ማህበራዊ ንቅናቄ የፓርቲ ፖለቲካ ሚናን እና ተልእኮን አይተካም! – ጠገናው ጎሹ

January 5, 2020
ጠገናው ጎሹ

በቅድሚያ ለዚህ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ ያሬድ ሃይለማርያም “የመጫወቻ ሜዳቸውን ያጠበቡት እስክንድር እና ጀዋር” በሚል ርዕስ ፅፎ ያስነበበው ፅሁፍ መሆኑን ግልፅ ላድርግ ። የሂሳዊ እይታ (critical view) አስፈላጊነት ወይም ተገቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ ያሬድ ያለማቋረጥ ለሚፀፋቸው አስተያየቶችና በትንታኔ ለታገዙ መጣጥፎቹ ተገቢውን አድናቆትና ከበሬታ ከሚሰጡ የአገሬ ሰዎች አንዱ ነኝ ።

የአስተያየቴ ዓላማ መሠረታዊና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን መሆን ካለበት እንደ ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ያሉ በንድፈ ሃሳብ ብቻ እና ከሸፍጠኛ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ትኩሳት ጋር በሚወጣና በሚወርድ የሞራልና የፖለቲካ ሰብእና ሳይሆን በእውነት ስለ እውነት ፀንተው የሚቆሙ ወገኖች ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውን (social movement) ወደ የፓርቲ ፖለቲካ (party politics) ማሸጋገራቸው ወቅቱና ሁኔታው የሚጠይቀው ወይም የግድ የሚለው በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ለማለት እንጅ ከፀሃፊውና ከአንባቢዎች ጋር አላስፈላጊ የሃሳብ መወራወር ለመፍጠር  አለመሆኑም ግልፅ ይሁንልኝ ።

ሁሉም ዜጎች በሠለጠኑበትና በሚፈልጉት የሙያ ወይም የሥራ መስክ ተሠማርተው በነፃነትና በፍትህ ጥላ ሥር የሚተዳደሩበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጨርሶ በሌለበት አገር ውስጥ ከማህበራዊ ንቅናቄ ወደ የፓርቲ ፖለቲካ አራማጅነትና መሪነት መሸጋገር “ሜዳን ማጥበብ ነው” የሚለው መከራከሪያ የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ ጨዋታን (በተለይ ደግሞ የእኛን) ጨርሶ  አያሳይም።

እንደማነኛውም የአገሩ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የአገሬ ሰው የጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የእስክንድር ነጋንና የባልደረቦቹን የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበት እና ዘላቂ ሰላምና ልማት/እድገት የሚረጋገጥበት  ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ የሚያካሂዱትን ትግል በተመለከተ የሚሰነዝሩ አስተያየቶችን እከታተላለሁ ። አስተያየቶቹ አዎንታዊም ይሁኑ አሉታዊ  ሃሳብን ከመግለፅ መሠረታዊ መብት አንፃር ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የፖለቲካ ባህል ለመለወጥ (ለማዘመን) ከባድና  ውስብስብ ፈተና እንዳለብን አውቀን ይህንኑ የሚመጥን የጋራ ትግል ማካሄድ እንዳለብን   ስለሚነግሩን ይጠቀሙናል እንጅ  ከቶውንም  አይጎዱንም። የሚጎዱን ሆን ብለን ስናንሻፍፋቸው ወይም ካለማወቃችን መሆኑን አውቀን ከማስተካከል ይልቅ ጋግርታም በሆነ የእልህ ፈረስ መጋለባችን ስንቀጥል ነው ።

እስክንድር ዴሞክራሲያዊትና የእኩልነት አገር ትኖረን ዘንድ ከክብርት ባለቤቱና ከውድ ልጁ ጋር ለዓመታት የከፈለውን መስዋእትነት እንደማነኛውም የአገሩ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የአገሬ ሰው ስለምከታተል በሚገባ አውቀዋለሁ ። በግል (in person) ባላወቀውም።

“የግፍ አገዛዝ ይብቃና ዴሞክራሲያዊት በሆነች ፣ እኩልነት በተረጋገጠባትና የጋራ ብልፅግና እውን በሚሆንባት አገር ውስጥ እንኑር” ብሎ መጠየቅ ወንጀል ሆኖ የፖለቲካ ሥልጣንን ለግልና ለቡድን ፍላጎትና ጥቅም ማርኪያነት በማዋል ተልእኮ ህሊናቸውን (ሰው የመሆን ትልቁ መለያቸውን) ጨርሰው ባረከሱ ፖለቲከኞቸ (ገዥዎች) እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው እጅ ሥር ወድቆ የቁም ሰቆቃ መቀበል ለመግለፅ የሚያስቸግር ህመም እንዳለው ከታዳጊ ወጣትነት ተሞክሮ ስለማውቀው እስክንድርና  በርካታ ንፁሃን ወገኖች በተደጋጋሚ የደረሰባቸውን ግፍና ሰቆቃ ሳስብ የሚሰማኝ ስሜት የተደበላለቀ ነው።

ድብልቅልቅ ስሜት ለምንና እንዴት ?

