በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለንባብ ለሚበቃው መንግስታዊው ‹‹ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ስምምነት ሊፈፅሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=SvwytfrDZTg&t=73s
ይህም በሁለቱ አገራት መሀከል ያለውን አዲስ ግንኑነት በህጋዊ ማእቀፍ ለማረጋገጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአገራቱ መሀከል የሚኖረውን የንግድ ልውውጥ በተመለከተ ሰፊ ውይይት መደረጉን የጠቀሱት አምባሳደር ሬድዋን በዚህ ውስጥ የወደብ አጠቃቀም፣ የጉምሩክ አሰራር፣ የሰዎች ዝውውርና የትራንስፖርት ግንኙነት ላይ ስምምነት ተደርጎ የተደረሰበት ውጤት የሁለቱም አገራት መሪዎች ጠረንጴዛ ላይ ለፊርማ መቀመጡን ገልፀዋል፡፡ ይህ ስምምነት የሚፈፀው ግን የሁለቱም አገራት ፓርላማዎች ተወያይተውበት ከፀደቀ በኋላ እንደሆነ አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡ በተያያዘ ዜና በአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ትብብርና ልማት ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ጉብኝት አደርገዋል፡፡
በዚህ ጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን ድንበር ከኤርትራ ወደቦች ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ግንባታ ለመደገፍ መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ በጉብኝታቸው ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸውን የተሰራጨው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ውይይቱም በተለይ በአውሮፓ ህብረትና በኤርትራ መሀከል ያለውን ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማደስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡ ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ ‹‹የአውሮፓ ህብረት የ20 አመታት ግጭታቸውን ፈትተው ታሪካዊ ሰላም የፈጠሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፡፡
ይህ ሰላም ለሁለቱም አገራት ዜጎች ዘላቂነት ያለው እድገት ለማምጣትና የስራ እድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ አለው›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም 22 ነጥብ 69 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚፈጀውን ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል፡፡ በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ትረስት ፈንድ በኩል ወጪ የሚሆነው ይህ ገንዘብ የኢትዮጵያን ድንበር ከኤርትራ ወደቦች ማለትም ከአሰብና ምፅዋ ጋር ለሚያገናኙ መንገዶች ጥገና እንደሚውል ታውቋል ሲል አፍሪካን ሪቪው ዛሬ ዘግቧል፡፡