በለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ቤታቸው የፈረሰባቸው ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ አቶ ለማ መገርሳን ማነጋገር አትችሉም ተባሉ

February 20, 2019

 

https://www.youtube.com/watch?v=SvwytfrDZTg&t=73s

የለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር አረንጓዴ ቦታዎችን፥ የወንዝ ዳርቻዎችን፥ ከፈቃድ ውጭ የተያዙ እና ካሳ ተከፍሎባቸው ግንባታ የተካሄደባቸው ናቸው ያላቸውን ቤቶች ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ሲያፈርስ ዋለ::

ትናንት ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ግለሰቦች ዛሬ ጠዋት ተሰባስበዉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳን አቶ ለማ መገርሳ ቢሮ አቤቱታቸውን ለማቅረብ  ቢያመሩም እሳቸዉን ማናገር አትችሉም ተብለው ወደ ክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ  ተልከዋል:: ነገር ግን ከክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮም ያገኙት ምላሽ “ቤታችሁ ከመፍረስ አይድንም። ልንተባበራችሁ አንችልም” የሚል መሆኑን ቤታቸው የፈረሰባቸው ወገኖች ገልጸዋል::

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በመቀጠል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቢያመሩም “ጉዳያችሁን እዛዉ ኦሮሚያ አስተዳደር ጨርሱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸዉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

“መንግሥት ጎዳና የወጡትን እንሰብስብ ሲል ደስ ብሎን እኛም ገንዘብ እያዋጣን ነበር። ነገር ግን በምትኩ ቤታችን የተቀመጥነውን ወደጎዳና እያባረርን ነዉ። እቃ እራሱ ማውጣት አልቻልንም ከነቤታችን ነዉ እየፈረሰ ያለው” ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

በዛሬው ዕለትም የማፍረስ ተግባሩ የቀጠለ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች በቤተ ክርስትያንና በመስኪዶች ተጠልለው ማደራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ ከተሞች የህገ ወጥ ግንባታ መስፋፋት እንዳለ በጥናት ማረጋገጡን የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቆ እንደነበር ከዚህ ቀደም ተዘግቧል::

በዚህም በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር 67 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት እና በቤት ደረጃ ከ12ሺ በላይ ቤቶች በህገወጥ መንገድ መገንባታቸውን መለየታቸውን ተገልጾ ነበር።

ነገር ግን የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ አሰተዳደር በከተማዋ በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ናቸው ያላቸውን ከ3ሺህ በላይ ቤቶች በዚህ ሳምንት ብቻ የማፍረስ እቅድ እንዳለሁ በመግለጽ የከተማው ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ ለኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ ”የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ፕላንን ለማስከበር የወሰነውን ውሳኔ እያስከበርን ነው። ከፕላን ጋር የሚቃረኑ ቤቶችን እያፈረስን ነው። ለከተማ ሳንባ የምንላቸውን አረንጓዴ ስፍራዎችን እና ከወንዞች እረቀው ያልተሰሩ ቤቶችን እናፈርሳለን” ሲሉ ተናግረዋል::

Previous Story

በሸዋ ሮቢት ከተማ ጎማ እየተቃጠለ ለሰአታት መንገድ ተዘግቶ ዋለ

Next Story

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ስምምነት ሊፈፅሙ ነው”

Go toTop