በአንድ በኩል ከዚያ ሁሉ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት በኋላም “እንወዳታለን የምንላት አገር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተረገገጠባትና ዜጎቿ ሁሉ ተከብረውና ተከባብረው የሚኖሩባት እስክትሆን ድረስ ጨርሶ እረፍት የለንም” የሚሉ የነፃነትና የፍትህ ተሟጋች ዜጎች (ወገኖች) ድሃዎች  አለመሆናችን የሚፈጥረው ስሜት እጅግ ጥልቅና ትውልድ ተሻጋሪ  ነው።

በሌላ በኩል ግን ፦

ሀ)   ብልፅግና ብለው በሰየሙት ኢህአዴጋዊ የሸፍጥ ፖለቲካ አካሄድ በግርግር ምርጫ አሸነፍን ብለው ከመጡበት ሩብ ምዕተ ዓመት እጥፍ በላይ (60 ዓመት) ብቸኛ አሸናፊ ሆነው ለመዝለቅ የቤት ሥራቸውን ሠርተው እንደጨረሱ ከኢህአዴግ የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታ ጨርሶ የተገላገለ መስሎት ተስፋ አድርጎ ለነበረው መከረኛ ህዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል በግልፅና በቀጥታ ሲያረዱት መስማት የሚፈጥረው መጥፎ ስሜት ከቶ ቀላል አይመስለኝም

ለ) የማጨበርበሪያ ስያሜ የተሰጠውን ብልፅግናን ህወሃት ካስለከፋቸው የአሽከርነት ፖለቲካ ልክፍት መላቀቅ በተሳናቸው በአዴፓ እና ደህዴን ፖለቲከኞች አጃቢነት የሚመሩት የኦዴፓ ፖለቲከኞችን አካሄድ ከስሜት ወጥቶ ልብ ለሚል ሰው የረቀቀ ሚስጥርነት የለውም።

  • እናም ገዳይና ዘራፊ የነበረውን የኦነግን ተዋጊ ቡድን (ሠራዊት) ተሃድሶ ሰጠሁ (ተሃድሶ ምን እንደሚሆን መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም) በሚል የመንግሥታዊ መዋቅሩ አካል ያደረገ  
  • እንደ ጀዋር ያሉ እኩይ የፖለቲካ ሰብእና ያላቸውን ግለሰቦች በተዘዋዋሪ የፖለቲካ ጨዋታው አካል እንዲሆን ያስደረገ
  • ኦሮሙማ በሚል ኦሮሞ በታሪክ አጋጣሚ የረገጠው መሬት ሁሉ የኦሮሞ ነው የሚል አደገኛ ቅዠት ውስጥ የሚገኝ ፣
  • “የሰባበሩንን ሰባብረን አዲስ አበባን ተቆጣጠናልና ደስ ይበልን” በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ የሚል
  • የጭቆና እንጅ በጎ የጋራ ታሪክ የለንም በሚል አደንቋሪና አደገኛ ትርክት ትውልድን በመንጋ አስተሳሰብ የሚያደነቁር  
  • ትውልድ ለዘመኑ የሚመጥን (የሰለጠነ) ፖለቲካ ሥራ ከመሥራት ይልቅ “የኩሽ ኤምፓየርን መመሥረት” በሚል አደገኛ ቅዠት ውስጥ እንዲቃዥ በማድረግ ሥራ ላይ የተጠመደ
  • የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚቆጣጠሯት ኢትዮጵያ ካልሆነች ድራሿ ይጥፋ በሚል የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኛ የተበከለ የኦሮሞ ፖለቲካ የሚፈጥረው ስሜት አያስጨንቅም ማለት እራስን ማታለል ነው።

ሐ) የተነሳበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አጀንዳን ለሸፍጥ ተሃድሶ ፖለቲካ ሰለባነት (ልጣፍነት/ተለጣፊነት) አስረክቦ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ “ለወጡ እንዳይደናቀፍ ብለን” በሚል እጅግ የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብ አዙሪት ውስጥ የሚዳክረው የተቃውሞው ጎራ ( ተፎካካሪ እያለ እራሱን የሚያታልለው) ፖለቲከኛ ጉዳይ ስሜትን አይጎዳም ማለት ውሸት ነው የሚሆነው ።

