆን መቃረቡን በግልጽ እያዩ ፣ ህሊና ቢስ በመሆን ፣አንድ አንድ የኃያላን መንግስታት መሪዎች ፣ ከብዝበዛ አንፃር ብቻ ፣ የአፍሪካን ህዝቦች በመመልከት ፤ በየጊዜው የማስፈራርያ ቃላትና ያልተገባ ማዕቀብ ማድረጋቸውን  ኢትዮጵያውያን አምርረን እንቃወማለን ፡፡ የሱዳን እና የግብፅን ህዝቦች ከቶም የማይጎዳ በሆነው የኃይል ማመንጫ ግድባቸን ፣  ከቶም አንደራደርም ። ሆኖም ለጋራ ብልፅግና በትብብር ከሁሉም የተፋሰሱ አገራት ጋር  ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን ደጋግመን መግለጻችንን ግን ልብ ሊሉት ይገባል  ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ለጆሮ ጠቢው – ካልታወቀ(ች) ገጣሚ (ደራሲዋ(ው)ራሷ(ሱ)ን ብታ(ቢያ)ስተዋውቅ እላለሁ::)

nmap
Next Story

በኢትዮጵያ የጦር አበጋዝ መንግሥቶች አንድ ሽህ አንድ የድንበርና ወሰን ግጭቶች ሃገሪቱን ወደ ማያባራ ጦርነቶች ከቷል!!

Latest from Same Tags

Go toTop

Don't Miss