ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

July 4, 2021
ሰኔ 27፣ 2013
ኤፍ ቢ ሲ
 
አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ዶ/ር አበበች ጎበና ከአገር ባለውለታነት አልፈው ለሰው ልጆች ትልቅ ክብርን በመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡ እናትም አባትም ሆነው ሰው ከወደቀበት ቀና እንዲል አድርገዋል።
 
ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ከጎዳና እያነሱ አጥበው፣ አብልተው፣ አስተምረው በርካታ ልጆችን ለቁም ነገር ማብቃት የቻሉ ጀግና ሴት እንደነበሩ በርካቶች መስክረውላቸዋል።
ክብርትዶ/ር አበበች ጐበና በ1928 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ በግራር ጃርሶ ወረዳ በቶርበን አሼ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ሸበል አቦ በተባለች የገጠር መንደር ተወለዱ፡፡
በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ ገና የ11 ዓመት ልጅ እንዳሉ ትዳር ለመያዝ ተገደዱ፤ ሆኖም የቀረበላቸውን የጋብቻ ጥያቄ በብቸኝነት በመቃወም ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
 
በአዲስ አበባ ስራን ሳይንቁ ከግለሰቦች ቤት ከማገልገል እስከ ምርት ክፍል ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡
ክብርት ዶ/ር አበበች (እዳዬ) በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ አብያተ ክርስትያናትን በማገልገል ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው፡፡
 
በዚህም አጋጣሚ በ1972 ዓ.ም ለመንፈሳዊ ጉዞ በሄዱበት በሀገራችን ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መሰረቱ፡፡
 
ክብርትዶ/ር አበበች(እዳዬ) ባለፉት 41 /አርባ አንድ አመታት/ ብዙ መቶ ሺህ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁነገር ያበቁ ሲሆን በተለይዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰተዋል፡፡
 
በመሆኑም በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና እውቅናዎችን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ በሰብአዊነት አግኝተዋል፡፡
 
ክብርትዶ/ር አበበች(እዳዬ) ድህነትን በተለይም የህፃናት ጉስቁልናን መቅረፍ የሚቻለው “በግለሰብ ደረጃ ለምፅዋት በሚወረወሩ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ሳይሆን በአንድነት በማበር እና ያለንን አቅም በማሳሰብ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በተለይም ሴቶችን ስናበቃ ነው፡፡” የሚል እምነት ነበራቸው፡፡
 
ሆኖም በቅርቡ በኮሮና በሽታ ምክንያት በጳውሎስ ሆሰፒታል በጽኑ ህሙማን ክፍል ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ጠዋት በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የራያና ወልቃይት ጉዳይ የአማራ ብቸኛ ጉዳይ አይደለም – ከአባዊርቱ

Next Story

የኦነግ-ኦፌኮ የሽግግር መንግስት ጉዳይና የአቶ ሬድዋን ሁሴን አስደንጋጭ መልስ

Go toTop