መ) ፊደል ከመቁጠር ጀምሮ እስከ ልሂቅነት ተምሬያለሁ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል  ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚመጥን የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት/ህብረት) እንዲመሠረትና ጠንክሮ እንዲወጣ የሚያስችል አስተዋፅኦ ማድረግ ሲገባው ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች እያዘጋጁ የሚያቀርቡለትን አጀንዳና ትርክት በማመንዠክ ክፉ ልማድ የመጠመዱ ጉዳይ ስሜታችንን የማያሸማቅቀን ከሆነ ስለ ዴሞክራሲያዊት አገር  እውን መሆን መናፈቃችን  ቅዠት ነው የሚሆነው።

አዎ! ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረውንና በእልፍ አእላፍ ንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና ደም የተጨተማለቀውን  ሥርዓተ ኢህአዴጋቸውን ከመቃብር በመመለስ ቅርፅና ስም እየቀየሩ (ውህዱንና አገር አቀፉን ብልፅግና ልብ ይሏል ) “ከእኛ ወዲያ በንስሃ የነፃና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋጋሪ ለአሳር ነው” የሚል ድንቅ ድርሰታቸውን በጥሩ አንደበታቸው ሲደሰኩሩለት (ሲደሰኩሩበት) ፊደል የቆጠረ (የተማረ) መሆኑ እስከሚያጠራጥር ድረስ አዎንታዊ ምላሹን በውዳሴ መነባንብና በጭብጨባ አጅቦ አዳራሹን ቀውጢ ሲያደርገው መታዘብ አንገት ያስደፋል ።

ለዚህ ነው በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን እያወቅን እነ እስክንድር ከማህበራዊ ንቅናቄ ወደ  የፖለቲካ ፓርቲነት መሸጋገር የለባቸውም የሚል መከራከሪያ ሃሳብ መሰንዘር መብት ቢሆነም አሳማኝነቱ ግን  ብዙም የሚያስኬድ የማይሆነው ።

ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መሸጋገር “ደጋፊዎቻቸውን እያሳጣቸው ነው” የሚለው ደግሞ ደምሳሳና ስሜታዊነት የተጫነው የፖለቲካ እይታ ነው ። ግለሰቦች መሬት ላይ ካለው ፈታኝ እውነት አንፃር ሳይሆን በእራሳቸው ምክንያት ሊሸሹ ይችላሉ ። ከደጋፊነቱ የሚሸሺ ከመጀመሪያውም የምር ደጋፊ ያለመሆኑን ነው የሚያረጋግጠው እንጅ ከማህበራዊ ንቅናቄ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የመሸጋገርን ድክመት አይደለም።

እንደ አሸን የፈሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተብየዎች ባሉበት አገር ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ለምን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ/ትክክል ነው ። እነዚህ እንደ አሸን የፈሉና በእውነተኛ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ጨርሶ የሌሉ  የፖለቲካ ፓርቲ ተብየዎች በሚተራመሱበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ይሆን ዘንድ እንቅስቃሴያቸውን ከማህበራዊ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት በማሸጋገር  የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል  የተሳካ እንዲሆን ተጨማሪ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ ከመገኘት ጋር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ዜጎችን (ወገኖችን) ማባረታታት ባንፈልግ እንኳ ጥረታቸውን ማንኳሰስ () ማድረግ ግን የአገር (የወገን) ጉዳይ ከምር ያሳስበኛል የሚል ግለሰብ ወይም ቡድን ባህሪና ተግባር ሊሆን አይችልም ።

አዎ! ትንናንት ከነበረበት የአስተሳሰብና የመርህ ልዕልና ላይ ፀንቶ መቆም እያቃተው ለማመን በሚያስቸግር አኳኋን እየተንሸራተተ እራሱን  ለሸፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (ብልፅግና) ፖለቲኞችና እና ለጎሳ/ ለመንደር/ ለቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞች ሰለባነት አሳልፎ የሚሰጠው ፖለቲከኛ እና ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው የአገሬ ሰው በበዛበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ እስክንድርንና  የሚያራምደውን ዕውነት ፣ ዓላማና  ተልእኮ የእኛም ነው ብለው የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ወገኖችን  የፖለቲካና የሞራል ሰብዕና ከሚያደንቁ ወገኖች  አንዱ ነኝ።

እስክንድር ባለፈው ዓመት መገባደጃ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን  በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጋር ያደረገውን ውይይት ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ መዘመን ምሥጋና ይግባውና በጥሞና ተከታትያለሁ ።

