ከደጃዝማች ባልቻ ቤተሰቦች የተላከ መልእክት
እኛ የደጃዝማች ባልቻ (አባነፍሶ) ሳፎ ቤተሰቦች የሆንን፣ በስማቸው በማሕበር የተደራጀን ስንሆን አላማችን ስለሳቸው ሳይነገር የቀረ ካለ ለመናገር፣ስማቸው ያለአግባብ ቢነሳ ለማሰተካከልና መስመር ለማስያዝም ጭምር በመሆኑ፣ ሰሞኑን በአድዋ 125ኛ መታሰቢያ ምክንያት ያላግባብ ስለሳቸው የሚባሉና የሚፈፀሙ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሳቸውን ማንነትና ሰብአዊነት በትክክል ስለማይገልጧቸው፣ ማንኛውም አካል ከዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠብ ግድ እንላለን።
ባልቻ በታሪክ አጋጣሚ፣ ከኦሮሞና ከጉራጌ ቤተሰብ የተወለዱ ቢሆንም፣ የኖሩትና የሞቱት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት መሆኑን ማሳወቅ እንፈልጋለን። በመጀመሪያ፣ የጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት አባት የሆኑትን ታላቁን ንጉሠ ነገስት አፄ ምኒልክ ባልተገኙበት ባልቻን ነጥሎ ማስቀመጥ ለባልቻ ክብር አይሆንም። በተጨማሪ ባልቻ ዘረኝነት የሚፀየፉና በእምነታቸውም የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነውና፣ ሁሉም በስራው እንጂ በቆዳው ቀለም፣በሐይማኖቱ ምክንያት ወይም በዘሩ አይዳኝም ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። የአድዋ 125ኛው የድል በዓል በኢትዮጵያ መዲና ደምቆ ሲከበር በማየታችን እንደ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተሰማን ደስታ ወሰን የለውም። ነገር ግን በማህበራዊ ገፆች ላይ ስለ ደጃዝማች ባልቻ አወዛጋቢ ፅሑፎች እየተፃፉ በማየታችን አንዳንድ ነገሮችን ግልፅ ለማድረግ ተገደናል።
የጥንት አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩልን አገራችን ዛሬ በዘርና በጎሳ ተከፋፍላ ማየት በጣም የሚያሳዝንና ልብ የሚያደማ ነው። ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በሁለቱም የጣልያን ጦርነቶች የተፋለሙትና ለአገራቸው የተሰውት ለሚወዷት አንድ አገራቸው ሆኖ ሳለ ዛሬ የእርሳቸውን ማንነት ከኢትዮጵያዊነት በማውረድ “ባልቻ ጉራጌ ናቸው” ወይንም “ባልቻ ኦሮሞ ናቸው” በማለት ለእርሳቸው በማይገባ ሁኔታ ሲነገር መስማት በጣም ያሳፍራል። ደጃዝማች ባልቻ የተወለዱት ሸዋ ውስጥ አገምጃ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ሲሆን አባታቸው ኦሮሞ እናታቸው ጉራጌ
ናቸው። ባልቻ የሳፎ ልጅ ሲሆኑ ከሳፎ ጀምሮ ያሉት፤ ሮባ፣ ሳንኩር፣ ግቦ፣ ላቅቻ፣ ከቶ፣ እሮቢ፣ ይዶኖ፣ ወዲቱ፣ ሶዶ፣ ቱለም፣ ዳጪ፣ ቦረና እያለ ይቀጥላል። ይህ የት ተወለዱ ለሚለው መልስ ይሁን እንጂ የባልቻን ኢትዮጵያዊ መሆን አንዳችም ቅንጣት ያህል አይቀንሰውም። ዛሬ ባልቻ ከመቃብር በላይ መናገር ቢችሉ ማንነታቸው ንፁህ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ እንዳልሆኑ ጮኸው በተናገሩ ነበር። ስለዚህም ነው እኛ የደጃዝማች ባልቻ የቅርብ ዘመዶችና ቤተሰቦች ባልቻ አባነፍሶን ወክለን የእርሳቸውን ድምፅ ለማስተጋባት የተገደድነው።
