ከሲዳማ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ለሚደረግ የትኛውም አይነት ድርደር ከሲድማ ኤጄቶች የተሰጠ የአቋም መግለጫ!!

April 24, 2019

የሲዳማ ህዝብ የራሱን ክልል መስርቶ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ከፍተኛ የሆነ የህይወትና የአካል መስዋእትነት ሲከፍል መቆየቱ ይታወቃል።

በዚህ ሂደት በተለያዩ ግዜያት የሲዳማ ህዝብ መብቱን ለማስከበርና ህገ መንግስቱ ገቢራዊ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ህገ መንግስታዊ ሂደቶችን ጨርሶ ወሳኝ ደረጃ ከደረሰ በኋላ አላስፈላጊ መደለያዎችንና መደራደሪያዎችን በማቅረብ እንዲሁም ታጋዮችን ነጥሎ በመምታትና በማሸማቀቅ ጥያቄያችንን ለመቀልበስ አደገኛ ፖለቲካዊ ሴራ ሲዘራ እንደነበር ይታወሳል።

አሁን የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ የደረሰበት ደረጃና ግዜ ለህጋዊ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ የሚፈልግ እንጂ ድርድር የሚደረግበት አይደለም።

ይሁን እንኳን ቢባል እስከ ዛሬ ኤጄቶ ስያንጸባርቅ ለነበረው ሰላማዊ ተጋድሎ ጆሮ ሳይሰጥ የቆየው የፌደራል መንግስት ዛሬ የራሳችንን ክልል በራሳችን ለማወጅ ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ባለንበት ዋዜማ ህዝባችንን ጥርጣሬ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ከፋፋይ ደኢህዴናዊ አጀንዳ በማምጣት ጥያቄያችንን ለመቀልበስ አልያም ጋብ እንዲል የሚደረጉ ርብርቦች መርህ የለሽ እንቅስቃሴዎች ከመሆናቸውም ባለፈ በትግላችን ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ የሚፈጥሩ አለመሆናቸው ግልጽ ነው።

በዚህም መነሻነት የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ቀን ተቆርጦ ለህዝባችን ይፋ እስኪደረግ ከየትኛውም የፌድራል አመራር ጋር ምንም አይነት ድርድር እና ውይይት ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆናችንን አጥብቀን እናሳውቃለን።

ይህ በእንዲህ እናዳለ ህገ መንግስቱ ህዝበ ውሳኔ ለማደራጀት ለክልሉ ም/ቤት የሰጠው ቀነ ገደብ 85 ቀን ብቻ የቀረው ሲሆን በነዚህ ቀሪ ቀናት ውስጥ የሪፈረንደም ቀን ተቆርጦ ወደ ህዝበ ውሳኔ የማይገባ ከሆነ የሲዳማ ዞን ም/ቤት የሲዳማን ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲያጸድቅ አስፈላጊውን ጫና ሁሉ ለመፍጠር የምንቀሳቀስ መሆኑን አጥብቀን እናሳውቃለን።

ሲዳማ ኤጄቶ

Previous Story

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕረስ ሴክሬተሪ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በኢትዮጵያና ቻይና መሪዎች ውይይት ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ

Next Story

ይቅርታ እና ይቅር ባይነት – በዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Go toTop