ከማህበራዊ ንቅናቄ ወደ የፓርቲ ፖለቲካ ትግል (party politics) ለመሸጋገር የግድ የሚሉ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች መኖራቸው የሚያጠያይቅ አይመስለኝም ። እነ እስክንድር የአዲስ አበባ ኗሪ ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ  አዲስ አበባ የማንም ልዩ ጥቅም ፈላጊ ፖለቲከኛ  ታጋች  (hostage) ልትሆን ፈፅሞ አይገባም የሚለውን የአደራ ቃል ተረክበው ባልደራስ ብለው በሰየሙት የሲቭል ም/ቤት አመካኝነት መታገል ሲጀምሩ ተረኞች ነን በሚል ሁሉንም የመቆጣጠር አባዜ የተጠናወታቸው  ሸፍጠኛ የኦዴፓ / ኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞችን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ  ጫና እና ወከባ  ቀን በቀን መጋፈጥ ነበረባቸው።

ሥልጣን  ላይ  የሚወጡ ፖለቲከኞችን የፖለቲካ ትኩሳት እየለካ ክስ የሚመሠርተውና ፍርድ የሚፈርደው የፍትህ ሥርዓት ተብየ የባልደራስ አመራር አባላትን  በአሸባሪነት እጠረጥራቸዋላሁ በሚል እስር ቤት አጉሮ የአካልና የሥነ ልቦና ጉስቁልና ሰለባ የዳረገበትን መሪር እውነት በጥሞና የሚያጤን ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው አንድ እጅግ ግዙፍና ግልፅ ሃቅን ለመረዳት አያቸገርም ። ይህ የማያወላዳ እውነት ጠንካራና ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ (ድርጅት) ወይም የድርጅቶች ትብብር በሌለበት  የፖለቲካ አውድ ውስጥ ማህበራዊ ንቅናቄ በራሱ የሚፈለገውን መሠረታዊ  ለውጥ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ   እውን ለማድረግ ያለመቻሉ ወይም ያለማስቻሉ ጉዳይ ነው። በለውጥ ትግል ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው   ከ1960ዎቹ ጀምሮ እጅግ ግዙፍ ህዝባዊ እምቢተኝነቶች (ማህበራዊ ንቅናቄዎች) በሸፍጠኛና አምባገነን ገዥ ቡድኖች እየተኮላሹ የመጣንበትና ይኸውና ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በኋላም አዙሪቱን ሰብሮ መውጣት  አልሳካልን ብሎ በከባድ ትርምስ ውስጥ የምንገኘው በዘላቂ ዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መርህና ዓላማ መሠረት ታግሎና አታግሎ የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ፓርቲ (ድርጅት) መፍጠርና ማብቃት ባለመቻላችን ነው ።

በህዋሃት የሚመራው የኢህአዴጋውያን ገዥ ቡድን የመከራና የውርደት ሥርዓት አብቅቶ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን መሆን አለበት በሚል የተካሄዱ የማህበራዊ ንቅናቄ ትግሎችና የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ ግዙፍና መሪር ነው ።

ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች የማንነትን ጨምሮ በሁለንተናዊ የቀውስ ማእበል ክፉኛ ሲናጥ የነበረውን ወጣት ትውልድ ቄሮ ፣ፋኖ፣ ኤጀቶ ፣ ዘርማ፣ ወዘተ በሚሰኙ ኢ-መደበኛ ማህበራዊ ንቅናቄዎች (social movements) የህወሃት የበላይነት ከተወገደ በኋላስ? ብሎ ለመጠየቅ ፋታ በሚነሳ አኳኋን ለሥልጣናቸው መቆናጠጫና ማጠናከሪያ ከተጠቀሙባቸው በኋላ አሁን ደግሞ 50ና 60 ዓመታት ለመግዛት ለሚያስችላቸው “ታሪካዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ”  አጃቢያቸው (መጫወቻ ካርዳቸው) ለማድረግ ያስችለናል በሚሉት ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል ። በየአዳራሹ እየሰበሰቡ በጅምላ ( በመንጋ) እንዲያስብ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳቸውን እየጋቱት ይገኛሉ። ይህ እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዋና ተዋናይነት ሲተወን ማየትና መስማት ደግሞ ህሊናን በእጅጉ ይፈትናል ።

አዎ! “መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ በማካሄድ ለዘመናት ከዘለቅሁበት የመከራና የውርደት ህይወት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እገላገላለሁ” የሚለው የመከረኛው ህዝብ ተስፋ  በለየለት የፖለቲካ  ሸፍጥ በተበከለ የኢህአዴጋውያን ተሃድሶ (ብልፅግና) አካሄድ ሲጨናገፍ (ሲኮላሽ) ከማየት የባሰ ህሊናን የሚፈታተን ጉዳይ የለም።