ደጃዝማች ባልቻ ከአስራአራት ዓመት እድሜያቸው ጀምረው እንደ አባት ሆነው አሳድገው ለክብር ያበቋቸው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው። ዛሬ ስለባልቻ ማንነት ለመናገር በመጀመሪያ የአፄ ምኒልክን እምዬነት፣ አባትነትና እና ትልቅነት ማመን ግድ ይላል። የአድዋ ድል መታሰቢያ በመስቀል አደባባይ ሲከበር የደጃዝማች ባልቻ ሳፎን ምስል በአደባባይ ሰቅሎ የእምዬ ምንሊክን ምስል መንፈግ ዋነኛው የአድዋ አውራን መካድ ብቻ ሳይሆን የማይገባ ታሪክን ከመፍጠር ምንም አይለየም። እምዬ ምኒልክ ከሌሉ አድዋ የለም። እምዬ ምኒልክ ከሌሉ ባልቻ የሉም። ደጃዝማች ባልቻ ለአንድ ኢትዮጵያ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩዋትን አገር ዛሬ ለእርሳቸው በማይመጥን ሁኔታ የዘር የብሄርና የፖለቲካ መሳሪያ መጠቀሚያ ሲያረጏቸው ማየት በጣም ያማል። ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶን፣ እኛ የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ቤተሰቦች ብቻ ሳንሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ የሚሆናቸው ንፁህ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ፣ የእርሳቸው ዋና መንስኤ የሆኑት የሚወዷቸውና ያሳደጏቸው እምዬ ምኒልክ እንደሆኑ የደጃዝማች ባልቻ ቤተሰብ ግልፅ ማድረግ ይፈልጋል።
የአድዋ ድል መታሰብያ በሚከበርበት ሳምንት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አገልግሎትና በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ስለ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሲዘከር ሰምተናል። ደጃዝማች ባልቻ ለአገራቸው ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ ያደረጏቸው ጀብዱዎች እንዲወሳና ታሪካቸውም ለትውልድ እንዲነገር በመደረጉ የደጃዝማች ባልቻ ቤተሰብ ትልቅ ምስጋናውን ያቀርባል። ስለ ደጃዝማች ባልቻ ከዘርና ከብሄር ነፃ ይሆነ ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም ስለዳግማዊ አፄ ምኒልክ ታላቅነት ከላይ በተገለፁት ነጥቦች መካተቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣በተለያዩ የሚዲያ መድረኮች ላይ ስለደጃዝማች ባልቻ በተደረጉ ዝግጅቶች አንዳንድ ልናልፋቸው የማይገባን ጥቃቅን የታሪክ ስህተቶችን ቤተሰቡ ስለ ታዘበ በእነዚህ ስህተቶች ላይ እርማት ለመስጠት ተገዷል።
በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አገልግሎት ስለደጃዝማች ባልቻ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ከዚህ በታች የሚከተሉት እርማቶች እንዲካተቱ እናሳስባለን።
