አቶ ለማ መገርሳ ‹‹ዶክተር አብይን በጉልበት እሳት አቀጣጥለን እናስወጣዋለን የሚሉ ከመጡ እንሟሟታታለን እንጂ አይለቅም›› አሉ

December 22, 2018

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንቱ አቶ ለማ መገርሳ ከሰሞኑ በቤተመንግስት ከኦሮሞ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት በኦህዲድና በህወሃት መሀከል የነበረው ግጭት የቆየ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ብዙ ሰው የኢህአዲግን ሊቀመንበር ለመምረጥ የተደረገው የ17 ቀናት ፍጥጫ እንደሚመስለው ያወሱት አቶ ለማ ሲናገሩ ‹‹ጉዳዩ የተጀመረው በ17ቱ ቀናት አይደለም፣ ቆይቷል፡፡ ትግሉ ከጀመረም ሰንብቷል፡፡ ዛሬ እዚህ አንናገረውም፣ አንድ ቀን ታሪክ ያወጣዋል›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ለሰባትና ስምንት አመታት ስንታደን የነበርን ሰዎች ነን፡፡ ሰዎች ተመድበውብን፣ ስንወጣና ስንገባ እየተከታተሉ ያስፈራሩን ነበር፡፡ ከነበርንበት ሃላፊነት የተባረርን ሰዎችም ነን፡፡ ዛሬ አይደለም ትግሉ የተጀመረው›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በሌብነትና በሰብአዊ መብት ጥሰት ስለታሰሩት ግለሰቦች ጉዳይ ሲያስረዱ ደግሞ ‹‹እነዚህ ሰዎች ከሰማይ በታች የሚፈሩ ነበሩ፡፡ በእናና በእናንተ ጭምር የሚፈሩ ነበሩ፡፡ ቀና ብሎ ለማየት የሚፈሩ ጭምር የነበሩ ናቸው፡፡ ህግ በዚህች አገር ከማንም በላይ እንደሆነና የትኛውም ወገን ተይዞ እንደሚታሰር ግን ማሳየት ተችሏል፡፡›› ብለዋል፡፡

ከአንዳንድ ወገኖች ሪፎርም አልመጣም ተብሎ የሚሰማውን ቅሬታ በተመለከተ አቶ ለማ ሲያስረዱ ‹‹ሪፍርሙን ለማምጣት ማንም የማይላተመውን ምሽግ ማፈራረስ ያስፈልጋል፡፡ እሱ ፈራርሶ መሬቱ ሲስተካከል ነው ሊታረስ የሚችለው፡፡ ሊዘራበትም የሚችለው፡፡ አሁን በየቀኑ እየጠሰራ ያለው ይህንኑ ማፍረስ ነው፡፡ የዚህች አገር ችግር የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አንዱን ከወንበር አንስቶ ሌላውን የመተካት ጉዳይ ሳይሆን የስርአት ችግር ነው፡፡›› ካሉ በኋላ የነበረው ስርአት አንድ ግለሰብ እንደግል ኩባንያው ለእሱ እንዲመቸው አድርጎ የዘረጋው እንደነበር አውስተዋል፡፡ የ

ድንበር ጉዳይን በተመለከተ ጎልቶ ባይወጣም ላለፉት 20 አመታት ሲያስቸግር የቆየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ለማ ከባለፈው አመት ጀምሮ ግን ጦርነት እንደተከፈተባቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ሲዋጉ የነበሩት በአሻጥርና ደባ ሌሎች እንደነበሩን አስረድተዋል፡፡ ሲናገሩ ‹‹በማስተዋል አለፍነው እንጂ ችግር ውስጥ የምንወድቀው አምና ነበር፡፡ አምና በሱማሌ በኩል ከሞያሌ አንስቶ እስከሃረር አንድ ቀን ውጊያ ገጥመናል፡፡ ከፍተኛ መሳሪያ የታጠቀ፣ ጠንካራ ስልጠና ያለው፣ ከኋላ ጠንካራ ድጋፍ የሚደረግለት ከ50 ሺህ በላይ ወታደሮች ተሰማርተውብን ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡ እነዚህ በስም ያልጠቀሷቸው ሀይሎች በዚያ በኩል ሲያቅታቸው ወደደቡብ ችግሩን እንደወሰዱትም ጠቅሰዋል፡፡

በሞያሌ ዛሬ ሰላም ሆኖ ነገ እሳት የሚነሳበት ምክንያት እነዚህ ሀይሎች እዚያ ብዙ አመታት ስለቆዩና ጠንካራ ኔትወርክ ስላላቸው መሆኑን ተናግረውም እዚያ የዘሩት ዘር ስሩ እንዳልተነቀለ አስረድተዋል፡፡ በጉጂና በጌዲዮ ህዝብ መካከል ለተፈጠረው ግጭት፣ በቤኒሻንጉል ለተፈጠረው ጦርነትሁሉ የእነዚህ አካላት እጅ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ‹‹እኛ እዚህ ቤተመንግስት የገባለው የኦሞ ቤተመንግስት ልናደርገው አይደልም›› ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ኦሮሞ የገባው የእውነትና የሀቅ ቤተመንግስት ሊያደርገው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ኦሮሞ ብቻ የሚጨፍርበት ቤተመንግስት ካደረግነው እኛም እንደትላንቶቹ ሰዎች እንሆናለን፡፡ እኛ እሱን አንፈልግም፡፡ ‹‹በህግና በምርጫ ዶክተር አብይ ከዚህ ቤተመንግስት መውጣት ባለበት ቀን መውጣት አለበት፡፡ በጉልበት መቆየት አለበት ብለን አናምንም፡፡ ግን ኦሮሞ በመሆኑ በጉልበት እሳት አቀጣጥለን እናስወጣዋለን የሚሉ ከመጡ እንሟሟታታለን እንጂ አይለቅም›› በማለት ከኦሮሞ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት አስረድተዋል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=et9pbbzq6mg&t=36s

Previous Story

ደምስ በለጠ ከአገሩ ከወጣ ከ30 አመታት በኋላ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ በገባ በ21 ቀኑ በተኛበት አርፎ ተገኘ

Next Story

በሃዋሳ አንድ ሌትር ቤንዚን 70 ብር እየተሸጠ መሆኑ ተሰማ

Go toTop