ለዚህ ሁሉ አገገመ (እየተሻለው ነው) ሲባል መልሶና መላልሶ የሚያገረሽ ክፉ የፖለቲካ ህመም ምክንያቶች በርካታ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከዋና ዋናወቹ (ወሳኝነት ካላቸው) ምክንያቶች አንዱ ከማህበራዊ ንቅናቄዎች (social movements) እና ከብሶት/ከቁጭት እምቢተኝነቶች የሚመነጩ ግዙፍ ግብአቶችን የፖለቲካ ሥልጣንን ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከእኩይና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድን(ች) በመንጠቅ ዴሞክራሲያት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚችል/ችሉ የፖለቲካ ፓርቲ/ዎች ለማቋቋምና ለማብቃት አለመቻላችን ነው ።   ለዚህ ነው ፀሃፊ ያሬድ ሃይለማርያም የእነ እስክንድር ነጋ ከማህበራዊ ንቅናቄነት ወደ የፖለቲካ ፓርቲነት መሸጋገር “መጥበብ ነው” የሚለው ደምሳሳ መከራከሪያ ጨርሶ ስሜት የማይሰጥ ነው የምለው።

ፀሃፊ ያሬድ እስክንድርና ባልደረቦቹ በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ዋጋ በሚያስከፍለው የሸፍጠኞች የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ሆነው ከማህበራዊ ንቅናቄነት ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት ለመሸጋገርና መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን እንዲሆን አጥብቆ በመጠየቅ ላይ ካለው የኢትዮጵያ ጋር በመሆን የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ” እኔ ብሞክረው ችግሩ ይቃለላል በሚል”  ብሎ የገለፀበት መንገድ ለምንገኝበት መሪር ፖለቲካዊ እውነታ ጨርሶ የሚመጥን አይደለም። በተቻለን መጠን የግል ስሜታችንን እና ፍላጎታችንን (emotion and intention) በመሬት ካለው መሪር ሃቅ በሚነሳ ምክንያታዊነት አደብ ብናስገዛው መልካም ይመስለኛል።  

“የፖለቲካ መሪ ሲኮን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ይቀንሳል” የሚለው እጅግ ደምሳሳ፣ እንጭጭና አሳሳች ፖለቲካዊ ድምዳሚ ነው ። በጥቅሉ ሳይሆን እውነት ሊሆን ከሚችልበት ሁኔታ (context) ጋር ቢገለፅ እንኳ ጥሩ ነበር ። በእስክንድር አካሄድ ደስተኛ ላይሆኑ የሚችሉ የውጭ አገር መንግሥታትና ሌሎች አካላት ሊኖሩ የመቻላቸው ጉዳይ የፖለቲካ እውቀት ሀ ሁ ነው።

ህወሃት/ኢህአዴግን ለቤተ መንግሥት በማብቃት ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከዘመኑ ትውልድ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ግንባር ቀድም አድርገው ሲያሞካሹ የነበሩ የውጭ አገር መንግሥታት አሁን ደግሞ በህዝብ የአልገዛም ባይነት አስገዳጅነት በተሃድሶ ስም ሥልጣኑን የተረከበው የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ጠቅላይ ሚኒስትር የእነርሱን የባህር ማዶ ብሔራዊ ጥቅም ለማስቀጠል ወይም ይበልጥ ለማጠናከር ይጠቅማል (ያገለግላል) ብለው እስከ አመኑ ድረስ ከህዝብ በሚገኝ ድጋፍ የእርሱን (የጠቅላይ ሚኒስትሩን) ሥልጣን ከምር የሚገዳደርን የፖለቲካ ድርጅት ይደግፋሉ ማለት የፖለቲካ ቂልነት ነው።  ይህን አይነቱን የተለመደና ጨርሶ ልናስወግደው የማንችለው የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ ጨዋታን እየጠበቅን (እየተከተልን) ከሆነ የእራሳችን ነፃና ፍትሃዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የምናስበውና የምንቀሳቀሰው ቅዠት ውስጥ እንጅ እውነተኛ ራዕይ ላይ አይደለንምና በጊዜ ለመንቃት እንሞክር ።

የዓለም መንግሥታትና ሌሎች አካላት አያሌ መስዋእትነት ከከፈሉና አሁንም በመክፈል ላይ ከሚገኙ እንደ እስክንድር ከመሰሉ የዴሞክራሲ አርበኞች ጎን ከምር የሚቆሙት የእነ እስክንድር ትግል አልፋና ኦሜጋ ዜጎቿ ከግፍ/ከሸፍጥ የፖለቲካ ሥርዓት እና ከምፅዋዕት ለማኝነት የተገላገለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መሆኑን በማያወላውል ሁኔታ ሲረዱ ( ሲገነዘቡ) ብቻ ነው።

ፀሃፊ ያሬድ ” ምንም እንኳ ሁለቱም የለመዱት ሰፊ ነፃነታቸው የሚሸበብ ቢሆንም ከምርጫው በፊትና በኋላ ያሉትን ወራት በውጥትን የተሞሉ ያደርጋቸዋል“ ሲል አስተያየቱን ይቋጫል ። ፣ አዎ! ውጥረት ይኖራል የሚለው ትንበያ ከምንገኝበት የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር ያስኬዳልና ትክክል ነው ።.