- ደጃዝማች ባልቻ በአምባላጌ ጦርነት ላይ ከፊትወራሪ ገበየው ጋር አብረው ተዋግተዋል የተባለው ትክክል አይደለም። የአምባላጌ ጦርነት በተደረገበት ወቅት በጅሮንድ ባልቻ (ደጃዝማች ከመሆናቸው በፊት የነበራቸው ሹመት) ከአፄ ምኒልክ ጋር በመሆን ገና መንገድ ላይ ነበሩ። በጅሮንድ ባልቻ፣ በጅሮንድ እንደመሆናቸው ሁሉ እርሳቸውና በእርሳቸው ስር የሚገኘው ጦር ሁልጊዜ ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ጋር አብሮ ነው የሚጏዘው። ንገሠነገስቱ በመንገዳቸው ላይ የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውም መሣሪያና ቁሳቁሶች ጠባቂነቱ፣ የቤተመንግስቱ ግምጃቤት ኃላፊ በነበሩት በበጅሮንድ ባልቻ ስር ነበር። ለምሳሌ ንጉሠነገሥቱ በሚያደርጉት ጦርነት ጉዞ ላይ ቀኑን ሙሉ ተጉዘው በቀኑ መጨረሻ ላይ እረፍት ለማድረግ ሰፈር በሚያደርጉበት ጊዜ ቀደም ብሎ ሄዶ የሚሰፍሩበትን አካባቢ በመቃኘትና ንጉሠንገሥቱ የሚያርፉበትን ድንኳን ማዘጋጀት የደጃዝማችባልቻ ኃላፊነት ነበር። አፄ ምኒልክ ከአምባላጌው ጦርነት በኃላ፣ የመቀሌውና የአድዋ ጦርነት ከመደረጉ በፊት፣ በአምባላጌው ጦርነት አዛዥ ከነበሩት ከራስመኮንን እና ከሌሎች የጦር መሪዎች ጋር በተገናኙበት ጊዜ፣ አፄ ምኒልክ የአምባላጌውን ድል እንደሰሙና ከዚያም በጅሮንድ ባልቻና ሊቀመኳስ አባተ፣ፊትወራሪ ገበየው አድርገውት በነበረው ጀግንነት ምን ያህል ወኔያቸው ተቀስቅሶ እንደፎከሩ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።
- ደጃዝማች ባልቻ እራሳቸውን አልገደሉም። ደጃዝማች ባልቻ በሁለተኛው የጣልያን ጦርነት ከጄኔራል ግራዝያኒ እንዲይዛቸው ከመጣው የባንዳና የጣልያን ጦር ጋር እስከመጨረሻ ተዋግተው፣ በመጨረሻ ሊይዛቸው የመጣውን የጣልያን ወታደር ገድለው በጥይት ተደብድበው እንደተገደሉ በብዙ የታሪክ መፅሐፍት ላይ ተፅፎ ይገኛል።
- የደጃዝማች ባልቻ ወንድም ፊታውራሪ ወልደፃድቅ ወደ መቃዲሾ ሱማሊያ በእስር ተወስደው እዚያው በእስር ላይ የሞቱት በአድዋ ጦርነት ጊዜ ሳይሆን በሁለተኛው የጣልያን ጦርነት ነበር።
- የደጃዝማች ባልቻና የአፄ ኃይለሥላሴ ቅራኔ መነሻ በልጅ እያሱና በተፈሪመኮንን መሀል በነበረው ቅራኔ የተነሳና፣ ደጃዝማች ባልቻ ለልጅ እያሱ በማገዛቸው ነው የተባለው የተሳሳተ ነው። በደጃዝማች ባልቻና በአፄ ኃይለሥላሴ መሀል የተፈጠረው ቅራኔ ብዙ ክፍሎች ሲኖሩት አንዱ ግን በወቅቱ በልዑል ራስተፈሪ (በኃላ አፄ ኃይለሥላሴ) እና ንግስት ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክ መሀል ተጀምሮ በነበረው አለመስማማት፤ በንግስት ጎራ በመሰለፋቸው ምክኒያት ነበር።እንደውም ደጃዝማች ባልቻ በጌታቸው በአፄ ምኒልክ ከተሰጣቸው የሲዳሞ ግዛት ለመጀመርያ ጊዜ አንስተው ያጋዟቸው ልጅ እያሱነበሩ። ልጅ እያሱ በሸዋ መኳንንት ከስልጣናቸው እንዲለቁ ሲደረግ ደጃዝማች ባልቻ በአዲስ አበባ ደጅ ይጠኑ እንደነበርና ልጅ እያሱ ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት ወደ ሀረር ሲሄዱ ይዘዋቸው እንደሄዱ፣ እዚያም እያሉ ልጅ እያሱ ከስልጣን መውረዳቸው ሲሰማ፣ መጀመርያ እራሳቸውን ከልጅ እያሱ በማራቅ ከከተማው ቅርብ ወደሚገኝ ተራራ በመሄድ ራሳቸውን ከእያሱ እንዳገለሉና በኃላም እያሱ ሀረርን ለቀው ሲሄዱ ተረብሾ የነበረውን የሀረር ከተማ እንዳረጋጉ ተፅፎ ይገኛል።
ሌላው በMarch 6, 2021 በEthio 360 ላይ ከአቶ አቻምየለህ ታምሩ ጋር በተደረገው ቃለ መጠይቅ ላይ፣ አቶ አቻምየለህ፣ ደጃዝማች ባልቻን በማይመጥን መንገድ የባልቻን ማንነትና በአድዋ ጦርነት ላይ የነበራቸውን ድርሻ አሳንሰው ለማቅረብ በመሞከራቸው በቤተሰቡ ስም የተሰማንን ቅሬታ ልንገልፅ እንወዳለን።
የአድዋ ድል መታሰበያ በመስቀል አደባባይ ሲከበር የተደረገውን የደጃዝማች ባልቻ ቤተሰብ ቅር መሰኘቱን ከላይ ስለጠቀስነው መድገም አያስፈልግም። በእርግጥም የአድዋ ጦርነት ላይ ባልቻ በጅሮንድ በነበሩበት ዘመን፣ እምዬ ምኒልክ ባልቻን ለማሳደግ ቤተመንግስት በወሰዱበት ማግስት፣ ክርስትና በማንሳት የክርስትና አባት የሆኗቸው ራስ መኮንንን ረስቶ፣ ባልቻን በነጠላ ማሞገስ አይገባም። ሌሎችም በጊዜው የነበሩ ታላላቅ ሰዎችን መዘንጋት ከታሪክ ጋር ያጣላል። ደጃዝማች ባልቻ በጅሮንድ በነበሩበት በአድዋ ጦርነት ወቅት፣ ሥልጣናቸው ከበጅሮንድ በላይ የሆኑና ለአገራቸው የደሙ ደጃዝማቾች፣ ፊታውራሪዎችና ራሶች በጦር ብዛትም ሆነ በሹመት ብዙ የነበሩ እያሉ፣አንድ ባልቻን ነጥሎ ማሞጋገስና ብቻውን ማወደስ ደጃዝማች ባልቻን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ከማድረግ በላይ ምንም ትርጉም የለውም። ሆኖም ከጌታቸው ከአፄ ምኒልክ የተሰጣቸውን እና የነበራቸውን ስልጣን ክብርና ሀላፊነት ደረጃቸውን በማኮሰስና እርሳቸውን በማይመጥን ሚዛን ከማይገባቸው ሰዎች ጋር ማወዳደር በፍፁም የሚገባ አይደለም።
ደጃዝማች ባልቻ በጅሮንድ በነበሩበት ጊዜ የንጉሠነገሥቱ ጦር መሳሪያና ግምጃቤት ኃላፊ የሚያዘውን ጦር ከመምራታቸው ባሻገር፣ በመንግስት ጦር ስር ሆኖ ለየአገረገዢው የሚደለደል ቁጥሩ ብዙ ሺዎች የነበሩት ባሩድቤት ተብሎ ለሚጠራው ጦር ከ1874 ጀምሮ የጦሩ አዛዥ ነበሩ። ይህንንም ጦር በመምራት ከአድዋ ጦርነት በፊት በርካታ ጦርነቶች ላይ በመዋል ለአገራቸውና ለንጉሠነገስታቸው ከፍተኛ መስዋእትነት ያበረከቱትን ጀግና፣ ከአድዋ ጦርነት ዋዜማ ላይ በመቀሌ ጦርነት ከእቴጌጣይቱ ትእዛዝ ተቀብለው የጣልያንን ጦር ምሽግ በመድፍና በመትረየስ ያረበደበዱትን እና በመጨረሻም የጣልያን ጦር ነጭ ባንዲራውን እያዉለበለበ እጁን ሲሰጥ በምሽጉ በመግባት የጣልያንን ባንዲራ አውርደው፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ የሰቀሉትን አባነፍሶን፣ በዛሬ ጊዜ ከሚገኙ ዝቅተኛ የጦርመኮንኖች ወደታች አውርዶ ማሳነስ በእውነቱ ከሆነ በጣም ያስተዛዝባል፣ በጣምም ቅር ያሰኛል። ይህ ከላይ የጠቀስነው ጀግንነት እንዲሁም ሀላፊነት የተፈፀመው ከአድዋ ጦርነት በፊት ሆኖ ሳለ ባልቻ በአድዋ ላይ አሳይተውት የነበረውን ጀግንነትና የነበራቸውን ማዕረግ በማኮሰስ የባልቻ አባነፍሶን ማንነት መካድ ትክክል እንዳልሆነ እኛ የደጃዝማች ባልቻ ቤተሰቦች ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን።
የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሳፎ የቤተሰብ ማህበር። እናመሰግናለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።