ነገር ግን በባለቤትነት በሚቆጣጠረው ሚዲያና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚያካሂደው አደገኛ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልላዊ መስተዳድሮችና እንዲሁም በአዲስ አበባ በአካል እየተገኘ ባደረጋቸው አደገኛ ቅስቀሳዎች ለአያሌ ንፁሃን መፈናቀል ፣ ለበርካታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደልድ እና ለብዙ ቤተ እምነቶች መቃጠል ግልፅ የሆነ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ያለምን ጠያቂና ገደብ እንዲንቀሳቀስ የተፈቀደለትን ጀዋርን በቢሮው ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠትና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ካልቻለው እስክንደር ጋር በማነፃፀር የለመዱት ሰፊው ነፃነት በሚል መግለፅ እንዴት ስሜት እንደሚሰጥ አላውቅም።

ጨርሶ የማይገናኙ የእስክንድርን እና የጀዋርን የፖለቲካ ሰብእና እና ተልዕኮ እያገናኘን ለንፅፅር (compare and contrast) ለምንና እንዴት   እንደምንጠቀምባቸው ጨርሶ ግልፅ አይደለም ። ሁለቱንም ፅንፈኞች  (extreme) እያልን የምንገልፅበት አገላለፅም ጨርሶ  ደምሳሳና እጅግ አሳሳች ነው። የሁለቱንም የፖለቲካና የሞራል ሰብእናዎች ፣ ንግግሮች ፣መግለጫዎች ፣ ማብራሪያዎች ፣ ቃለ ምልልሶችና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች  በጥሞና ለተከታተለና ለሚከታተተል የአገሬ ሰው እስክንድርን ጀዋርን ከመሰለ ከቃል እስከ ድርጊት የለየለት የጎሳ /የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ  ፖለቲካ ልክፍተኛ  ጋር በፅንፈኝነት ማነፃፀር ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ የፖለቲካ እይታ ሆኖ የሚያገኘው አይመስለኝም ።

ሚሊዮኖችን ከማፈናቀል እና የአያሌ ንፁሃንን ህይወት በግፍ እስከ መቅጠፍ የተፈፀመውን  ፖለቲካ ወለድ ወንጀልን  ቢያንስ በማነሳሳት ግልፅ ሚና የነበረውን (ያለውን) ጀዋርን  ለህግ ለማቀረብና አደብ ለማስገዛት ቢያንስ የሞራል ግዴታ ያልተሰማቸው  ገዥ ፖለቲከኞች የባልደራሱን ፍፁም ሰላማዊ የመብት ይከበር ጥያቄን ለማፈን የሄዱበት መንገድ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ የገጠመንንና የሚገጥመንን ብርቱ ፈተና ነው የሚነግረን ።

አዎ! እስክንድር አዲስ አበባ ኗሪዎቿ በሚመርጡት አስተዳደር የሚትተዳደር  እና የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሆነች የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ መሆን ሲገባት  ልዩ ፍላጎትና ጥቅም አለን የሚል ቅዠት የሚቃዡ የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች ልትታመስ አይገባም  ብሎ መከራከሩ ፅንፈኝነቱ  የት ላይ እንደሆነ ለመረዳት የሚቻል አይመስለኝም።

ከዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ ጀምሮ አሁንም የአዴፓ እና የደህዴን  ፖለቲከኞች በአሽከርነታቸው በቀጠሉበት የፖለቲካ አውድ  ተረኛ ነን ባዮች የኦዲፓ ፖለቲከኞች በሚዘውሩት  “የብልፅግና” ፖለቲካ  በአንድ ማህበረሰብ (አማራ ነው በሚሉት) ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ ይቁም ብሎ መከራከርና ለዚህም መፍትሄው በአብሮነት መቆምና በደልንና ግፍን መፀየፍ ነው ብሎ መታገል  በየትኛው የፖለቲካ ሳይንስና ተሞክሮ ፅንፈኝነት ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት እንዴት እንደሚቻል አላውቅም።

አዎ! ማህበራዊ ንቅናቄ (social movement) ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ያለው ሚና እና አስተዋፅኦ ችላ እንዳይባል ወይም እንዳይዘነጋ ከምር ማሳሰቡና ማስጠንቀቁ በጣም ትክክል ነው። የፀሃፊ ያሬድ አስተያየትም ከዚህ አኳያ የያዘውን መልእክት   ትክክልኛነትና ጠቃሚነት መገንዘብ   አያስቸግርም።

አዎ! ከአገራዊ ማህበራዊ ንቅናቄ ወርዶ በጎሳ/በዘር/በቋንቋ/በመንደር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ አሸን መፈልፈል የጨዋታ ሜዳን ማጥበብ ብቻ ሳይሆን የመጥፊያና የመጠፋፊያ መርዘኛ የወባ ትንኝን ማራባት ማለት ነው።

ከማህበራዊ ንቅናቄ ወደ ፖለቲካ ፓርቴነት መሸጋጋር መጥበብ ነው” የሚለው የመከራከሪያ ሃሳብ ግን ከፖሊቲካ ሳይንስም ሆነ ከተግባራዊ ተሞክሮ (አገራችን ጨምሮ) አንፃር ሲፈተሽ ብዙም አያስኬድም። የፖለቲካ ሎጅክነቱም (አመክንዮነቱም) ልፍስፍስ (clumsy) ነው።

ለተደጋጋሚ ውድቀታችን ምክንያቶች አንዱ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሚሆንባትና የድህነትን  አዙሪት ሰብራ በመውጣት በሁለንተናዊ የእድገት ግሥጋሴ ላይ ከሚገኘው ዓለም ተርታ የምትሰለፍ አገር ባለቤት  ለመሆን የሃሳብ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነና የሚበጀንን መፍትሄ ለማስገኘት በሚያስችል አኳኋን ለመፍታት ያለመቻላችን አዙሪት ነው።

የዚህን ትውልድ ፈተና ይበልጥ አስከፊ ያደረገው ለሥልጣን መወጣጫና ልክ ለሌለው የግል ወይም የቡድን ፍላጎታቸው ማርኪያ ሲሉ ለስሜታዊነት እጅግ ቅርብ የሆነውን የጎሳ/የቋንቋ/የመንደርተኝነት ፖለቲካ እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ እያራገቡ እንደ ደመነፍስ እንስሳ በጅምላ (በመንጋ) እንዲያስብና እንዲንቀሳቀስ  ሲያደርጉት “ከዘመን ሥልጣኔ ወደ ኋሊት እየጎተታችሁ መከራና ውርደቴን አታራዝሙብኝ” ለማለት የሞራልና የፖለቲካ አቅም ማጣቱ ነው።

የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞችም ይህን ደካማ ጎኑን  አሳምረው ስለሚያውቁት የሁሉም አይነት የፖለቲካ ትእይንትን ለማስተናገድ በማይታክተው ሚሊኒየም አዳራሽ እንዲታደም በማድረግ በድንቅ ሥነ ቃል ያዘጋጁትን ዲስኩራቸውን (ፕሮፓጋንዳቸውን) ቋቅ እስኪለው (እስከሚተናነቀው) ይግቱታል ። መግረም ሳይሆን በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ ሌላ ፖለቲከኛ ወይም ባለሥልጣን በአገር የጠፋ እስኪመስል ድረስ ሌላ እጅግ አሳሳቢና አጣዳፊ ሥራዎች የሌሉት ይመስል  ይህን የፖለቲካ ተውኔት  በዋናነት የሚተውነው ጠቅላይሚኒስትሩ መሆኑ ነው።

ከማህበራዊ ንቅናቄ መሪነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት መሸጋገር “መጠበብ ነው” የሚለው አስተሳሰብ የፓርቲ ፖለቲካ (party politics) ማለት የፖለቲካ ሥልጣንን ከመያዝ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አንፃር በመነሳት የሚደረግ ሰለማዊና ህጋዊ ትግል ነው ከሚለው መሠረታዊ ሃሳብ አንፃር ሲፈተሽ ወንዝ የሚያሻግር የፖለቲካ አመክንዮነት የለውም ።  መልሶና መላልሶ እየተንኮላሸ ካስቸገረን የፖለቲካ  አዙሪት ለመውጣት ያልቻልነው የማህበራዊ እንቅስቃቀሴዎችን (ንቅናቄዎችን) በግብአትነት ተጠቅመን  ሥልጣንን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ከሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ለመንጠቅ የሚችል የፖለቲካ ድርጅት ወይም ህብረት ለመፍጠርና ለማብቃት ባለመቻላችን እንጅ የማህበራዊና ሌሎች የብሶትና የቁጭት መገለጫ እንቅስቃሴዎች ስላልነበሩና ስለሌሉ አይደለም

ማህበራዊ ንቅናቄም እንበለው ወይም እንቅስቃሴ በዴሞክራሲያዊ  አስተሳሰብ ፣ ተልእኮ/ዓላማ ፣ግብ፣ መርህ  ፣ ስትራቴጅ እና የድርጊት ፕሮግራም የሚመራ የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) ፈጥሮ  (አቋቁሞ) በሸፍጠኛ ፖለቲከኞች (ገዥ ቡድኖች) የሚዘወረውን ሥርዓተ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓት መተካት   እስካልተቻለ ድረስ  ትርጉም ያለው ለውጥ መጠበቅ ጨርሶ የሚቻል አይሆንም።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን አይወድቁ ውድቀት እየወደቅን የመጣነውና አሁንም ከዚሁ አዙሪት ከመውጣት ይልቅ ከባድ ፈተና ውስጥ እራሳችን ያገኘነው የህወሃትን የበላይነት ያስወገደውን ግዙፍና መሪር ህዝባዊ እና ማህበራዊ ንቅናቄ (social and popular movement) እውነት ስለ እውነት የተደራጀና በማይበገር የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አርበኝነት በፅናት የቆመና የሚቆም የፖለቲካ ሃይል ወይም ድርጅት ወይም ስብስብ መፍጠርና ማጎልበት ባለመቻላችን ው።

በአፈጣጠራቸው ፣በባህሪያቸው ፣ በትግል ልምዳቸው (በተግባራዊ ተሞክሯቸው)፣ በአጠቃላይ ባላቸው ራእይና የግብ ተልእኮ  ጨርሶ የማይገናኙትን የፖለቲካ ሰብእናዎች “ፅንፈኞች” እያሉ መግለፅ ክፉ ልማድ ሆኖብን ከሆነ በተቻለ መጠን ለማስወገድ እንሞክር፤ ማሳመኛ የሚኖረን ከሆነ ደግሞ ከስሜታዊ አገላለፅ  ያለፈ ትንተና ወደ ፊት እናምጣና እንነጋገርበት ።

ያለዚያ ገዥ ቡድኖች በአድንቋሪ የግፍ አገዛዛቸው ለአያሌ ዘመናት ከእውነታው ጋር በማይገጥም ነገር ግን ለስሜት ቅርብ  በሆነ ደምሳሳ  ቃል ወይም አባባል  ያደነቆሩትን መከረኛ ህዝብ  በእንዲህ አይነት እጅግ ደምሳሳ በሆኑ አገላለፆች ወይም አባባሎች መልሰን መላልሰን ማደንቆር ነው የሚሆነው። አዎ! እስከ አሁን ባለው እውነታ ጨርሶ የማይገናኘውን የእነ እስክንድርን እና የነጀዋርንና መሰሎቹን አስተሳሰብና አካሄድ በጥንቃቄ ሳያስተውሉ  ሁለቱም ፅንፈፍ ላይ የቆሙ እንደሆኑ የሚያስመስል ጅምላ (ደምሳሳ) አነጋገር ወይም አፃፃፍ ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ግራ እያጋቡት ያለውን መከረኛ  ህዝብ ይበልጥ ግራ ማጋባት ነው የሚሆነው።

ለሩብ ምዕተ ዓመት የመጣንበት በጎሳ/በዘውግ/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ የተመሠረተው አምባገነን ሥርዓት በሌሎች ተረኛ ነን ባዮች በሚገርም ፍጥነትና ሸፍጠኝነት እየቀጠለ ነውና መሠረታዊ የዜግነት መብቶች እና የብሄረሰብ/የጎሳ መበቶችች በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሚከበሩበት ኢትዮጵያዊነት (አገራዊነት) ጥላ ሥር በመደራጀት ለምንኖርበት ዘመንና ትውልድ የሚመጥን ሥርዓት እውን እናድርግ  የሚለውን  የእነ እስክንድር እንቅስቃሴ በሂሳዊ አስተያየት መሞገት ትክክል ነው።

በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ማለትም ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቁ ኢህአዴጋውያን በመሪነት በማይዘውሩት ሥርዓተ ፖለቲካ እውን መሆን ላይ ከሚስማሙና ከሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች ጋር ተባብራችሁ ለመሥራት ዝግጁ ሁኑ የሚል ጠንካራ አስተየትና ምክር መለገስም በጣም ትክክል ነው ።

ከማህበራዊ ንቅናቄ መሪነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት  መሸጋጋር መጠበብ ነው፤ እኔ ስይዘው ይሳካ እንደሆነ ልሞክረው ባይነት ነው፤ ደጋፊን የሚያሳጣ ነው፤ ዓለም አቀፍ እውቅናን የሚቀንስ ነው የለመዱትን ሰፊ ነፃነት የሚሸብብ ነው፤ ወዘተ” የሚለው እይታና መከራከሪያ ግን ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ የፖለቲካ እይታ አይደለምና ከምር ልብ ልንለው ይገባል ።

 

Previous Story

ፍራሽ አዳሽ -5- ተስፋሁን ከበደ – ውሃ ውስጥ ሆኖ የሚያልበው አሳ ጦቢያ ግጥምን

Next Story

የግብጽ ባርነት ይሻለናል? – ኤፍሬም አሰፋ ክአዋሳ

Go toTop